Take a fresh look at your lifestyle.

ጦር አውርድ ( በእውቀቱ ስዩም እንደፃፈው )

792

ከዘመናት በአንዱ ዘመን የሀበሻ መዲና በነበረችው አክሱም በጎረቤቶቿ በኑብያና የመን ሰላም ነገሰ ይልቁንም በአክሱም ብልጽግና ሰፈነ ሁሉም እንጀራና ወይን ጠገበ ከጥቂት አመታት በኋላ ከተመሰገኑት የአክሱም ሊቃውንት አንዱ ንጉሱ በተገኙበት ጉባኤ ልቦናዬ ያሳየኝን ልናገር አሉ ፡፡ ተፈቀደላቸው
ግርማዊ ጃንሆይ አሉ ባማረ ድምጻቸው ግርማዊ ጃንሆይ አክሱም የምትገኝበት ሁኔታ ለረጋው ህሊናየ ስጋት ፈጥሮብኛል ይሄ ስጋት ደግሞ ቀስ በቀስ ወደወገኖቼ መጋባቱ አይቀርም
ምንድን ነው የስጋትህ ምንጭ አሉ ንጉሱ ሊቁ ማብራራት ጀመሩ እንደምናየው በመንግስታችን ሰላም አለቅጥ ሰፍኗል የባሩድ መአዛ ከሸተተን ብዙ ዘመን ሆነን የሽለላ የፉከራ ዜማዎቻችን ተዘነጉ እረኞቻችንንም ስሟቸው በዜማዎቻቸውም ውስጥ የብልግና እና የፍቅር እንጂ የጉብዝናና የጀግንነት ስንኝ አይገኝም ጋሻዎቻችን በተሰቀሉበት ድር አደራባቸው ጦሮቻችን ዶልድመዋል ሀኔዎቻችን ዛጉ ነጋሪቶቻችን ዳዋ ዋጣቸው ሰላም ልማዶቻችንን እና ትፊቶቻችንን አጠፋብን ህንጻ ያለጡብ ያለ ጣርያ ህንጻ እንደማይሆን እኛም ያለነውጣችን እና ያለሽለላችን ያለድላችን እና ያለሽንፈታችን እኛ አይደለንም ግርማዊነቶ እንደሚያውቁት ሀንበሳ ከሚዳቋ ጋር ተኝቶ ማየት ለጊዜው የሚያስደስት ትእይንት ሊሆን ይችላል ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ይሰለቻል የሁሉም አይን አንበሳው ሚዳቆዋን ሲያሳድዳት እና ሰብሮ ሲገነጣጥላት ለማየት ይናፍቃል ፡፡ ጃንሆይ እርግቦቻችን በሰገነቶቻችን ላይ ሰፍረዋል የዘንባባ ዛፎች በጓሮ በቅለዋል ብለው የሚያዘናጉትን አይስሟቸው ብርቱ መንግስት ከእርግቦች ላባ ፍላጻ ያበጃል ከዘንባባዎች ዝንጣፊ የጦር ሶማያ ይሰራል ለራሳችን ብርቱዎች ነን ብለን እንጃጃላለን ካልታገሉ ሀቅምን ማወቅ አይቻልም ጎረቤቶቻችን ከፈገግታቸው ባሻገር ምን እያሴሩ እንደሆነ አናውቅም የጎረቤቶቻችን በር ተዘግቷል በዚህ ምክንያት በእልፍኞቻቸው ውስጥ ምን እየተሰራ እንደሆነ አናውቅም የጎረቤቶቻችንን ልክ አለማወቅ በቤታችን ላይ ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል ፡፡ ጃንሆይ የምንኖረው ፈተና በሌለበት ዘመን ነው ፈተና የሌለበት ዘመን የተፈጥሮን ህግ ያዛባል እስቲ ጎረምሶቻችንን እዩዋቸው እንደሴት ዳሌና ጡት ማብቀል ጀምረዋል በምትኩ ጺማቸውን ከአገጫቸው ከከንፈራቸው ጠርዝ አራግፈዋል መዳፎቻቸው ከሀር ጨርቅ ይለሰልሳሉ እግራቸውን ዘርግተው የባልቴት ተረት በመተርተር ግዜያቸውን ያጠፋሉ የደም ቀለም አያውቁም አያቶቻችን ፍላጻ የወጠሩባቸው ደጋኖች የሴት ልጆቻችን የጥጥ መንደፍያ ሆኑ ስለዚህ የምንለብሰው ሸማ በውርደት አድፏል ይህ እድፍ ከደም በቀር የሚያነጻው ምን አለ?
ታድያ ምን ይሻላል አሉ ጃንሆይ ኑብያዎችን ለምን አንወጋም አሉ ሊቁ
ኑብያዎች ምን አደረጉን ?
ሁለታችንን በሚለየን ድንበር ላይ ዋርካ ተክለዋል ፡፡
እና ቢተክሉስ ?
ዋርካዎች እየሰፉ በመጡ ቁጥር የኛን መሬት መውሰዳቸው አይቀርም ፡፡
እና ምን ይሻላል ?
እናቅምሳቸው አሉ ሊቁ እንበላቸው አሉ መኳንንት በሏቸው አሉ ንጉሱ፡፡
ሁኔታዎች ተቀያየሩ ሴቶች ቆሎ በመማስ ጭብጦ በማሰናዳት ተጠመዱ ወንዶች ኢላማ ልምምዱን አጣደፉት አሮጌ ጋሻዎች ከተሰቀሉበት ወረዱ ደጋኖች ተወለወሉ ፍላጻዎች ተሳሉ የጎበዞች አረማመድ ተለወጠ የእረኞች የፍቅር ዘፈን አንደበታቸው ላይ ሟሟ የደም ቃና ያላቸው ዜማዎች መስኩን ዱሩን ጋራውን ሞሉት የአክሱም ባንዲራ ከእንቅልፏ ተቀሰቀሰች ጥቂት ወራት አለፈ ፡፡
ከወደ ኑብያ ግድም ደብዳቤ መጣ ዛቲ ጦማር ተፈኖ ታእብ ንጉሰ አክሱም የየመን ሊቃውንት አንድ መረጃ ነገሩን እናንተ አክሱምች በኛ ላይ ሰራዊት ልታዘምቱ እንደተሰናዳችሁ ነግረውን አዝነናል ይሁን እንጂ የጠባችን ምክንያት በድንበሮቻችን ላይ የተተከሉት የዋርካ ዛፎች መሆናቸውን በማወቃችን ለሰላም የሚበጀውን አድርገናል ከዛሬ ጀምሮ ዋርካዎች እንዲቆረጡ ትእዛዝ አስተላልፈናል ይቅርታ አድርጉልን የሚታይ ማህተም ፡፡ ደብዳቤው ከደረሳቸው በኋላ ንጉሱ ሊቁን አስጠሩ ምን ይሻለናል ኑብያዎች ሳንወጋቸው ዋርካቸውን ቆረጡ እንግዲህ ምን ሰበብ እንፈጥራለን አሉ በቅሬታ
ግርማይ ሆይ አሉ ሊቁ የሰማነው ዜና በእውነቱ የሚያስቆጣ ነው እንደሚያውቁት ሰራዊት ለማደራጀት ብዙ ገንዘብ ብዙ ጉልበት ብዙ ጊዜ ፈጅተናል ጎበዞቻችንን ከሙያዎቻችው አፈናቅለን አስታጥቀናቸዋል ሴቶቻችን ቡሃቃቸውን አሟጠው ስንቅ ሰርተዋል ይህ ሁሉ ያለአንዳች ተግባር ብላሽ መሆን የለበትም ጃንሆይ አሉ በመማጸን ድምጽ
ታድያ ምን አድርግ ነው የምትለኝ ?
የዘመቻችንን እቅድ ሰልሎ ለኑብያዎች የነገራቸው የየመን መንግስት ነው ፡፡
እናስ ?
በዚህ ምክንያት የመኖች የኛን ሉአላዊነት ደፍረዋል ስለዚህ ዘመቻውን ለምን ወደ የመን ለምን አናዛውረውም ?
አማራጭ አልተገኘም በማግስቱም አዋጅ ተነገረ ጠላታችን ወደሆነው ወደ የመን አገር ዝመቱ በዝያ ህያው የሆነው ሁሉ ፍጁ ከተሞቻቸውንም ወደ ፍርስራሽ ለውጡ ፡፡
ተፈጸመ

Comments are closed.