ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሠጠ መግለጫ ። በህዝቦች ትግል የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስ የተገኘውን ተስፋ ነፃነት እና ሠላም መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

በህዝቦች ትግል የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስ የተገኘውን ተስፋ ነፃነት እና ሠላም መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

የሚታዩ ችግሮችንም በሰከነ መንገድ የህግ የበላይነትን አስጠብቆ መፍትሄ ለመስጠት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ሰሞኑንም በምዕራብ ጐንደር ዞን አዳኝ አገር ጨንቆ ወረዳ ምስረታ በዓልን አክብረው እየተመለሱ ባሉ ወገኖች ላይ ማንነታቸው ለጊዜው ያልታወቁ ግለሰቦች ባደረሱት ጥቃት የ4 ሠዎች ህይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡ በዚህ መነሻ በተፈጠረ ግጭት በዞኑ መተማ እና ሽንፋ አካባቢዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል አጋጣሚውን በመጠቀም ሁኔታውን በማባባስ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ህዝባችን ችግሮችን በውል የመረዳት አስተውሎት ያለው በመሆኑ ችግሩ ወደ ከፋ ግጭት እና ጥፋት ሳይሄድ አካባቢው እንዲረጋጋ ማድረግ ተችሏል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፀጥታ ሀይሎች ከኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር በመሆን በአካባቢው ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመሆን መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ጥፋተኞች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ ያለውን ጥረት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በእጅጉ ያደንቃል፡፡
በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተሣትፎ በማድረግ ችግሩ እንዲፈጠር ያደረጉ ተጠርጣሪ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር እየዋሉ ይገኛሉ፡፡

ግጭቱን የህዝብ ለህዝብ በማስመሰል ከዚህ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ሙከራ ፍሬ አልባ እና ምንም መሠረታዊ መነሻ የሌለው ከንቱ ድካም መሆኑን የክልሉ መንግስት ያስታውቃል፡፡ ይህንን ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ አካላት እና የዚህ አስፈፃሚ ግለሰቦችም ትርፋቸው ኪሣራ እንደሆነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

በክልሉ በየትኛውም አካባቢ ህግን የሚፃረሩ ተግባራትን ለማስወገድ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ የሚሠሩ ሲሆን ህዝቡ ያገኘውን ሠላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በማጋለጥ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡

በቀጣይ የክልሉ ህዝብን ሠላም ለማስጠበቅ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ርብርብ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን እየገለፅን መላ የክልላችን ህዝቦችም የተገኘውን ሠላም እና ነፃነት በመጠበቅ ከመንግስት ጐን እንዲሰለፍ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡