Take a fresh look at your lifestyle.

የጉምሩክ ኮሚሽን በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ ስራ ይገባል

213

የጉምሩክ ኮሚሽን በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ ስራ ይገባል

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን በሁለት ሳምንት ውስጥ ተቋቁሞ ወደ ስራ እንደሚገባ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ መንግስት ለሚያከናውናቸው ስራዎች የሚያስፈልገውና ራሱ መንግስት በግብር መልክ በሚሰበስበው ገንዘብ መካከል አለመጣጠን አሁንም ይታያል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዛሬ ሁለት ሳምንት አካባቢ ባጸደቀው የአስፈጻሚ አካል ስልጣንና ተግባርን የሚወስነው አዋጅ ውስጥም፥ የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አሁን ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር አድጎ የጉምሩክ ስራውም በሚኒስቴሩ ስር እየተመራ የጉምሩክ ኮሚሽን እንዲሆን የሚለው ይገኝበታል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉትም፥ የሚኒስቴሩ የቀጣይ ሁለት ሳምንታት ቀዳሚ ተግባርም ይህንኑ ኮሚሽን ማቋቋም ነው።

አሁን ላይ የጉምሩክ ኮሚሽኑን ስልጣንና ተግባር የሚወስነው ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን ያነሱት ሚኒስትሯ፥ ረቂቅ ደንቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ አመራር ይመደብለታል ብለዋል።

የሀገሪቱ የገቢ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻሎች የሚታይበት ቢሆንም ከብዙ ኢኮኖሚያዊ መለኪያዎች አንጻር ግን ገና ብዙ የሚጠበቅበት ነው።

ለአብነትም ሀገራት የበጀት ጉድለታቸው ከአጠቃላይ አመታዊ ምርታቸው ከሶስት በመቶ እንዳይበልጥ ይፈለጋል፤ ይህንን መስፈርት ጤናማ በሆነ መልኩ ማሟላት የሚቻለው ግን ተገቢውን ግብር በመሰብሰብ ነው።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ የበጀት ጉድለት ከቅርብ አመታት ወዲህ የተቀመጠውን አለም አቀፍ መስፈርት አልፏል።

በዚህ አመት የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በጋራ ስራቸውን ሲጀምሩ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፥ የመንግስትን የበጀት ጉድለት ችግር የማስተካከሉ ስራ ትኩረት ይደረግበታል የሚል ንግግር አድርገዋል።

ኢህአዴግ ባደረገው ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤም በ2009 ዓ.ም የሀገሪቱ የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ አመታዊ ምርት አንጻር ያለው ከአለም አቀፍ መስፈርቶች ሶስት በመቶ አልፎ 3 ነጥብ 3 በመቶ መሆኑን ገምግሟል፤ ይህም በብር ሲተመን ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ነው።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች እንዳሉትም በቀጣዮቹ ጊዜያት የሰው ሀይል ጥንካሬ ላይም በመስራት የመንግስትን ወጪና ገቢን ማመጣጠን ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በሌላም በኩል የሀገሪቱ የግብር ገቢ ከአጠቃላይ አመታዊ ምርት አንጻር ያለው ድርሻ 15 በመቶ እንዲሆን ይፈለጋል።

የኢትዮጵያ የግብር ገቢ ከአመታዊ ምርቷ አንጻር በብዙ ስራ 12 በመቶን ካለፈ በኋላ ከጥቂት አመታት ወዲህ ወደ 11 በመቶ ቤት ዝቅ ብሏል፤ ከግብር ማጭበርበርና ከህግ አለማክበር ጀምሮ የዚህ መነሻዎች ብዙ ናቸው።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች ከግብር አንጻር ያሉ አለም አቀፍ መለኪያዎችን ለማሟላትም የተቀመጡ ማሻሻያዎች ላይ ለመስራት ትኩረት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

ከሂሳብ መመዝገቢያ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ተደጋጋሚ ችግሮች፣ የተገልጋዮች እርካታና መሰል ስራዎች ላይ እንደሚተኮርም አንስተዋል።

ለዚህም ሲባል ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ይኖራሉም ነው ያሉት።

ለሚኒስቴሩ በቤት ስራ መልክ በተሰጠው የመቶ ቀናት ስራ መሰረትም በመጨረሻዎቹ ቀናት ፈጣን ለውጥን በማምጣት ገቢ ላይ ለውጥ እንዲታይ ይሰራል ብለዋል ሚኒስትሯ።

 

 

Comments are closed.