” ትግራይ ልትገነጠል ትችላለች የሚሉ ሰዎች፡ የትግራይን ህዝብ ማንነት ጠንቅቀው የማያውቁ ሰዎች ናቸው ፡፡ (ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ኃይማኖት ጆቤ )

ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ኃይማኖት ስለ ትግራይ መገንጠል –

ኢትዮጲስ፡ ሕወኃት እያሳየ ባለው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች፤ ትግራይን እስገመገንጠል ሃሳብ እንዳለው የሚገልፁ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ምን ያህል ትክክል ነው?

ጄነራል አበበ፡- ትግራይ ልትገነጠል ትችላለች የሚሉ ሰዎች፡ የትግራይን ህዝብ ማንነት ጠንቅቀው የማያውቁ ሰዎች ናቸው፡፡ የትግራይ ህዝብ ራሱን እንደ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ህዝብ ነው፡፡ ራሱን ኢትዮጵያን ከመሰረቱ ህዝቦች አንዱ አድርጎ ነው የሚያየው፡፡ እያንዳንዱ የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምንና የሚኮራ ህዝብ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ አይደራደርም፡፡ ራሳቸውን ብቻ እንደ ኢትዮጵያዊ በመቁጠር፡ የትግራይን ህዝብ ገለልተኛ ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች በጭራሽ የትግራይን ህዝብ አያውቁትም፡፡

የትግራይን ህዝብ የፈለገውን ልትለው ትችላለህ፡፡ ነገር ግን፡ በኢትዮጵያዊነቱ ልትመጣበት አትችልም፡፡ ሕወኃትም ይህን ስለሚያውቅ የመገንጠል ሙከራ ያደርጋል ብዬ አላስብም፡፡ እኔ በግሌ ሕወኃት በሚከተለው በርካታ አጀንዳዎች የማልስማማ ቢሆንም፡የመገንጠል አጀንዳ ግን አለው አልልም፡፡ ሕወኃት ይህንን ሃሳብ እንኳን ቢይዝ፡ የትግራይ ህዝብ እንደማይቀበለው ስለሚያውቅ፡ መገንጠልን እንደ አማራጭ ያነሳል የሚል እምነት የለኝም፡፡

ሰዎች ትክክለኛ መረጃና ግንዛቤው ሳይኖራቸው ስለ አንድ ነገር በስማ በለው ሲናገሩ ታዝቤያለሁ፡፡ ከየት ሰማህ? ማን ነገር? ለሚለው ተጨባጭ ማስረጃ የላቸውም፡፡ብቻ እየተቀባበሉ አንዱ የተናገረውን ለሌላው ማስተጋባት ነው፡፡አንዱ ሕወኃት ትግራይን የመገንጠል ዓላማ አለው ካለ ሳያጣራ የሰማውን ለሌላው ያሰራጫል፡፡ ለሌላውም እንደዚሁ ያሰራጫል፡፡ ይህም የመንጋ ፖለቲካ ነው፡፡

ኢትዮጲስ ጋዜጣ፡ ኅዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም
_________