ከስምንት መቶ ዓመታት በላይ እድሜ የስቆጠሩት የቅዱስ ላልይበላ አብያተ መቃድስ በተደቀነባቸው የመፍረስ አደጋ ምክንያት ከፍ ያለ ሀገራዊ የመወያያ አጀንዳ ሆነዋል፡፡ አንድን ችግር ለመፍታት ‹‹የችግሩን ዓይነት›› እና ‹‹የችግሩን መጠን›› አስቀድሞ መረዳት ቀዳሚው ሊሆን ይገባል፡፡ በዚሁ መርህ የቅዱስ ላልይበላ አብያተ መቃድስ ዋንኛ ችግራቸው እርጅና ይዞት የመጣው የመዳከም (Deterioration) አደጋ ሲሆን የችግሩ መጠን ደግሞ ሊጠገኑ ወይንም ሊተኩ በማይችሉበት ሁኔታ ጉዳት ሊደርስባቸው መቻሉን ልብ ይሏል፡፡
በርካታ ባለሙያ የሆኑ አርኪቴክቶች፣ መሀንዲሶች እና ሥራ ተቋራጮች (Contractors) በበጎ ፈቃድ ሙያዊ እገዛ ለማድረግ የመሰባሰብ ሙከራዎች እያደረጉ ነው፡፡ ለእኔም በግሌ ወዳጆቼ የ ”እንሰባሰብ” ጥያቄ አቅርበውልኛል፡፡ እንደመፍትሔም በአፋጣኝ አብያተ ክርስቲያናቱ አናት (rooftop) ላይ የተዋቀሩትን የብረት መጠለያ ለማንሳት ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ቅንነታቸውን እና ተቆርቋሪነታቸውን እያደነቅሁ አካሄዱ ግን የቅርሱን የጉዳት ዓይት (type) እና መጠን (magnitude) እንዲሁም የቅርስ ጥገና መርህን (Principles of Conservatio)ግምት ውስጥ ያስገባ ስላልመሰለኝ ይህችን አጭር ማስታወሻ ለመካፈል ወደድኩ፡፡ እንደ አንድ ኮንሰርቬሽን ላይ እንደሠለጠነ አርኪቴክት (Conservator) ሦስት ጉዳዮች ላይ አተኩሬ ሃሳቤን ላጋራ!
1) ጉዳይ አንድ፤
መጠለያው (Shade) በጥድፊያ ይነሳ?
መጠለያውን ለማንሳት ውሳኔ ላይ ከመድረሳችን በፊት ማስተዋል ያለብን ጉዳይ ሕንጻዎቹ ላለፉት ዐርባ ዓመታት ያህል በጥላ ሥር መቆየታቸውን ነው፡፡ (ይህ መጠለያ በዩኔስኮ ከመሠራቱ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ከእንጨት እና ከቆርቆሮ የተሠራ መጠለያ ነበረው) ለረጅም ዓመታት የዝናብ ጠብታ እና ቀጥተኛ የጸሐይ ብሃን ሳያገኛቸው ተሸፍነው የቆዩትን ዐለቶች መጠለያቸውን አንስቶ በአንድ ጊዜ ላልተለማመዱት የአየር ጠባይ ማጋለጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ልክ ቤት ውስጥ ያደገን ተክል ውጪ አውጥቶ ጠራራ ጸሐይ ላይ እንደመትከል ዓይነት !
የጸሐዩ ብርሃን እና የውሃው ስርገት የአለቶቹን መበስበስ እና መፈረካከስ ከማባባሱም በላይ ተቀጽላዎች እና ሻጋታዎች በፍጥነት በአለቱ ስንጥቆች ውስጥ እንዲያድጉ እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሥራቸውን በመስደድ የንቃቃቶቹን ብዛት እና ስፋት ያባብሰዋል:: ስለዚህ መጠለያዎቹን ከማንሳታችን በፊት የሚቀድም ሥራ መኖሩን የዘነጋ ግርግር በመጀመሪያ ረገብ ይበል:: ይህን የመሰለ መተኪያ የሌለው እጅግ ውድ ቅርስ በዘመቻ ሳይሆን በዕውቀት እና በጥናት በሚመራ ጥንቁቅ አካሄድ ሊጠገን ይገባል::
በነገራችን ላይ የመጠለያውን ተሸካሚ ብረት ለማንሳት (ፈቃድ ሲገኝ) የሀገር ውስጥ ሕንጻ ተቋራጮች በቀላሉ ሊያነሱት የሚችሉት ተራ የብረት ፍርግርግ እንጂ “ፈረንጅ ካልመጣ እና በዶላር ካልተከፈለ የማይነካ” ውስብስብ የሕዋ መንኩራኩር ግንባታ ዓይነት ሥራ አድርጎ አጋንኖ መነገሩም ተገቢ አይደለም፡፡
2) ጉዳይ ሁለት፤
ታዲያ ምን ይደረግ?
መጠለያዎችን ከማንሳታችን በፊት በትንሽ ወጪ (ለምሳሌ እስካሁን ከተመደበው ብር ባነሰ) የጥገና ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ በተለይ የአብያተ መቅደሶቹ አናት (rooftop) ለውጪያዊ የአየር ጠባይ ከመጋለጣቸው በፊት የሚከተሉት ተግባራት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊከወኑ ይገባል እላለሁ::
ሀ) የአቧራ ቅንጣቶችን ማጽዳት
ለ) ሻጋታዎችን እና እጽዋትን ማጥፋት
ሐ) የሚታዪትን እና የማይታዩ ነፍሳትን ማጽዳት
መ) የዐለቶቹን ንቃቃት በሀገራዊ ኖራ (Indigenous lime) መሙላት
ሠ) መጠነኛ ውሃ በማርከፍከፍ አለቱን በጥቂት በጥቂቱ ውሃን ማለማመድ ያስፈልጋል፡፡
3) ጉዳይ ሦስት፤
ማን ነው የሚጠግነው?
ምንም ዓይነት የጥገና ሥራ ከመሥራታችን በፊት ይህንኑ ሥራ ለማከናወን ሥልጣን ያለውን ዐለም አቀፍ አካል (UNESCO) ማማከር እና ይሁንታ ማግኘት ይጠይቃል፡፡ መዘንጋት የሌለብን እውነት ከአሁን በኋላ ቅርሶቹ የኢትዮጵውያን ብቻ ሳይሆኑ በምድር ላይ ያሉ የሰው ልጆች ሁሉ ሀብት ሆነው በዩኔስኮ የተመዘገቡ እደመሆናቸው እንኳንስ ቅርሶቹን ለጥገና መነካካት ይቅርና በአከባቢያቸው ምንም ዓይነት ግንባታ ለማካሄድ መሞከር ቅርሶቹን ከዓለም የቅርስ መዝገብ ሊያሰርዛቸው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገሪቱ ገጽታ፣ ለቅርሶቹ ዘላቂ ጥበቃ እና ክብካቤ እንዲሁም ለቱሪዝሙ ከፍ ያለ ጉዳት ያስከትላል፡፡ እንደእኔ ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በቅርስ ጥናት እና ጥበቃ የሰለጠኑ አርኪቴክቶች፣ የጥንታዊ መዋቅር መሃንዲሶች፣ ጂኦሎጂስቶች፣ የታሪክ ባለሙያዎች ወዘተ የተሰባሰቡበት አንድ ሀገራዊ የባለሙዎች ኅብረት ቢመሠረት ሙያዊ የሆነ የውትወታ (lobbying) ሥራም ሆነ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ውይይቶችን በማድረግ ሀገራዊ ግንዛቤን ለማሳደግ እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የሚረዳ ይመስለኛል፡፡
[የቅርሱ ወዳጆች መልእክቱን ለሌሎች በማካፈል ሙያዊ ውይይት እንዲደረግበት እናግዝ – Share ]
ዮሃንስ መኮንን ( አርኪቴክት )
Comments are closed.