የቱርክ ኩባንያ በትግራይ ክልል በ750 ሚሊዮን ዩሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣት ጀመረ

4 November 2018

በቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ቀጥተኛ መመርያ ተርኪሽ ሆልዲንግ ኤኤስ፣ በትግራይ ክልል በ750 ሚሊዮን ዩሮ አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡

ተርኪሽ ኢንዱስትሪያል ሆልዲንግ የኮንስትራክሽን፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዕቃዎችን የሚያመርት ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ያቀደው በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አዲጉደም ከተማ ነው፡፡

የኩባንያው ባለሥልጣናት ከአዲጉደም ከተማና አቅራቢያ ነዋሪዎች ጋር፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

ተርኪሽ ኢንዱስትሪያል ሆልዲንግ ግንባታውን ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማካሄዱን በመቀጠል፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት ሒደት ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የትግራይ ክልል ከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀብቶም ፋንታሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተርኪሽ ኢንዱስትሪያል ሆልዲንግ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ለማካሄድ 500 ሔክታር መሬት እንደሚፈልግ አሳውቋል፡፡

‹‹ኩባንያው የኢንቨስትመንት ፈቃድና የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን ሲያጠናቅቅ፣ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ቦታ ያገኛል፤›› ሲሉ አቶ ሀብቶም ተናግረዋል፡፡

ተርኪሽ ኢንዱስትሪያል ሆልዲንግ በቱርክ ከሚገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በተለይ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ የኢንዱስትሪ ምርቶች ይታወቃል፡፡

ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ በእነዚህ ዘርፎች በስፋት ለመግባት ፍላጎት እንዳለው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ሲያስረዳ፣ አቶ ሀብቶምም ይኼንኑ አረጋግጠዋል፡፡

‹‹የደቡባዊ ትግራይ አካባቢ ከፍተኛ የማዕድን ሀብት አለው፣ ለመቀሌ ከተማም ቅርብ በመሆኑ በኩባንያው ተመራጭ ሆኗል፤›› ሲሉ አቶ ሀብቶም ገልጸዋል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ትግራይ ለሚገኘው ጥንታዊው ነጋሽ መስጊድ ልዩ ፍላጎት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ የኩባንያው ኃላፊዎች አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በጥንታዊው ነጋሽ መስጊድ ጉዳይና በትግራይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከፕሬዚዳንት ኤርዶዋን መመርያ እንደተሰጣቸው መወያየታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

Source ፡ ethiopianreporter

FacebookTwitterLinkedInShare