የቋሚ ተጠሪነት (Permanent Secretary) ሹመት የተሰጣቸው አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ፣ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ፣ አምባሳደር ዶ/ር ቦጋለ ቶሎሳ፣ አምባሳደር ነገ ፀጋዬ እና አምባሳደር ደዋኖ ከድር ናቸው፡፡
ሹመት የተሰጣቸው አምባሳደር ወይንሸት በሲዊዲን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ የነበሩ ሲሆን አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ ደግሞ በኒውዮርክ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት ምክትል የሚስዮን መሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡
አምባሳደር ወይንሽት ታደሰ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሰዳር ማህሌት ኃይሉ የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የኤዥያ እና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ፣ አምባሳደር በጋለ ቶሎሳ የዳያስፖራ እና ቆንስላ ጎዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ነጋ ፀጋዬ የኃብት ማኔጅመንትና አገልግሎት ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ደግሞ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ ሆነዋል፡፡
አምባሳደር ዶ/ር ቦጋለ ቶሎሳ በኩባ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እንዲሁም ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ተመልሰውም የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው አገልግለዋል፡፡ አምባሳደር ነጋ ፀጋዬ በፈረንሳይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄነራል በመሆንም ሰርተዋል፡፡ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ደግሞ በኩባ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አምባሳደር ሆነው ቆይተዋል፡፡ ሁለቱም በተለያየ ወቅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ቋሚ ተጠሪዎች የመስሪያ ቤቱን የዕለት ተዕለት ስራ የመከታተልና ውሳኔ የማሳለፍ ሃላፊነት የሚኖራቸው ሲሆን በተለያዩ አገሮች በስፋት ይሰራበታል፡፡ የመስሪያ ቤቱን ተቋማዊ ትውስታ (Institutional Memory) ለማስቀጠልም ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በቀጣይም የዳይሬክተር ጀኔራሎች እና ሌሎች የሃላፊነት እርከኖች ድልድል ይፋ ይሆናል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስራና ሰራተኛን ለማገናኘት እና ተቋሙ ለዘመኑ የሚመጥን ቁመና እንዲኖረው የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን የሰራተኛ ድልድል አንደኛ ነው፡፡
ተቋሙ የመስሪያ ቤቱን መዋቅር የማስከታከል እና ሌሎች የሪፎርም አካል የሆኑ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
( MOFA )