“ነጭ የለበሰ ‘መልአክ’ በኦሮምኛ አናገረኝ”- የሬሳ ሳጥን ፈንቅለው የወጡት ግለሰብ

ሰው ነፍሱ ከሥጋው ተለየች የሚባለው መቼ ነው? ምን ሲሆን?

አቶ ሂርጳ ነገሮ ለዚህ ፍንጭ ሊሰጡን የሚችሉ ሁነኛ ሰው ናቸው፤ የቅርብ ጊዜ ምሥክር። ትውልዳቸው ከወደ ምሥራቅ ወለጋ ሲቡ ስሬ ወረዳ ነው።

ዘለግ ላለ ጊዜ በጽኑ ታመው ቆይተዋል። ከ2 ዓመት በፊት ሆድ ዕቃቸው ተከፍቶ በቀዶ ጥገና ታክመዋል። የጤና ታሪካቸው በአጭሩ ይኸው ነው።

ማክሰኞ ረፋድ ላይ ግን ድንገት ደካከሙ። በዚያው ዕለት 4፡00 ሰዓት ላይ ሞቱ [ተባለ]። ጥሩምባ ተነፋ፣ ጥይት ተተኮሰ፣ ድንኳን ተጣለ፤ ለቀስተኛ ተሰበሰበ፤ ሬሳ ተገነዘ።

ከአራት ተኩል ሰዓታት በኋላ ግን አቶ ሄርጳ[ሳጥን ፈንቅለው ወጡ]፤ ‘ኢጆሌ ኢጆሌ እያሉ….’። ይህ የኾነው ማክሰኞ ‘ለታ ተሲያት ላይ ነው። ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከእርሳቸው ጋር የስልክ ቆይታ አድርጓል። በ’ሞቱበት’ ሰዓት ያለ ቀጠሮ ያገኙት ‘መልአክ’ ምን ሹክ እንዳላቸው ጭምር አብራርተዋል።

ኾኖም መቅደም ያለበትን እናስቀድም። አቶ ኢታናን፤ ገናዣቸውን።

ቢቢሲ፦ ሳይሞቱ እንዳይሆን አጣድፋችሁ ሳጥን ውስጥ የከተታችኋቸው።

አቶ ኢተና፦ “ዛሬ አይደለም እኮ ሰው የገነዝኩት [ቆጣ አሉ]። ስንትና ስንት ሰው ገንዣለሁ። ትና ስንት…”

ቢቢሲ፦ እና ሳጥን ውስጥ ሲከቷቸው ትንፋሽ አልነበራቸውም? እርግጠኛ ኖት?

አቶ ኢታና፦ [ምን ነካህ!] ስንትና ስንት ሰው ሲሞት ይቻለሁ። ስንትና ስንት አው ገንዣለሁ። መሞቱን አረጋግጬ ነው ሳጥኑ ውስጥ ያስገባሁት። ዝም ብዬ እከታለሁ እንዴ [የምር እየተቆጡ መጡ]

ቢቢሲ፦ ታዲያ እንዴት የሞቱ ሰውዬ ሊነሱ ቻሉ?

አቶ ኢተና፦ እንጃ! እንዲህ ዓይነት ነገር ሆኖ አያውቅም። ይሄ ከእግዛቤር የሆነ ነው እንጂ

እሑድ ሊናዘዙ ቀጠሮ ነበራቸው

“ሞቼ ተነሳሁ” የሚሉት አቶ ሂርጳ በሽታቸውን በውል አያውቁትም። ኾኖም እምብርታቸው አካባቢ ለረዥም ጊዜ ይቆርጣቸው ነበር። ነገርየው የጉበት ሕመም ሳይሆን እንዳልቀረ ይጠረጥራሉ። ሐኪምም ዐይቷቸዋል። የፈየደላቸው ነገር ባይኖርም።

መጀመርያ ነቀምት ሆስፒታል፣ ከዚያ ደግሞ ጥቁር አንበሳ ‘ሪፈር’ ተብለው ሄደዋል። ደንበኛ ምርመራ አድርጊያለሁ ነው የሚሉት። ኾኖም የምርመራ ውጤቱ አልተነገራቸውም። በታኀሣስ 1፣ ሊነገራቸው ቀጠሮ ተይዞ ነው በዚያው ‘ያሸለቡት’።

በዚያ ላይ ለመዳን ከነበረ ጽኑ ፍላጎት የተነሳ በሬ ሽጠዋል። ዘመድ አዝማድ ተቸጋግሯል። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄዶ ለመታከም።

ከሰሞኑ ጉልበት ሲከዳቸው ታዲያ እንደማይተርፉ ጠረጠሩ። ያለቻቸውን ጥሪት ለአምስት ልጆቻቸው ሊናዘዙ ፈለጉ። ሰኞ ሊሞቱ እሑድ ዕለት ለመናዘዝ ቀጠሮ ተይዞ ነበር። ያጋጣሚ ነገር ኾኖ በዕለቱ የበኩር ልጃቸው ስላልነበረ ኑዛዜው ላልተወሰነ ጊዜ ተላለፈ። ማክሰኞ ‘ለት ‘ሞቱ’።

“ሬሳ ሳጥን የሰጠሁት እኔ ነኝ”

ገናዥ አቶ ኢታና ቤተሰብም ናቸው፤ ጎረቤትም ናቸው። ‘ሟች’ የወንድማቸው ልጅ ናቸው። 3ሺህ የሚያወጣ ሬሳ ሳጥን በታላቅ ቸርነት ያበረከቱትም የገነዙትም እርሳቸው ናቸው።

“ጋዜጠኞች ትናንት መጥተው ዐይተዋል። የወንድሜ ልጅ ስለሆነ የራሴን ሳጥን ሰጠሁት” ይላሉ።

ቤተሰቡን ከወጪ ለመታደግ ነው ታዲያ ይህን ያደረጉት። ሳጥኑ ውስጥ ልብስ ምናምን ነበር የሚቀመጥበት። ምናምኑን ሁሉ ወለል ላይ ጣጥለው፣ አራግፈው፣ የወንድማቸውን ‘ሬሳ’ በክብር አኖሩበት።

“ነጭ ልብስ የለበሰ መልአክ ተመለስ አለኝ”

እጅግ በተረጋጋ ሁኔታ የሚያወጉት አቶ ሄርጶ በሰማይ ቤት ቆይታቸው የተመለከቱትን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

እርግጥ ነው አንዳንድ ነገሮች ተዘንግተዋቸዋል። አንዳንዶቹ ትውስ ይሏቸዋል፣ ኾኖም በጠራ መልኩ አይደለም። አንዳንዶቹን ነገሮች ግን አጥርተው ማስታወስ ይችላሉ። ልክ ዛሬ የኾነ ያህል።

ለምሳሌ በሰማይ ቤት በብረት ሰንሰለት የሚታጠር ግቢ ብዙ ሺ ሰዎች ተሰብስበው ተመልክተዋል። አጥሩ ከምን እንደተሠራ ግን አያስታውሱም፤ በሩ የብረት ይሁን የሳንቃ ትዝ አይላቸውም። አካባቢው ደጋና ልምላሜ የወረሰው እንደነበር ያስታውሳሉ። ኾኖም የሰማይ ቤቱ መልከዐምድር አይከሰትላቸውም።

ከሁሉ ከሁሉ ያልዘነጉት ግን ከባድ ንፋስ ይነፍስ እንደነበረ ነው። ክብደቱን ሲገልጹ ድምጻቸውን ሁሉ ይበርደዋል።

ሰዎች ተሰብስበውበታል ከሚሉት ከዚያ ግቢ ታዲያ ማንንም አያውቁም። ከሦስት ሰዎች በቀር። እነርሱም ከ2 ዓመት በፊት የሞቱትን አባታቸው፤ ከዓመታት በፊት የሞቱትን አማቻቸውን እና አንድ ሌላ አጎት ናቸው።

ከሦስቱ ጋር ምን እንዳወጉ በውል አያስታውሱም። የሚያስታውሱት “እኛን ተከተለን” ብለዋቸው ቢከተሉ፣ ቢከተሉ፣ በፍጥነት ቢራመዱ፣ ቢሮጡ ሊደርሱባቸው እንዳልቻሉ ነው። ነገሩ የሕልም ሩጫን ይመስላል።

ቀዩን መልአክ ግን መቼም አይረሱትም። በሁለተኛው ምዕራፍ የሕይወት ዘመናቸውም የሚረሱት አይመስልም።

ቢቢሲ፦ መልአኩ ቀይ ነው ጥቁር?

አቶ ሂርጶ፦ ነጭ ነው፤ ቀይ ነው…ጌታን ኢየሱስንም ይመስላል

ቢቢሲ፦የሰው መልክ ነው ያለው ወይስ የመልአክ?

አቶ ሄርጶ፦ፊቱ በደንብ አላየሁትም። ወደ አጥሩ ቆሞ እኔ ውጭ ነበርኩ። መልኩ ቀይ ነው ነጭ ልብስ ይለብሳል። ሰዎቹን ወደ ውስጥ አስገባና ይዟቸው ሄደ

ቢቢሲ፦ሌላ መልአክ አልነረም አጠገቡ?

አቶ ሄርጶ፦ አላስታውስም፤ እሱን ብቻ ነው ያየሁት

ቢቢሲ፦ምን አሎት?

አቶ ሄርጶ፦ ‘አንተ የት ትሄዳለህ? ተመለስ!’ አለኝ።

ቢቢሲ፦በምን ቋንቋ ነው ያናገርዎት?

አቶ ሄርጶ፦ በኦሮኛ።

ቢቢሲ፦ አልፈሩም?

አቶ ሄርጶ፦ አቅም አጣሁ እንጂ አጥሩን ኬላውን አልፌ ብገባ ደስ ባለኝ ነበር።

“ኢጆሌ ኢጆሌ…”

ማክሰኞ ተሲያት ላይ ከሬሳ ሳጥኑ ውስጥ ድምጽ ሲሰማ የአጋጣሚ ነገር በቅርብ የነበሩት የ’ሟች’ እናትና ባለቤቱ ነበሩ። “ኢጆሌ ኢጆሌ…” ይላል ድምጹ። ሚስትና እናት ራሳቸውን አልሳቱም፤ በርግገው ከአካባቢው ተሰወሩ እንጂ። ድምጹ አልቆመም። “ኢጆሌ ኢጆሌ ነምኒ ሂንጂሩ?…”

ለቀስተኛው ግማሹ እግሬ አውጪኝ አለ። ግማሹ የሚይዘው የሚጨብጠውን አጣ። የሰሙት ሬሳው እየጮኸ እንደሆነ ተናገሩ። ለመጠጋት የደፈረ አልነበረም። ከገናዣቸው በስተቀር። “ወንዶቹ ሁሉ ጥለው ጠፉ” ይላሉ አቶ ኢታና።

ቢቢሲ፦ እርስዎ ግን አልፈሩም?

አቶ ኢታና፦ ለምን እፈራለሁ፤ ሬሳውን ማስቀመጤን አውቃለ

“ከዚህ በኋላ የምኖረው ትርፍ ሕይወት ነው”

ያን ‘ለታ ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ሚሪንዳ ቀመሱና ነፍሳቸው መለስ አለች። ሲረጋጉ ዘመድ አዝማድ መሰብሰቡን አስተዋሉ። እልልታና ለቅሶም ሰሙ። “ምንድነው ይሄ?”። ‘ሞተው ነበረኮ’ ተባሉ።

“እንኳን በሰላም ገባህ፤ እንኳን በሰላም ተመለስክ ብለው ተደሰቱ” ይላሉ የወቅቱን የለቀስተኛውን መደነቅና ደስታ ለቢቢሲ ሲያስረዱ።

“ተጸጸቱ እንዴ ግን? ወደ ሕይወት በመመለስዎ?” ብለናቸው ነበር።

“እዛ ብሆን ጥሩ ነበር…። ግን አሁን ቅር የሚለኝ ነገር የለም። ወደ ልጆቼ፣ ወደ ቤተሰቤ በመመለሴ በጣም ደስ አለኝ።”

ከዚህ በኋላ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ ሲጠየቁ ጊዜያቸውን የሃይማኖት ትምህርት በመስጠትና የተጣሉ ሰዎችን በማስታረቅ ለማሳለፍ እንዳሰቡ ተናግረዋል።

Image copyrightSIBU SIRE COMMUNICATION
አጭር የምስል መግለጫለቀስተኞች

ወለጋ ሲቡ ስሬ ወረዳ እነ አቶ ሄርጳ ቤት ዛሬም ለለቅሶው ሲባል የተተከለው ድንኳን ባለበት አለ። “ሰዎች በብዛት እየመጡ ነው። እንደለቅሶ ነው የሚመጡት” አሉ ገናዡ አቶ ኢታና።

ጥቁር አንበሳ ቀጠሮ አላቸው

“ከመሞቴ በፊት ከነሐሴ ጀምሬ እንጀራ በልቼ አላውቅም” የሚሉት አቶ ሄርጳ “አፌም እንደዚህ መናገር አይችልም ነበር” ይላሉ።

ከሬሳ ሳጥን ከወጡ በኋላ ግን ሕመማቸው ሙሉ በሙሉ ድኖ በሶም እንጀራም መቀማመስ ጀምረዋል። ድምጻቸው ደከምከም ይበል እንጂ ዘለግ ላለ ሰዓት እንደልብ ያወራሉ።

የተዘነጋው ጉዳይ! ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቀጠሮ አላቸው። ለታኅሣሥ አንድ። ለውጤት ነው የተቀጠሩት።

ከዚህ በኋላ ሐኪም ዘንድ ይሄዳሉ? ተብለው ሲጠየቁ ታዲያ መልሳቸው አጭርና ፈጣን ነው። “ለምን ብዬ!”

source : BBC

Follow us @ www.facebook.com/wasihune.tesfaye