የብስራተ ገብርኤል አደባባይን በማፍረስ በትራፊክ መብራት የመተካት ስራ ሊጀመር ነው

የብስራተ ገብርኤል አደባባይን በማፍረስ በትራፊክ መብራት የመተካት ስራ ሊጀመር ነው

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚስተዋልባቸውን አደባባዮች በማፍረስ በትራፊክ መብራት በመተካት በርካታ ስራዎችን እንዳከናወነ ይታወቃል፡፡
ይህንን ስራ በያዝነው በጀት ዓመትም በማስቀጠል በብስራተ ገብርኤል አደባባይ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመፍታት አደባባዩን በማፍረስ በትራፊክ መብራት የመተካት ስራ ቅዳሜ ጥቅምት 24 ምሽቱ 2፡00 ሰአት ይጀምራል፡፡
ከካርል አደባባይ – ጀሞ – ቆሬ እና ከመካኒሳ – 3 ቁጥር ማዞሪያ የሚመጣው ትራፊክ የሚገናኝበት የብስራተ ገብርኤል አደባባይ በአካባቢው እያደገ በመጣው ከፍተኛ መጠን ያለው የትራፊክ ፍሰት በተሳለጠ መልኩ እንዲስተናገድ አደባበዩ ፈርሶ በትራፊክ መብራት ለመተካት 3,300 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የአስፋልት ንጣፍ ስራ እና የከርቭ ስቶን ስራ የሚከናወን ሲሆን ለዚህ ስራ 3.6 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡
የብስራተ ገብርኤል አደባባይ ከጥቅምት 24 ቀን 2011ዓ.ም. ጀምሮ የማፍረስ ስራውን የሚጀምር በመሆኑ ቅዳሜ ጥቅምት 24 ምሽቱ 2፡00 ሰአት ጀምሮ እሁድ ጥቅምት 25 ሙሉ ቀን መንገዱ ለተሸከርካሪ ዝግ ስለሚሆን አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገድ በመጠቀም እንዲተባበሩ የተጠየቀ ሲሆን ሰኞ ጥቅምት 26 ጠዋት ለትራፊክ ክፍት ተደርጎ አደባባዩን አፍርሶ በትራፊክ መብራት የመተካት ስራ ሙሉ በሙሉ በአንድ ሳምስት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ሲል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል ።
ከዚህ ቀደም በአስራ ሁለት አደባባዮች ላይ የማሻሻያ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ዘጠኝ አደባባዮች ማለትም አስራ ስምንት ማዞሪያ፣ ቦሌ ሚካኤል፣ ለቡ መብራት ኃይል፣ ጀሞ ሚካኤል፣ ኢምፔሪያል፣ ጃክሮስ፣ ሳሪስ አቦ፣ ካዲስኮ እና ሳፋሪ አደባባዮች ላይ ይከሰት የነበረውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ አደባባዮችን በማፍረስ ወደ ትራፊክ መብራት የመቀየር ስራ እንዲሁም የላምበረት፣ የኪዳነ ምህረትና ዊንጌት አደባባዮች በሲሚንቶ ኮንክሪት የመልሶ ግንባታ ስራ በመከናወኑ የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ከማስቻሉም በተጨማሪ የትራፊክ አደጋ መቀነሱ ተስተውሏል፡፡
በቀጣይም ባለስልጣኑ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይባቸውን አደባባዮች በመለየት በመጠገንና አፍርሶ በትራፊክ መብራት በመቀየር የትራፊክ መጨናነቆችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎችን የሚያከናውን ይሆናል፡፡