Take a fresh look at your lifestyle.

የመከላከያ ሠራዊት ግጭት የተቀሰቀሰባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢዎች ተሰማራ ።

467

ለውጡን ለማደናቀፍና ኦሮሚያን የጦርነት ዓውድማ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን ኦዴፓ ገለጸ

ውጫዊ ምክንያት ከመፈለግ ይልቅ የኦሮሞ ሕዝብን ደኅንነት ክልሉ እንዲያስከበር ኦነግ አሳሰበ

ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ውጥረትና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን፣ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው መሰማራቱ ታወቀ።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ኃላፊዎች ከሐሙስ ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. አመሻሽ ጀምሮ ከምዕራብ ወለጋ ዞን ጋር በሚዋሰኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖች የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ፣ በርካታ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሰማራት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን በምዕራብ ወለጋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ላለፉት ሦስት ወራት ግጭትና ውጥረት መኖሩ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት  ካሚሺና ያሶ በሚባሉ ዞኖች የኦሮሞ ተወላጆችን በማጥቃት የመግደል ዘመቻ ባልታወቁ ታጣቂዎች መካሄዱ ተገልጿል፡፡ ረቡዕ ኅዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ተመሳሳይ ታጣቂዎች በአካባቢው ነዋሪዎችና በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ላይ በፈጸሙት ጥቃት፣ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፋ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ቁጣ ቀስቅሷል።

ከዚህ ቀደም ብሎም በምዕራብ ወለጋ ማኅበረሰብ ዘንድ ታዋቂ የሆኑ አቶ ስሜ የተባሉ ባለሀብት ተገድለው መገኘታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህና በሰሞኑ ግድያዎች ከ40 በላይ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ ጥቃቱ የምዕራብ ወለጋ ነዋሪዎችን ቁጣ ቀስቅሶ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሐሙስ ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ አደባባይ በመውጣት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ደኅንነታቸውን እያስከበረ እንዳልሆነ የሚገልጹ ተቃውሞዎችን አሰምተዋል።

ይኼንንም ተከትሎ ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) አስቸኳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ የስብሰባው በሊቀመንበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰብሳቢነት ተካሄዷል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በምዕራብና በምሥራቅ ኦሮሚያ የሚስተዋለውን ግጭትና አለመረጋጋት የተነጋገረበት ሲሆን፣ ስብሰባ መጠናቀቅን ተከትሎም መግለጫ አውጥቷል።

የመግለጫው ይዘት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በኦሮሞዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መከፈቱ ምክንያት እንዳለው፣ ይኸውም ለበርካታ ዓመታት በዝርፊያና በሰብዓዊ መብት ረገጣ ላይ ተሰማርተው በነበሩትን ወደ ሕግ ማቅረብ መጀመሩንና አገሪቱ የተያያዘችውን የለውጥና የነፃነት ጉዞ ለማደናቀፍ በሕግ መጠየቃቸው እንደማይቀር የተገነዘቡ፣ በእጅ አዙር የጀመሩት የተደራጀ ሴራ መሆኑን ገልጿል።

‹‹የዚህ የተደራጀ ወንጀል ዓላማም በጥቅሉ ሲታይ የኦሮሞ ልጆችን ደም በማፍሰስ ኦሮሚያን የጦር አውድማ በማድረግና አንድነታችንን በማፍረስ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር አድርገው የሕዝብን ሀብት ለመዝረፍ፣ እንዲሁም ሕዝቡ ወደ ነፃነት የሚያደርገው ጉዞ እንዲደናቀፍ በማድረግ ለሌብነት፣ ለዝርፊያና ለባርነት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፤›› ሲል የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫው ያትታል።

‹‹ዕርምጃችን በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ ባርነትንና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን፣ እንዲሁም የተደራጀ ሌብነትን ከሥሩ ነቅሎ መጣልና በዜጎች ላይ አሰቃቂ ተግባራት ሲፈጸም የነበረ እጅ እንዲሰበሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ለጠፋው ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆን በእጃቸው ካቴና በማስገባት ሕግ ፊት ማቆም ጀምረናል፤›› ሲልም አክሏል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ይኼንን ሴራ ተገንዝቦ ቀዳዳ ባለመክፈት ከክልሉ መንግሥት ጋር በመቆም ብልህ መሆን እንዳለበት አሳስቧል።

‹‹ምንም ያህል ችግር ውስጥ ብንሆንና በተለያየ መንገድ ቀዳዳ በመክፈት ጥቃት እየፈጸሙ ሊያዘናጉን ቢሞክሩም፣ የሕዝቡን ፍላጎትና ጥቅም ለማረጋገጥ ለመስዋዕትነት የተዘጋጀን በመሆኑ ለአፍታም አንዘናጋም፤›› የሚለው የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ‹‹በሕዝባችን ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላትንም የገቡበት ጉድጓድ በመግባት ለሕግ በማቅረብ ተመልሰው ጉዳት ማድረስ እንዳይችሉ እንሰብራቸዋለን፤›› በማለት አቋሙን ገልጿል።

ይሁን እንጂ ተደራጅቶ በእጅ አዙር ጥቃት እየሰነዘረ ያለው ወገንን በግልጽ አላስታወቀም። ከሰሞኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሰላም በሚኖሩ ኦሮሞዎች ላይ፣ በሶማሌ ክልል ወሰን አካባቢ በሞያሌ፣ በጭናክሰንና በባቢሌ ወረዳ በሚኖሩ ሰላማዊ ሕዝቦች ላይ አሰቃቂ የሆነ ግድያና ማፈናቀል መፈጸሙን አስታውቋል፡፡

በአካባቢው ያፈነገጡ የኦነግ ኃይሎች እንቅስቃሴ ቢገለጽም፣ ኦነግ ስለዚህ ኃይል መኖር ያመነውም ያስተባበለውም ነገር የለም።

የሰሞኑ ግጭት ከመድረሱ ቀደም ባሉ ቀናት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ተገናኝተው፣ በክልሉ የሰላምና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተባብረው ለመሥራት መግባባታቸው ተገልጾ ነበር።

ሰሞኑን የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ኦነግ ባወጣው መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ኦሮሚያ በኩል እየደረሰ ያለው ጥቃት በጉሙዝ ሕዝብ ስም እንዲታጠቁ በተደረጉት ኃይሎች እንደሆነ፣ በአካባቢው በሚገኙት ኦሮሞዎች ላይ እየተካሄደ ያለው የግድያ ዘመቻ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክቷል።

እየተፈጸመ ላለው ጥቃት መንግሥት እንደ ችግር እያቀረበ የሚገኘው ኮንትሮባንዲስቶች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችና በሌሎች ስሞች የተሰየሙትን መሆኑን የሚገልጸው የኦነግ መግለጫ፣ እስካሁን ግን የችግር ምንጭ ናቸው የተባሉትን ለሕግ በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት በቂ ዕርምጃ አልወሰደም በማለት ተችቷል።

የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ የሚጠቅሰው መግለጫው፣ ‹‹በተጠያቂነት መንፈስና ባለን ራስን የመከላከል መብት ተጠቅመን፣ እንደ ብሔር እየተፈጸመብን ያለውን ግድያና ማንኛውንም ችግር መከላከል የሕዝባችን መብትና ግዴታ መሆኑን እናሳስበለን፤›› ብሏል።

( ዮሃንስ አንበርብር ሪፖርተር  )

Comments are closed.