በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በግራዋ ወረዳ ሙደና ጅሩ በሊና በምትባል የገጠር ቀበሌ ውስጥ ከአርብ ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከሰማይ በሚወርድ እሳት ከ40 በላይ የሳር ቤቶች ተቃጠሉ፡፡
የአደጋውን መንስኤ ለማጥናት እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነና እስካሁን በደረሰው ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሱ ውጪ በሰው ህይወት መጥፋት እንዳልተከሰተ ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከሀረር ከተማ እስከ 110 ኪሎ ሜትር በሚገመት ርቀት ላይ የሚገኘው የሙደና ጅሩ በሊና በግራዋና በዶጉ (የገጠር ከተማ) ከተሞች መካከል የሚገኝና የፈዲስ ወረዳና ዶጉ ከተማንም የሚያዋስን በጎቤሌ ሸለቆ (ሰርጥ) ውስጥ የሚገኝ በጣም ሞቃታማ ቀበሌ ነው፡፡ በዚህ ቀበሌ ውስጥ ከዓርብ ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከሰማይ ወረደ በሚባለው የእሳት ፍንጥቅጣቂ (በኦሮምኛ ቃንቄ) 42 የሳር
ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡
አደጋው እንደደረሰ ቤቶቹን ሰዎች በእሳት አያይዘዋቸው ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ የአካባቢው ማህበረሰብና የፀጥታ አካላት አካባቢውን ከበው የጥበቀና የክትትል ስራ የተከናወነ ቢሆንም የሳርቤቶቹ የቃጠሎ መንስኤ ከሰማይ በሚወርደው ፍንጥቅጣቂዎች መሆኑ በመረጋገጡ በአካባቢው በሳርቤቶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችንና እንስሳትን በማውጣት በቃጠሎው ህይወት እንዳይጠፋ የመከላከል ስራ
እየተሰራ መሆኑን ለሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ሀ.ዩ. ኤፍ ኤም 91.5 ሬዲዮ አስተያየታቸውን የሰጡ የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የግራዋ ወረዳ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ሲራጅ አህመድ እንደሚሉት ቃጠሎው በቀበሌው ውስጥ የሚገኙ በሳር ቤቶችን ማቃጠል እንደጀመረ ህብረተሰቡ ንብረቱን ከሳር ቤቶች ውስጥ እያወጣ እንደሆነና ቤታቸው የተቃጠለባቸውንም ሰዎች ለመርዳት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት በዚሁ ግራዋ ወረዳ ሁፌ በሚባሌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተመሳሳይ ቃጠሎ ተከስቶ 50 የሳር ቤቶች ተቃጥለው እንደነበርና በወቅቱ አደጋውን ከመከላከል ባለፈ የአደጋውን መንስኤ ኃይማኖታዊ ተደርጎ እንደተወሰደ አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡ አካባቢው በጣም በማዕድናት የበለፀገ፤ መሬቱም ጠጠራማና በጣም የሚያብለጨልጭ እንዲሁም አፈሩን እሳት ሲነካው እንደ ዕጣን የመጨስና
የመንጣጣት ባህሪ እንዳለውና በጎቤሌ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝና በጣም ሞቃታማ ስለሆነ ቃጠሎው የሚነሳው ከማዕድናትና ከአየር ንብረቱ ጋር በተያያዘም ከሆነ ሳይንሳዊ ጥናት ቢደረግበት ለወደፊቱ መሰል አደጋዎችን ለመከላከል እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጥናቱን እንዲያካሂድላቸው ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ነገ እንደሚጠይቁ አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡
በግራዋ ወረዳ ሙደና ጅሩ በሊና የተከሰተውን አደጋ መንስኤውን ፖሊስ ላይ እንደሆነና በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መንስኤውን በሳይንሳዊ መንገድ በምሁራን ለማስጠናት እንደታሰበ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ ኮሚሽን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዥን ኃላፊ ኮ/ር ስዩም ደገፋ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል ሲል የሃረማያ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰብ ራዲዮ ዘግቧል ።