ኮሚሽኑ እርዳታውን ለማድረስ ፈተና የሆነበት ጉዳይ እርዳታውን ለማቅረብ የሚያደርገው እንቅስቃሴ መሆኑ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለአዲስ ዘመን ገልተዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነር ምትኩ ገለጻ እኛ ፈተና የሆነብን ጉዳይ እርዳታውን ለማቅረብ የምናደርገው እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህም ማለት ችግሩ እርዳታ የማቅረብ ጉዳይ ሳይሆን የጸጥታው ሁኔታ ነው፡፡ በመንገዶቹ ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻላችን እርዳታውን በማጓጓዝ ወደሚያስፈልጋቸው ዜጎች ማድረስ አልቻልንም፡፡ ይህ ደግሞ ከባድ ነው፡፡ እርዳታው ሳይጠፋ ወደ ተጎጂዎች ግን ማድረስ አለመቻል ማለት ከምንም በላይ አሳዛኝ የሆነ ክስተት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እርዳታ በተገቢውና በአስፈላጊው ወቅት ለተጎጂዎች ማድረስ አልተቻለም ነበር፡፡
አሁን ግን ከጸጥታ አካላት ጋር በፈጠርነው ትስስር መሰረት እንዲሁም ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር በመገናኘት እርዳታው ለተጎጂዎች እንዲቀርብ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በቀረበልን የእርዳታ መጠን ልክ በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ እያቀረብን እንገኛለን፡፡ ምስራቅ ወለጋ ላይ የሚገኙ ተፈናቃዮች እርዳታው ሙሉ ለሙሉ ያለምንም መሰናክል ደርሷቸዋል፡፡
ኮምሽነሩ አክለው እንዳሉት ማንም ሆነ ማን የሚታገለው ወደ ስልጣን ለመምጣት ነው፡፡ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የምናገለገለውም ደግሞ ህዝብን ነው፡፡ ስለዚህ የምናገለግለው ህዝብ ከተጎዳና ከሞተ ማንን ነው የምናስተዳድረው፡፡ ልናስተዳድረው የምንፈልገው ህዝብ ሊኖር ይገባል፡፡ እየተጎዳ ግን ማስተዳደር አይታሰብምና ይህ ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ስለሆነም ሰላማዊ በሆነ አግባብ ጥያቄ ያለው አካል ያለውን መንግስታዊ አሰራር መሰረት አድርጎ ጥያቄውን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
Source ፡EPA
(ሙሉ ቃለ ምልልሱን አዲስ ዘመን ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም የወጣውን ጋዜጣ ያንብቡ )