Take a fresh look at your lifestyle.

ብሄራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች  ለተበዳሪዎች እፎይታን የሚሰጥ አዲስ መመሪያ አወጣ ።

300

ብሄራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች  የብድራቸው 20 በመቶ የረጅም ጊዜ ብድር እንዲሆን የሚያዝና ለተበዳሪዎች እፎይታን የሚሰጥ አዲስ መመሪያ አወጣ። ዋዜማ ዝግጅት ክፍል የደረሰው አዲሱ መመሪያ የግል ንግድ ባንኮች ባበደሩ ቁጥር ከብሄራዊ ባንክ የሚገዙትን የ27 በመቶ ቦንድን ሊያስቀረው ይችላልም     እየተባለ ነው።

የሀገሪቱ ንግድ ባንኮች እስከዛሬ ሲሰሩበት የነበረው የብድር ማረዘሚያ መመሪያ ሳብያና በሌሎች ምክንያቶች የተበላሸ ብድር ምጣኔያቸው በብሄራዊ ባንክ ከተቀመጠላቸው መስፈርት በላይ እየሆነ መምጣቱን ዋዜማ ራዲዮ ከሰሞኑ መዘገቧ የሚታወስ ነው ።
በዚህም ሳብያ ማእከላዊ ባንኩ አዲስ መመሪያን እስካወጣ ድረስ ባንኮች ምንም አይነት ሀራጅ እንዳያወጡ መመሪያን ማስተላለፉ ይታወሳል ።በዚህም መሰረት ብሄራዊ ባንኩ አዲሱን መመሪያ አውጥቶ ለንግድ ባንኮች ሰጥቷል ።

ግልፅ ተመንና የተራዘመ የክፍያ ጊዜ

በብሄራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን አቶ ሶሎሞን ደስታ ተፈርሞ የወጣው መመሪያ ለሀገሪቱ ንግድ ባንኮች አዳዲስ ትእዛዛት የተላለፉበት ነው ። ከዚህ ውስጥም ባልተለመደ ሁኔታ የንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ ብደርን በግልጽ ተመን እንዲሰጡ ማዘዙ ይገኝበታል ።
እስካሁን ባለው አሰራር የሀገር ውስጥ ንግድ ባንኮች አጠቃላይ ከሚሰጡት ብድር 60 በመቶው የመካከለኛና ረጅም ጊዜ እንዲሆን ቢያዝም የረጅም ጊዜ ብሎ የተመነው ቁጥር አልነበረም ። ባንኮች የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ብድር እንዲሰጡ ብቻ ነበር የሚበረታቱት ።
የአጭር ጊዜ ማለትም በአንድ አመት እንዲመለስ የሚሰጡት ብድር ደግሞ የአጠቃላይ ብድራቸው 40 በመቶ እንዲሆን ነው የሚያዘው ።
ነባሩ መመሪያም በተለይ የንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ ብድርን ለሚፈልጉት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ብድርን እንዲያቀርቡ የሚገፋፋ አልነበረም ።

ብሄራዊ ባንኩ የግል ንግድ ባንኮች ለአምራች ኢንዱስትሪው ገንዘብን እንዲያቀርቡ የሚያደርገው እያንዳንዱን ብድር ሲሰጡ 27 በመቶ ቦንድ እንዲገዙ በማድረግ ነው ።ማእከላዊ ባንኩ ደግሞ ይህን ገንዘብ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በማቅረብ ልማት ባንኩ ለአምራች ኢንዱስትሪና መሰል ዘርፎች እንዲያበድረው ነው የሚያደርገው ።

በዚህ መልኩ ከ2003 አ.ም ጀምሮ ብሄራዊ ባንክ ከግል ንግድ ባንኮች ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ ፤ ከዚህ ውስጥ አምስት አመት የሞላውን ገንዘብ ለባንኮች መልሷል ።

27 በመቶ የቦንድ ግዥው ግዴታ ሊቀር ይችላል 

አሁን ለንግድ ባንኮች የተበተነው መመሪያ እንዲሚያሳየው ደግሞ ፤ ንግድ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ውስጥ 40 በመቶው የአጭር ጊዜ ፤ 40 በመቶው ደግሞ የመካከለኛና ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ የረጅም ጊዜ ብድር እንዲሆን ታዘዋል ።ንግድ ባንኮች 20 በመቶ የረጅም ጊዜ ብድር እንዲሰጡ ከታዘዙ ባንኮች የረጅም ጊዜ ብድርን ለሚፈልጉ እንደ አምራች ኢንዱስትሪ ላሉ ዘርፎች በሰፊው በድርን እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል ።

እንዲህ ከሆነ ደግሞ ንግድ ባንኮች ባበደሩ ቁጥር ከብድሩ 27 በመቶ የሚመጣጠን ገንዘብን በማውጣት ከብሄራዊ ባንክ ቦንድን እንዲገዙ ላይገደዱ ይችላሉ ።ምክንያቱም ራሳቸው ባንኮቹ የረጅም ጊዜ ብድር ውስጥ የሚገቡ ከሆነ እንደከዚህ ቀደሙ በአጭር በአጭር ጊዜ ውስጥ ብድር እየሰጡ ቦንዱን የመግዛት አዝማሚያቸው ይቀንሳል ።

አዲሱ መመሪያ በስራ ላይ መዋሉ በቀውስ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር የሚያቀርብበት ገንዘብ ስለሚቀንስ በመንግስት በኩል አዲስ አይነት አማራጭ ሳይታሰብ እንዳልቀረ አመላካች ነው ።

በሌላ በኩል አዲሱ የብሄራዊ ባንክ መመሪያ ለተበዳሪዎች ከፍተኛ እፎይታን በሚሰጥ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን መመሪያውን ያዩ የአንድ ባንክ ከፍተኛ ሀላፊ ነግረውናል ።

ከዚህ ቀደም አንድ ተበዳሪ ብድሩን በጊዜው መክፈል ሲያቅተው ሶስት ጊዜ እንዲራዘምለት ነበር ነባሩ መመሪያ የሚያዘው ። አዲሱ መመሪያ ግን የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ተበዳሪዎች ብድራቸውን አምስት ጊዜ እንዲራዘምላቸው ፈቅዷል ። የረጅም ጊዜ ተበዳሪዎች ደግሞ ብድራቸው ስድስት ጊዜ ሊራዘምላቸው እንደሚችል መመሪያው ፈቅዷል ። መመሪያው በዚህም ሳያበቃ የብድር ማራዘሚያ ቅድመ ሁኔታዎችን  ላላ እንዲል አድርጎታል ።

የቀደመው መመሪያ አንድ ተበዳሪ ለመጀመርያ ጊዜ ብድሩ እንዲራዘምለት ከፈለገ የመጀመርያው ዙር የብድር ክፍያ እስከነ ወለዱ እንዲከፍል ፤ ሁለተኛ እንዲራዘምለት ደግሞ የብድሩን 20 በመቶ ፤ ሶስተኛ እንዲራዘምለት  የብድሩን 50 በመቶ እንዲከፍል ይገደድ ነበር ።
ይህን ገንዘብ እየከፈሉ ማራዘም ለአብዛኛዎቹ ተበዳሪዎች ከባድ ሆኖ ቆይቷል ።
መመሪያውም ለተበዳሪዎች አጅግ በጣም ከባድ በመሆኑ ምክንያት ባንኮችን ለመያዣነት የያዙትን ንብረት ሀራጅ እንዲያወጡ በብዛት የሚያደርግ ከመሆኑ ባለፈ የባንኮቹን የተበላሸ የብድር ምጣኔ ከተቀመጠው የአምሰት በመቶ ገደብ ከፍ ያደረገ ነው ።
አዲሱ መመሪያ ግን ብድርን በአንጻሩ ለአምስትና ለስድስተኛ ጊዜ ማራዘምን ከመፍቀዱም ባለፈ ፤
ብድሩን የሚያራዝመው እንደ ቀደመው ተበዳሪዎች የብድሩን አካል የሆነ ገንዘብ እየከፈሉ ሳይሆን ወለዱን ብቻ እየከፈሉ እንዲያራዝሙ ማድረጉ በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ነው ።
ይህም ተበዳሪዎችን ወደተበላሸ የብድር ሰነድ ውስጥ የማስገባት አዝማሚያን ስለሚቀንሰው የንግድ ባንኮችን የተበላሸ ብድር ከተቀጠመው መስፈርት በላይ እንዳያድግ ይረዳል ።

ዘገባው የዋዜማ ራዲዮ ነው

 

Comments are closed.