በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠ

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ዐኛ የወንጀል ችሎት በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት፣ ፌደራል ፖሊስና ማረሚያ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በነበሩት ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ፡፡

ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጉሃ አጽብሃ፣ አማኑኤል ኪሮስ፣ ደርበው ደመላሽ ፣ኢዮብ ተወልደና ሸዊት በላይ ይገኙበታል፡፡

ከብረታ ብረትና ኢንጀነሪንግ ኮርፖሬሽን ደግሞ ብርጋዴር ጀነራል ጠና ቁርንዲ ፣ብርጋዴር ጀነራል በርሃ በየነ ፣ብርጋዴር ጀነራል ጥጋቡ ፈትለ፣ ብርጋዴል ጀነራል ሃድጉ ገብረጊዮርጊስ ይገኙበታል፡፡

ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮማንደር አለማየሁ ሃይሌ ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሀሰን ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፋይኔና ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜም ይጠቀሳሉ፡፡

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ዐኛ የወንጀል ችሎት ባቀረበው የአቤቱታ መዝገብ በተለይም የሜቴክ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ሜጋ ፕሮጀክቶች በተገቢው መንገድ እንዳይከናወኑ አድርገዋል የሚለውን ጠቅሷል፡፡

ስልጣናቸውን ሽፋን በማድረግ ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ህገ-ወጥ ግዢ በመፈፀም ለራሳቸውና ለሌሎች ያልተገባ ጥቅም ለማስገኘት በመንቀሳቀሳቸው በከባድ የሙስናና የመንግስትን ስራ በማይመች አኳኋን መምራት ወንጀል ተጠርጥረዋል፡፡

ፖሊስ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን 14 ቀን ሲጠይቅ ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ግራ ቀኙን የመረመረው ችሎቱ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን ፈቅዷል፡፡

ችሎቱ ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ፌደራል ፖሊስና ማረሚያ አስተዳደር ተቋማት በከፍተኛ የስራ ኃላፊነት እና ባለሙያ ሆነው ይሰሩ የነበሩ 33 ግለሰቦች የተካተቱበትን የምርመራ መዝግብ ተመልክቷል፡፡

ከደህነት ጉሃ አፅብሃ ፣ አማኑኤል ኬሮስ፣ ደርበው ደመላሽ፣ ተስፋዬ ገ/ፃዲቅ፣ ሸዊት በላይ፣ እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮማንደር አለማየዑ ሃይሌ፣ ምክትል ኢንስፒክተር የሱፍ ሃሰን፣ ከማረሚያ ደግሞ ኦፌሰር ገ/ማሪያም ወልዳይ ዋና ሱፐር ኢንተዴንት አሰፋ ኪዳኔ እና ኦፊሰር አስገለ ወ/ጊዮርጊስ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡

በተለይም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በሽብር ወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን አፍነው በመያዝ አይናቸውን በጨርቅ በመሸፈን የሚወሰዱበትን ቦታ እንዳያውቁ ስውር ቦታ በማሰር ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙና ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ በማድረግ ኢሰብአዊ ድርጊት ፈፅመዋል በሚል ወንጀል ነው የተጠረጠሩት ብሏል ፖሊስ በምርመራ መዝገቡ፡፡

ችሎቱ ግራ ቀኙን በመመርመር ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን የምርመራ ግዜ ፈቅዷል፡፡

አዳነች ተሰማ፣ ጌታቸው አሰፋና ሙሉ ፍስሃ የተሰኙ ተጠርጣሪዎች ከሌሎች የተቋማት ኃላፊዎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አፍርተው ተገኝተዋል በሚል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡

ፍርድ ቤቱ የእነዚህ ግለሰቦች የወንጀል ዝርዝር ተደራጅቶ እንዲቀርብለት 3 ቀናት ፈቅዷል፡፡

Source ፡EBC