Take a fresh look at your lifestyle.

“ቢሾ” ኢትዮጵያዊቷ ኦሮሞ ባሪያ፣ ደቡብ አፍሪቃዊቷ መምህርት ( ትርጉም – በጥላሁን ግርማ )

342

 

ሳንድራ ሮዎልድት – ሼል ዩንቨርስቲ – ኬፕታውን
ኦገስት 2011 – ቢቢሲ አፍሪካ
ትርጉም – ጥላሁን ግርማ
———————————————————————-
ኔቪል አሌክሳንደር በልጅነቱ የእናቱ እናት የሆኑትን ሴት አያቱን ለመጎብኘት ሲመላለስ ሴት አያቱ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ፖርት ኤሊዛቤት የመጡበት አስገራሚ ታሪክ መኖሩን ጠርጥሮ አያውቅም ነበር።

“ቢሾ” እ.ኤ.አ. በ1888 በብሪቲሽ የጦር መርከብ የመን የባህር ጠረፍ ላይ ነፃ ወጥተው ወደ ደቡብ አፍሪካዋ የጠረፍ ከተማ ተወስደው በሚሲዮናውያን እጅ እንዲያድጉ ከተደረጉ ባሪያዎች መሃከል አንዷ ነበረች።

“በህይወት ሳለች ማናችንም በማንረዳው ቋንቋ ከእራሷ ጋር ብቻ በምታወራው ነገር በጣም እንገረም ነበር።” ይላል የ74 ዓመቱ አሌክሳንደር።

ይሁን እንጂ ቢሾ ታወራ የነበረው አፏን በፈታችበትና እያረጀች ስትመጣ እንደገና ልታወራበት በመረጠችው የኢትዮጵያው አፋን ኦሮሞ ቋንቋ ነበር።

ሚስተር አሌክሳንደር በ1960 የፖለቲከኛ እስረኛ በመሆን በሮበን ደሴት ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የታሰረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በደቡብ አፍሪቃ ከሚገኙ ጥቂት ምሁራን መሃከል አንዱ ነው።

አስታውሳለሁ ልጅ ሆነን ትንንሽ ወንድሞቼ እናታችን ዲምቢቲን “አያታችን ምንድነው የምታወራው? ስለ ምንድነው የምታወራው? ምን ሆና ነው?” በማለት ሲጠይቋት እናታችን “ስለአያታችሁ አታስቡ ከአምላኳ ጋር እያወራች ነው።” በማለት ትመልስላቸው ነበር።

ሚስተር አሌክሳንደር እድሜው አስራዎቹ መጨረሻ ላይ ሳለ እናቱ ስለኢትዮጵያ የዘር ግንዱ ብትነግረውም ስለታሪኩ በዝርዝር እንደማታውቅ ያወቀው እድሜው ሃምሳዎቹ ውስጥ እያለ ስለታሪኩ በደንብ ካወቀ በኋላ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ወደ ደቡብ አፍሪቃ መጥተው ነፃ የወጡት ኢትዮጵያውያን ቃለመጠይቅ ተደርጎላቸው እንደነበረ መረጃ ያገኘው።

ታሪኩ የሚጀምረው እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 1888 የብሪቲሽ ኮማንደር ቻርለስ ኢ ጊሰንግ “ኤች ኤም ኤስ ኦስፕሬይ” በተባለችው የብሪቲሽ የጦር መርከብ ሶስት ኢትዮጵያውያን ባሪያዎችን ጭነው ወደ ሳዑድ አረቢያዋ ጂዳ ወደብ ሲገሰግሱ የነበሩ ጀልባዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ ነው።

#በእፍኝ #በቆሎ #የተሸጠች

የኮማንደር ጊሲንግ ተልዕኮ ታላቋ ብሪታኒያ እ.ኤ.አ. እስከ 1807 ትደግፈው የነበረውን የባሪያ ንግድ በኋላ ላይ ከቅኝ ግዛቶቿም ጭምር ልታጠፋ የምታደርገው ዘመቻ አካል ነበር። ኮማንደሩ ነፃ ያወጣቸው 204ቱም ኦሮሞዎች ሲሆኑ አብዛኞቹ ህፃናት ነበሩ።

ቢሾ ጃርሳም በጀልባዋ ውስጥ ከነበሩ 183 ህፃናት መሃከል አንዷ ነበረች። ቢሾና ወንድሞቿ እ.ኤ.አ. በመላ ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ወረርሽኝ ምክንያት እናትና አባታቸውን አጥተው የአባታቸው ባሪያ በነበረ ሰው እጅ ይኖሩ ነበር።

ይሁን እንጂ በወቅቱ እየባሰ በመጣው የረሃብ ችግር ምክንያት ቢሾ በጥቂት እፍኝ በቆሎ ለባሪያ ፈንጋዮች ተሸጠች። ከስድስት ሳምንታት የየብስ ጉዞ በኋላም ቀይ ባህር ደርሳ ወደ ጅዳ በመጓዝ ላይ ሳሉ በብሪቲሿ መርከብ “ኤች ኤም ኤስ ኦስፕሬይ” ከተያዙት ሶስት ጀልባዎች በአንዱ ላይ ተጫነች።

ስለብሪቲሾች በመጀመሪያ የምታስታውሰው ወደ ባህረተኞቹና ወደ ጀልባዎቹ የተኮሷቸውን አውቶማቲክ መሳሪያዎች ድምፅ ተከትሎ በጀልባዋ የዕቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ ከሌሎች የኦሮሞ ህፃናት ጋር በፍርሃት ተቃቅፈው መቀመጣቸውን ነው። የፍርሃታቸው ምክንያት ደግሞ በአረብ የባሪያ ነጋዴዎች “ብሪቲሾቹ ከያዟችሁ ይበሏችኋል” ተብለው ስለነበረ ነው።

ይሁን እንጂ ኮማንደር ጊሲንግ ኦሮሞዎቹን ልጆች ወደ ኤደን ወስዷቸው ስለባሪያዎቹ ልጆች እጣ ፈንታ የብሪቲሽ ባለስልጣናት እንዲወስኑ አደረገ። በዚሁ መሠረት ሃይማኖታቸው ሙስሊም የሆኑ ህፃናት ለየመናውያን በማደጎ ተሰጡ። የተቀሩት ህፃናት “ሜሽን ኦፍ ፍሪ ቸርች ኦፍ ስኮትላንድ” የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ እንዲቀመጡ ተደረገ። ይሁን እንጂ በአስቸጋሪው የኤደን የአየር ንብረት ምክንያት 11ዱ ልጆች ሞቱ።

ሚሲዮናውያኑ ችግሩን ለመፍታት ለልጆቹ የሚሆን ተለዋጭ የመኖሪያ ስፍራ በመፈለግ በቤተክርስቲየኗ በደቡብ አፍሪቃ ኢስተርን ኬፕ ላቭዴል ተቋም ውስጥ በሌላኛው የአፍሪካ አህጉር ክፍል እንዲሰፍሩ ወሰኑ።

ቢሾና ሌሎቹ ህፃናት እ.ኤ.አ. በ1890 ላቭዴል ደረሱ። ሚሲዮናውያኑም የእያንዳንዱን የቀድሞ ባሪያ ዝርዝር ታሪክ በማህደር አኖሩ፣ አስተምረዋቸውም በክርስትና እምነት አጠመቋቸው።

#የማንዴላ #ፍቅር

ህይወት በደቡብ አፍሪቃም ከባድ ነበረች። በ1903 ደቡብ አፍሪቃ ከደረሱት ልጆች ውስጥ 18ቱ ህይወታቸው አለፈ። በእዛው ዓመት የላቭዴል ባለስልጣናት በህይወት የተረፉትን ሰዎች ወደ ሃገራቸው ኢትዮጵያ መመለስ ይፈልጉ እንደሆነ ጠየቋቸው። የተወሰኑት ወደ ሸጠቻቸው ሃገራቸው ለመመለስ ወሰኑ። ይሁን እንጂ ከተንዛዛ ሂደት በኋላ የአፄ ምኒሊክ ጀርመናውያን አማካሪዎች በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው 17ቱ ሰዎች በ1909 ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።

የተቀሩት እዛው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ትዳር መስርተው ወይም ስራ ይዘው ስለነበር እዛው መቆየትን ምርጫቸው አደረጉ። ቢሾም በቤት ሰራተኝነት ብትሰለጥንም የተለየ ተሰጥኦ እንዳላት በማሳየቷ በመምህርነት ለመሰልጠን ዕድል ካገኙ ሁለት የኦሮሞ ልጃገረዶች አንዷ ሆነች። በ1902 ላቭሌድን ለቅቃ በ”ክረዶክ” ትምህርት ቤት በመምህርነት ተቀጠረች። በ1911 ፍሬድሪክ ስኪፐርስ የተባለ የቤተክርስቲያን ካህን አገባች።

ፍሬድሪክ እና ቢሾ ጃርሳ “ዲምቢቲ” የተባለች ልጅ ወለዱ፣ ዲምቢቲም ዴቪድ አሌክሳንደር የተባለ አናፂ አግብታ ከልጆቻቸው መሃከል አንዱ የሆነውን “ኔቭል አሌክሳንደር”ን በ1936 ወለደች።

አሌክሳንደር በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ የታወቀ የፓለቲካ አቀንቃኝ በመሆን እድሜው በአጭር ቢቀጭም ” ናሽናል ሊብሬሽን ፍሮንት” የተባለ ግንባር መስርተ። በዚሁ ምክንያት ከ1964 እስከ 1974 በሮበን ደሴት ለእስር ዓመታት ታሰረ።

አብረው ከታሰሩት ጓደኞቹ መሃከል ኔልሰን ማንዴላ እና ዋልተር ሲሱሉ ግማሽ ኢትዮጵያዊ በሆነው የዘር ግንዱ እጅግ ይማረኩ ነበር። ይሁን እንጂ በእዛ ሰዓት አያቱ በባርነት ተይዛ መምጣቷን አያውቅ ስለነበር በወቅቱ እነርሱ ከሚያደርጉት የጭቆና ትግል ጋር አገናኝተውት አያውቁም ነበር።

አያቱ ወደ ደቡብ አፍሪቃ እንዴት መጥታ ህይወቷን እንዳሳለፈች ሲያውቅ ምን እንደተሰማው ሲጠየቅ:-

“የአፍሪካዊነት መንፈሴን መሰረታዊ በሆነ መንገድ አጠንክሮልኛል።” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

በአፓርታይድ ዘመን ቤተሰቦቹ ከአፍሪካውያን ጥቁር ይልቅ “ክልስ/Colured” በሚል የዘር ክፍል ተመድበው ነበር። ሁኔታውን “ሁሌም ይሄንን ስያሜ ስንቃወም ኖረናል።” በማለት ገልፆታል።

የኢትዮጵያዊ የዘር ሃረግ እንዳለው ማወቁ በየቦታው ሲጓዝ ሰዎች ለምን አትዮጵያዊ እንደምመስላቸው እንዳውቅ አድርጎኛልም ብሏል።

በእርሱና በአያቱ ህይወት መካከል ሊያሰምረው የሚቸው ጠንካራ የትስስር ገመድ ቢኖር የመማር ሚና መሆኑንም ገልጿል።

“የአያቴ እውነተኛ ነፃ አውጪ የብሪቲሽ የጦር መርከቦች ሳይሆኑ ደቡብ አፍሪቃ ከመጣች በኋላ የተማረችው ትምህርት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ በሮበን ደሴት ሳለን ቦታውን ወደ ዩንቨርሲቲነት ቀይረነው ሁሉም እስረኛ ማንብብና መፃፍ ተምሮ ለወደፊት ህይወቱ እንዲዘጋጅ ተደርጓል።” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
———————————————————————
ፀሃፊዋ በፅሁፏ ውስጥ አፄ ምኒሊክ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያደርጉት መስፋፋት የሚጠቅማቸውን የጦር መሳሪያ ለመግዣነት የሚሆን ግብር ከባሪያ ፈንጋዮችና ነጋዴዎች ይሰበስቡ ነበር በማለት ወቅሳቸዋለች።

Comments are closed.