ፓርላማው ሁለት ዕጩዎችን ለቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት አልቀበልም አለ ።

( ዮሐንስ አንበርብር )

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲያደርግ የነበረው ስብሰባ ለቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት በዕጩነት የቀረቡትን አቶ አማኑኤል አብርሃምና አቶ ሞቱማ መቃሳን አልቀበልም በማለት ያለ ውሳኔ ተበተነ፡፡

በስብሰባው በዕጩነት የቀረቡት አቶ አማኑኤል የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሆኑ ሲሆን፣ አቶ ሞቱማ ደግሞ የውጭና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰብሳቢነት እንዲመሩ ነበር የታጩት፡፡

ፓርላማው በተመሳሳይ ውሎው በፓርላማው የነበሩ 20 ቋሚ ኮሚቴዎችን ወደ አሥር ዝቅ ያደረገ ሲሆን፣ ለምን በሚል በፓርላማው አባላት ለሁለት ሰዓታት የዘለቀ ክርክርም ተደርጎበት ነበር፡፡ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን በሚኒስትር ማዕረግ ለመሰየም ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ይኼንን ማዕረግ በመተው የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀቱን አፅድቆታል፡፡

Source ፡reporter amaharic