Take a fresh look at your lifestyle.

ዕጣ ፈንታዬ ባንተ መዳፍ ውስጥ ካለች ከመዳፍህ ፈልቅቄ አወጣለሁ ብዬው ወጣሁ፡፡ በዚህ ጊዜ እቤቴ ገብቼ ተጠቅልዬ ተኛሁ፡፡ ( አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ )

1,024

አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ-  በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል

አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ናቸው፡፡በስልጣን ላይ በቆዩባቸው ዘመናት በተለይም በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት  ያጋጠማቸውን የሥራ ላይ ችግሮች፣የታዘቡትንና የታገሉትን የሌብነት ሂደት እና በሌሎችም  ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርገናል።

አዲስ ዘመን፤ አምባሳደር ሱሌይማን ማን ናቸው ?

አምባሳደር ሱሌይማን፤ ውልደቴና ዕድገቴ በምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ ነው፡፡ ከደሀ አርሶ አደር የተገኘሁ ልጅ ነኝ፡፡ አካባቢው በወቅቱ የትምህርት ዕድል ያገኘ አልነበረም፡፡ እኔ ለትምህርት በደረስኩበት ወቅት የስውዲሽ ሚሽን በመንደሬ መሰረተ ትምህርት ይከፍታል፡፡ በዛን ጊዜም የሰባት ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡ ከብት ማገዱን ትቼ በዕድሉ ለመጠቀም  ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡

ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ጥያቸው የሄድኳቸው ከብቶችም የተሰጣ  እህል በልተው፣ ማሳ ገብተው ጥፋት በማድረሳቸውም ለቤተሰቤ አቤቱታ ቀረበ፡፡ በዚህ  ምክንያትም ከቤተሰቤ ጋር አጋጨኝ፡፡  እኔም በትምህርት ቤቱ የተመደበውን አዲሱን አስተማሪያችንን በአማላጅነት ይዤ ቤተሰቤ ጋር ሄድኩኝ፡፡ መምህሬም ከቤተሰቤ ጋር አስማማኝ፡፡ በትምህርቴ እንድቀጥልም መንገድ ጠረገልኝ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ትምህርቴን አላቋረጥኩም፡፡

እስከ ስድስተኛ ክፍል ስዊድሽ ሚሽን፣ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም በአቅራቢያ በሚገኝ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማርኩኝ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ወደ አሰላ በመጓዝ እስከ 12ኛ ክፍል አጠናቀቅኩ፡፡ በመቀጠልም ወደ ውትድርና ገባሁ፡፡ በመጀመሪያ በስፔሻል ፎርስ ተቀጥሬ ፍቼ ከተማ ስልጠና ላይ እያለሁ በካዴትነት ተመለመልኩ፡፡ በ1970 ዓ.ም በጦር ትምህርት ቤት እያለሁ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ መጥቶ ተፈትኜ ጥሩ ውጤት ባገኝም በዛን ጊዜ አልገፋሁበትም፡፡ ወደ ትምህርት ዓለም የተመለስኩት በ1988 ዓ.ም ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወደ ትምህርት ዓለም ከተመለሱ በኋላ የነበሩበት ቆይታስ?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- በመጀመሪያ የቀድሞው ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በማታው ክፍለ ጊዜ ገብቼ በውጭ ቋንቋዎች ስነ ጽሁፍ የመምህርነት ስልጠና ነበር የማጠናው፡፡ አንድ ዓመት እንደተማርኩ በቀጣዩ ዓመት ሲቪል ሰርቪስ ይባል በነበረው ኮሌጅ ዕድል አገኘሁ፡፡ ኮሌጁ የመንግስት ሠራተኞች እንዲሰለጥኑበት የተከፈተ ነበር፡፡ እዚህ ለመግባት አመለከትኩ፡፡ ግን በወቅቱ እሰራበት የነበረው  ሬዲዮ ፋና ዕድሉን ከለከለኝ፡፡ የተቋሙ አመራር ኮሚቴም በወቅቱ እንዳልማር ወስኖብኛል፡፡ ዕድሉን ያገኙት ሌሎቹ ሰዎች የመግቢያ ፈተናውን እንዲያልፉ ወደ ሦስት ወራት ያህል ለዝግጅት ስልጠና ይወስዱ ነበር፡፡ እኔ ከስልጠና ቀረሁ፡፡

የሬዲዮ ፋና ሥራ አስኪያጅ ጋር ቀርቤ ዕድሉ እንዲፈቀድልኝ ተማጸንኩ፡፡ የተመለመሉት ስልጠና መጀመራቸውንና ጊዜው ያለፈ መሆኑን ገለጾልኝ፡፡ ‹‹መግቢያ ፈተናውን ማለፍ አትችልም›› አለኝ፡፡ የኦሮሚኛ ክፍል የሬዲዮ ፕሮግራም ኃላፊ ስለነበርኩና የሚተካኝ ሰው ባለመኖሩም ‹‹አልለቅህም አትማርም›› አለኝ፡፡ ‹‹ይህ ከሆነ እንድማር የማይፈልገኝ ድርጅት ውስጥ አልቀጥልም፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ በገዛ ስልጣኔ ሥራ ለቅቄያለሁ፡፡ ድርጅቱንም አልፈልግም ራሴን አግልያለሁ›› ብዬ ተጣላን፡፡ ‹‹ለቅቄያለሁ ብለህ ማመልከቻ አስገባ›› አለኝ፡፡ ወረቀት ተቀብዬው አጠገቡ ቁጭ ብዬ ማመልከቻውን ጻፍኩ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ በገዛ ፈቃዴ ሥራዬን ለቅቄያለሁ፡፡ እንድማር የማይፈልገውን ድርጅቴንም ለቅቄያለሁ፡፡ ብዬ ጽፌ ሰጠሁት፡፡ ዕጣ ፈንታዬ ባንተ መዳፍ ውስጥ ካለች ከመዳፍህ ፈልቅቄ አወጣለሁ ብዬው ወጣሁ፡፡ በዚህ ጊዜ እቤቴ ገብቼ ተጠቅልዬ ተኛሁ፡፡ ይህንን ስወስን የት እንደምሄድ፣ ምን እንደምሰራ፣ ልጆቼን እንዴት እንደማስተዳድር አላውቅም ነበር፡፡

ማመልከቻዬንም ይዞ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት በመሄድ ለአንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ ኃላፊ ሪፖርት አደረገብኝ፡፡ እንዳልማር መከልከሉ የጥሩ ሥራ አስኪያጅ ውሳኔ ባለመሆኑ ሲጠየቅ ኦሮሚኛ ክፍልን የሚመራ ሰው ስለማናገኝ ነው የሚል ምክንያት ይገልጻል፡፡ በወቅቱ ሌሎቹን የማይፈልጉትን እንዲማሩ ያስገድዳል ፤እኔ እንድማር የምለምነውን ደግሞ ይከለክለኛል፡፡ ይህ ከፍተኛ አመራርም ፕሮግራሙን የሚመራ ከጠፋ እንዲዘጋና እኔ ትምህርቱን ገብቼ እንድማር ይወስናል፡፡ቀዳሚው ውሳኔ የተሳሳተ መሆኑንና መማር እንዳለብኝ ተወሰነ፡፡ ይህ ሲሆን ስልጠናው አልቆ ፈተናው አንድ ቀን ቀርቶት ነበር፡፡ አለቃዬ ውሳኔውን ይዞ በፍጥነት እንድመጣ መልዕክት ላከብኝ፡፡ መነጋገር እንዳለብንም አሳወቀኝ፡፡ ግን እንደማልመጣ ፊቱ ቀርቤ ይግባኝ እንደማልጠይቅ በምላሼ አሳወቅኩት፡፡

በመቀጠልም ታጋይ የሆነች የምትቀርበኝ የሥራ ባልደረባ ላከብኝ፡፡ እርስዋም ‹‹የኢህአዴግ የሥራ ኃላፊ መጥቷል፤ ሊያናግርህ ይፈልጋል›› ብላ ጎትታ ይዛኝ ሄደች፡፡ ስሄድ እርሱ የለም ፈተናውን ሄጄ እንድፈተን ተነገረኝ፡፡ አሁን ለምን ተፈቀደልኝ ብዬ ስጠይቅም ከላይ ተወስኗል ተባልኩ፡፡ ለፈተና አልተዘጋጀሁም፣ ስልጠናውንም አልወሰድኩም ነበር፡፡ ሦስት ወራት ልዩ ስልጠና ከወሰዱት ጋር ተወዳደርኩ፡፡ አንደኛ ወጥቼ አለፍኩ፡፡ ስሜ ቀድሞ ለኮሌጁ ተልኮ ስላልነበረ  የኢህአዴግ ከፍተኛ ኃላፊ የነበረው (በወቅቱ የኮሌጁ የቦርድ አመራርም) በልዩ ሁኔታ እንድመዘገብ ፈቅዶልኝ ደብዳቤ ጽፎልኝ ገባሁ፡፡ እየሰራሁ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ እማር ነበር፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ስገባ ግን ሥራውን አቁሜ የህግ ትምህርት መማር ቀጠልኩኝ፡፡ በሁለቱም ኮርሶች እስከ 31 ክሬዲት ሃወር እወስድ ነበር፡፡ በ1991 ዓ.ም እና በ1992 ዓ.ም በአንድ ዓመት ልዩነት ሁለቱንም ትምህርት አጠናቀቅኩኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንዲማሩ የፈቀደልዎ የኢህአዴግ የሥራ ኃላፊ፣ ታጋይ የነበረችው ጓደኛዎ እና በወቅቱ የሬዲዮ ፋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን ሊነግሩን ይችላሉ ?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- አያስፈልግም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲታረሙ ከታገሉባቸው መካከል የሚያስታው ሱትን ቢገልጹልኝ?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- የመልካም አስተዳደር ችግርን እንደእኔ የታገለ የለም ብዬ ለመኮፈስ አልችልም፡፡ ግን የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲወገዱ በጣም እፈልጋለሁ፡፡ ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲሰቃይ በጣም ይሰማኛል፡፡ በየደረስኩበት አካባቢ የማየውና ህዝቡ የሚነግረኝ ነገር በጣም ያንገበግበኛል፡፡ ሚዲያ ውስጥ እያለሁ በሙያዬ አማካኝነት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማጋለጥ በርካታ ሥራዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ሬዲዮ ፋና እያለሁ ለአብነት ቢሾፍቱ፣ ከሞጆ እስከ ዝዋይ በኢንቨስትመንት ስም አርሶ አደሮች ሲፈናቀሉ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በትንሽ ገንዘብ አርሶ አደሩን በመደለል አትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ሲያስፋፉ ነበር፡፡ በኮንትራት ስም 15 እና 20 ዓመታት እያስፈረሙ አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው ገፍተው ከፍተኛ የመሬት ወረራ ነበር፡፡ የተፈናቀሉት አርሶ አደሮች ደግሞ ያገኟትን ጥቂት ገንዘብ ጨርሰው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው የነበረበትን ሁኔታ በስፍራው በመገኘት በሚዲያ በማጋለጥ መንግሥት እርምጃ ወስዶ የመሬት ኮንትራት ህግ እንዲሻሻል ማድረግ ችያለሁ፡፡

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የመሬት ንግድ አለ፡፡ የመሬት ንግዱ በመንግሥት አካላት የሚከናወን ነው፡፡ ከመሬት አስተዳደር ጋር የተያያዙ የመንግሥት ሠራተኞች በሙሉ በዚህ ውስጥ እጃቸው አለበት፡፡ የፓርላማ አባልም ስለነበርኩ አንድ ጊዜ ወደ ትውልዴ ወረዳ ኮፈሌ ሄጄ በጣም ከፍተኛ በሆነ መልኩ ችግሮች እንደነበሩ ህዝቡ አልቅሶ አንድ መሬት ለሁለትና ሦስት ሰዎች ይሸጥ የነበረበት ሁኔታ እንዳለ የገለጹልኝን ለምክር ቤት አቀረብኩ፡፡ ምክር ቤቱ ይህ ከአንድ የኢህአዴግ አባል የሚጠበቅ አይደለም በሚል ቋሚ ኮሚቴውና አፈ ጉባዔው ሪፖርቱ እንዳይቀርብ አገዱት፡፡

በሪፖርቱ የጠቀስኩት አርሶ አደሩ መሬቱን  ተነጥቆ፤ የቀብር ቦታ አጥቶ እየኖረ መሆኑን የሚያመለክት ነበር፡፡ ሁሉም ሰው በየቤቱ በየበራፉ ይቅበር ከዚህ በኋላ የጋራ ቀብር ቦታ ሞልቷል ተብሎ ከፍተኛ ችግር ነበር፡፡ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት አለ፡፡ ዛሬም ድረስ አልተፈታም፡፡ ችግሩ ቀጥሏል፡፡ ይህንን ችግር የፈጠረው የመሬት አስተዳደሩ ነው፡፡

በሙስና የተነሳ በጭካኔ አርሶ አደሩ ከመሬቱ በመፈናቀሉ የሚያርስበት፣ ቀብር የሚፈጽምበት ቦታ የለውም፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮም እኔም ምክር ቤት አልገባም ብዬ አቆምኩ፡፡ ያ ምክር ቤት ጊዜውን አጠናቅቋል፡፡ አሁን ካለው ምክር ቤት በፊት የነበረ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የህዝቡን ብሶት እና ጩኸት ላለማየት ወደተለያዩ አካባቢዎች መጓዝ ይጨንቀኝ ነበር፡፡ ለሚቀርቡኝ ኃላፊዎች እናገራለሁ፡፡ ቢሰሙም እርምጃ ሲወሰድ አይታይም፡፡ ችግሮችን ስትናገር ካድሬው ራሱ ይነሳብሃል፡፡ ምዕራብ አርሲ የነበረው የቀድሞ አመራሮች እየመጣ ህዝብ ያሳምጽብናል ብለው ከሰውኛል፡፡ ወጣቶች ተደራጅተው መሬት ወስደው መስራት እንዳለባቸው፣ መንግሥትን ብቻ መጠበቅ እንደማይገባቸው የተለያዩ ጥረቶችን አደርግ ነበር፡፡ እነርሱ ግን አምባሳደሩ እየመጣ ህዝብ ያሳምጽብናል ይሉ ነበር፡፡ በእዚህ የተነሳ ምንም አላመጣም ብዬ እግሬን ወደ ማሳጠር ገብቻለሁ፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግር ለማስተካከል ችያለሁ አልልም፡፡ ግን በማየው ነገር በተቻለኝ መጠን በቅንነት በመሳተፍ፣ በማዳመጥ ለማስተካከልና የመፍትሄ አቅጣጫ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ ከሚረዱኝ የዞንና የወረዳ የአስተዳደር አካላት ጋር አንዳንድ ሥራዎችን እሰራለሁ፡፡ እነርሱ እንደተወነጀሉ፣ እንደተጋለጡና እንደተተቹ ስለሚቆጥሩ፣ ከላይም በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች እነርሱን የበለጠ ስለሚያምኑና ስለሚቀበሉ እየታመምኩና ውስጤ እየቆሰለ ከመኖር በስተቀር ዕድል አልነበረም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮግራም ኃላፊ ከነበሩበት ወደ ቀድሞው ሬዲዮ ፋና ተዘዋውረው መስራትዎ ይታወቃል፡፡ የዝውውሩ ምክንያትና በወቅቱ ያሳለፉት ሁኔታ ምን እንደነበር ሊነግሩን ይችላሉ?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- ከበረሃ እንደገባሁ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የሦስቱም ፕሮግራሞች አስተባባሪ ሆኘ ነው ተመድቤ የሰራሁት፡፡ ያኔ ተቋሙ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተብሎ በኢህአዴግ ፕሮፖጋንዳ ቢሮ ይመራ ነበር፡፡ ሁለት ዓመታት እንደሰራሁ አንዳንድ አቋሜ ስላልጣማቸው ወይም ስላልተመቸኋቸው ይመስለኛል በገዛ ፍቃዴ ስልጣን እንድለቅ መመሪያ ተሰጠኝ፡፡ በፈቃደኝነት ስልጣን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ ምክንያቱን እስካሁን አላውቅም፣ ይህንን አጠፋህ ተብዬም አልተቀጣሁም፣ አልተወቀስኩም፣ አልተገሰጽኩምም፡፡ ሳስበው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነባር ሠራተኞችም ይህንን ነገር የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡አንዳንድ ጊዜም ከኦነግ ጋር እያገናኙም ይወነጅሉኝ ነበር፡፡ ግን የኦነግ አባልም አልነበርኩም፡፡

ሚዲያው ነጻ ሆኖ እንዲሰራ ጋዜጠኞችም ነጻነት እንዲሰማቸው እፈልግ ነበር፡፡ ይሄ አልተመቻቸውም፡፡ ሥራ ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ ሥራ ፈት ሆኜ ነበር፡፡ በኋላ ሬዲዮ ፋና በመቋቋም ሂደት ላይ ስለነበር እዛ እንድገባ ተወሰነ፡፡ ሥራ ጀመርኩ ካቋቋምን በኋላ የኦሮምኛ ፕሮግራም ኃላፊ ሆኜ ሰራሁ፡፡ ተማርኩ፡፡ በመቀጠልም በሁለቱም ትምህርት ዲግሪዬን ከያዝኩ በኋላ ተሃድሶ መጣ፡፡ በተሃድሶ ማግስት ኦሮሚያ ክልል እንደገና እንዲዋቀር ስለተደረገ ተዘዋወርኩ፡፡ አዲስ አመራር ተመሰረተ፣እኔም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኜ ተመደብኩ፡፡ ባህልና ማስታወቂያም አብሮ ነበር፡፡ ሁለት ዓመታት ያህል እንደሰራሁ እዛም ያለመጣጣም አጋጠመኝ፡፡ በወቅቱ የድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ላይ ደርሼ ነበር፡፡ ከነበሩት አንዳንድ የድርጅትና የክልል አመራሮች ጋር ባለመስማማት ግምገማ እንኳን ሳይካሄድ ተወገድኩ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከስራ እንዲለቁ በተደጋጋሚ ጫና የሚደርስብዎ ለምንድን ነው?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- እንዲህ አይነት ጫና በእኔ ላይ ብቻ የተደረገ አይመስለኝም፡፡ ጫና በሁሉም ላይ ይደርሳል፡፡ በእኔ ላይ የሚደረገው በተለየ መልኩ ነው፡፡ የኢህአዴግ አመራር  ተገዢ ሰው ነው የሚፈልገው፡፡ የሚሰጠውን መመሪያ ያለመጠየቅና ያለማመንታት የሚቀበልና ፈጽም የተባለውን የሚፈጽም ሰው ነው አመራሩ የሚፈልገው፡፡ ጥያቄ ወይም አማራጭ ካቀረብክ፣ ካላመንክበትና ከተቃወምክ እንዳፈንጋጭ ትቆጠራለህ፡፡ ስም ይወጣልሃል፡፡ ኦሮሞ ከሆንክ ጠባብ ወይም ኦነግ ትባላለህ፡፡ አማራ ከሆንክ ትምክህተኛ እየተባልክ ትወገዳለህ፡፡ በመሆኑም ጠያቂ መሆን የለብህም፡፡ የሚሰጥህ አመራር ምንም አይነት ችግር ያለበት ቢሆንም ያለማመንታት መፈጸም አለብህ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባል ነገር አለ፡፡ ባታምንበትም ከማዕከል የተሰጠህን መመሪያ ባለማመንታት ተፈጻሚ ማድረግ አለብህ፡፡  እዚህ ላይ ጉድለት ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ በዚህ የተነሳ እባረራለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ከኦሮሚያ ክልልም የተባረርኩት፡፡

የኦሮሚያ ክልል አመራርና የኦህዴድ አመራር ድንገት በአንድ ስብሰባ እኔና አንድ ጓደኛዬን ከአመራርነት እንድንወርድና እንድንወገድ ተደረገ፡፡ አራት ወራት ያህልም ሥራ ፈት ሆነን ተቀመጥን፡፡  ቤት መዋል ጀመርኩ፡፡ መኖሪያ ቤቱንም ለመልቀቅ ተገደድኩ፡፡ ሥራ ፍለጋ ላይ እያለሁ የኢህአዴግ አመራር ሰምቶ ውጭ ጉዳይ እንድመደብ ተደረገ፡፡ ውጭ ጉዳይ መግባት በአንድ በኩል ልዩ ጥቅም ነው፡፡ ግን በስደት መልክ በመሄዴ ብዙ እርካታ ሳይሰማኝ ነው የኖርኩት፡፡ ምክንያቱም ከክልሉ የወጣሁት አጥፍቼ አይደለም፣ ብቃት አለው ተብዬም አይደለም የተመደብኩት በግዞት መልክ ነው፡፡ የክልሉ አመራርና ገዢ ፓርቲ አንድ ላይ ተባብረው   ነው በሴራ ያስወጡኝ፡፡ የፍትህ መጓደል ስለሚሰማኝ ያገኘሁት ልዩ ጥቅም ቢሆንም ግን እርካታ አልነበረኝም፡፡ ያገኘሁት ጥሩ ደመወዝ፣ ጥሩ ሥራ ቢሆንም ኢ- ፍትሃዊነት ስለሌለው እርካታ አይሰጠኝም፡፡ ሌብነትን፣ አድልዎን፣ የአስተዳደር በደልን በመቃወሜና በመናገሬ ከኃላፊነት ተወግጃለሁ፡፡ ካጠፋሁ መቀጣት ሲገባኝ በሹመት ወደ ሌላ መስሪያ ቤት መዘዋወሬ አያስደስተኝም፡፡ በኋላም ራሴን አሳምኜ በተቋሙ በውጤታማነት ስሰራ ቆየሁ፡፡ አሁን ወደ 20 ዓመታት ተጠግቷል፡፡ የውጭ ግንኙነት ሥራ በጣም አስደሳች ሥራ ነው፡፡ አለምን ለማየት አስችሎኛል፡፡ እዛም ሆኖ ግን መታገል ይቻላል፡፡ በመታገል ድርጅቱ ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ተግባር አድርጌያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጅቡቲ ለረጅም ዓመታት እንደመቆየትዎ በሜቴክ ላይ ይታዘቡት እንደነበረው ዓይነት በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ላይ የከፉ ችግሮች፣ሌብነቶች ያውቁ እንደነበር አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ እስኪ ይንገሩኝ?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- የትኛውን ነክቼ የትኛውን ልተወው፡፡  ብዙ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ተቆጥሮ የማያልቅ ጥፋት በአገራችን ላይ ደርሷል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የምናስገባበት ስርዓታችን በጣም አድሎአዊ ነው፡፡ ወደ ውጭ የምንልክበት ስርዓታችን  ደግሞ ስርቆት ነው፡፡ ለምሳሌ በጣም ተፈላጊ የሆኑ ሸቀጦች (ብረት) የግንባታ መሳሪያዎች ለተወሰኑ ቡድኖችና ቤተሰቦች ብቻ የተለቀቀ ነው፡፡ ሌላው አይሳካለትም፣ ውድድር የለም፡፡ ተወዳድሮ ሁሉም የፈለገውን እያስገባና እየላከ የሚከብርበትና የሚከስርበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ወደ ፊት በህግ የሚጣሩ ናቸው፡፡ የተወሰኑ ወደ ውጭ የሚላኩ ሸቀጦች ለተወሰኑ ሰዎች ተከልሎ ተከፋፍሎ የተሰጠ ነው የሚመስለው፡፡ ለምሳሌ የግድግዳ ቀለም የሚያስገባ አንድ ሁለት ሰዎች ወይም ድርጅት ብቻ ነው ያለው፡፡ ብረት የሚያስገባ የታወቀ ብቻ ነው፡፡ በሞኖፖሊ የተያዙ ናቸው፡፡

ብዙ ዕቃ ወደብ ላይ ይባክናል፡፡ የቡና ንግዳችን በዋናነት ወደ ውጭ የሚላክ ምርታችን ነው፡፡ ወደ ውጭ የሚላክበት መንገድ ሲታይ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ የውጭ ንግዱ የሚያስገኘው ገቢ አብዛኛው ወደ ውጭ የሚከፈል ነው፡፡ አገር ውስጥ የሚገባው ጥቂቱ ነው፡፡ አርተፊሻል የዋጋ ንረት የሚፈበረከውና የሚፈጠረው እዛ ላይ ነው፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሎባቸው የሚገቡት እቃዎች ቀልጣፋ የማንሳት ስርዓት የለም፡፡ ወጪውን የሚከፍለው ደግሞ ደሃው ሸማች ህብረተሰብ ነው፡፡ ከቀረጥ ነጻ በኮንትሮባንድ የሚገባ እቃ መጠን የለውም፡፡ የመኪና መለዋወጫዎች፣ የግንባታ መሳሪያዎች፣ ሲጋራ፣ መጠጥና ሌሎች በርካታ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ የሚገቡበት ሁኔታ በርካታ ነው፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ የተወሰኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ለአገር ከፍተኛ ጉዳት ነው፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚው በህግና በሥርዓት ተመርቶ ቢሆን ኖሮ አገራችን የትና የት በደረሰች ነበር ብዬ እቆጫለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በተላለፈው ዶክመንታሪ እንደተጠቆመው ሜቴክን በተመለከተ ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ሰፋ አድርገው ቢነግሩኝ፡፡ የጻፉት ለነማን ነበረ፣ ይዘቱስ ምንድን ነው?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- መጀመሪያ የጻፍኩት ለምሰራበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ነበር፡፡ ‹‹ተወው ይቅርብህ›› የሚል ምላሽ ሳገኝም አመራር ብሆንም አላመንኩበትም ነበር፡፡ አመራር መቀበል ግዴታ አለብኝ ግን ይህንን አመራር በመቀበል የሚደርሰው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ በአገር ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን እያወኩ መተው አልቻልኩም፡፡ ትክክለኛ አመራር ካለ ልጠየቅበት ብዬ ወደ ሌላ አካላት አመለከትኩ፡፡ ለሚዲያ መጻፍም አስቤ ነበር፡፡ ግን ጉዳዩን ደፍሮ የሚሰራ የሚዲያ ተቋም አለ ብዬ አልገመትኩም፡፡

ቀጥዬ ለፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጻፍኩኝ፡፡ በአካል ቀርቤም አነጋገርኩኝ፡፡ ጉዳዩ አስቸጋሪ መሆኑን፣ የመንግሥት ፖለቲካን ይጎዳል በሚልም ምንም እንደማያደርጉ ነገሩኝ፡፡ ተቋሙ ገለልተኛ አለመሆኑን ስለተረዳሁ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጻፍኩኝ፡፡ በአካልም ተገናኝተን ጠቅላይ ሚኒስትሩን አስረዳኋቸው፡፡ ውጭ ጉዳይም የነበሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሲሆኑ አከታትዬ ጻፍኩላቸው፡፡ አዲስ ለመጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ደጋግሜ ጻፍኩ፡፡

ስድስት ወራት መርከቦቹ ወደብ ላይ ሲቆሙ በመጻፍ ላይ ነበርኩኝ፡፡ ምንም የተወሰደ እርምጃ የለም፡፡ ጥፋቱ ከባድ እንደሆነ ይታየኛል፡፡ ይህ ሁሉ እየታወቀ ጥፋቱ የሚፈጸመው ለምንድን ነው ? ወይም እነርሱ የሚፈልጉት ነገር አገራዊ ጥቅምን ሳይጎዳ እንዲደረግ ይመቻች፡፡ ይህ ካልሆነ በጥፋት መንገድ ሃብቱን እየመሩ ስለሆነ አስቁሙ እያልኩ ብጽፍም ደፍሮ ማስቆም የሚያስችል ግን አልተገኘም፡፡ በመጨረሻ ላይ በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያቆሙ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ አሁን ተጠርጥረው የታሰሩትን የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ጠርተው መርከቦቹን ወደ ኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት እንዲመልሱና የባህር ትራንስፖርት ክፍል የማቋቋም እቅዳቸውን እንዲሰርዙ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከእዛ ወጥተው ዘወር በል ነው ያሉት፡፡ መርከቦቹን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መመሪያ መሰረት አላስረክብም ነበር ያሉት፡፡ ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር እንኳን ተቀባይነት የሌለው ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የመንግሥት ስልጣን አራት ኪሎ ሳይሆን ሌላ ቦታ ነው ያለው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ፡፡ የማይታዩ የተደራጀ ቡድን በእኔ አጠራር (oligarchy) አገሪቱን በአምባገነንነት ለመግዛት በግዛታቸው ስር አስገብተው በማይታይ ስልጣናቸው የሚመሩ ናቸው፡፡ ስልጣኑ ያለው የሚታወቀው መንግሥት ጋር ሳይሆን የማይታይ ኃይል ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ተሸንፏል፣ መንግሥትም የለም ብዬ ደመደምኩኝ፡፡  የተደራጀው የዘረፋ ቡድን የህግ አወጣጥና የህግ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ ማድረግ ይችላል፡፡ ህግ እንዲወጣ የሚያደርገውም በሚፈልገው ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ እስከ ለውጡ ድረስ የምትመራው በተደራጀው ቡድን ነበር፡፡ ስልጣን የነበረው ደህንነቱና መከላከያው ጋር ነበር፡፡ ይህ ቡድን በአካል የተለያየ ቦታ የነበረ ነው፡፡ ስልጣኑም በእጁ ነበር፡፡ ጠመንጃ ያለው፣ ጀኔራሎችና ወታደሮች የበዙበት ስለነበር ሲገዛ የነበረው በጠመንጃ ነበር፡፡ አገሪቱን ሲመራ የነበረው ስልጣን የተሰጠው አካል አልነበረም፡፡

በቻልኩት መጠን ባገኘሁት መድረክ ግን ትግሌን አላቆምኩም ነበር፡፡ ለምሳሌ በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የህዝብ አመጽ ተከስቶ የኢህአዴግ ምክር ቤትና ነባር ካድሬዎች አንድ ላይ በችግሩ ለመወያየት  በተጠራ ስብሰባ ላይ የችግሩ እውነተኛ ምንጭና መፍትሄን በግሌ አንስቼ ተናግሬ ነበር፡፡ ብልሽቱ ከህዝብ ውስጥ ሳይሆን የአመራር ችግር እንደሆነ ጠቁሜ ነበር፡፡ አገር እየተዘረፈ ህዝብ እየተጎሳቆለ፣ ጥቂቶች እየከበሩ ህዝቡ እየቆረቆዘ ነው፡፡ እኩልነትና ዴሞክራሲ ጠፍቶ፣ መብት እየተጣሰ ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ብልጽግና እና ዴሞክራሲን እያወራን መቀጠል አንችልም በሚል ሰፊ ዕድል ተሰጥቶኝ ተናግሬ፣ አዳምጠውኝም ነበር፡፡ ይህንን ለአመራሩና ለምክር ቤቱ ግልጽ በሆነ መንገድ አቅርቤያለሁ፡፡ ያንን ዕድልም በማግኘቴ ደስተኛ ነበርኩኝ፡፡ በወቅቱ ተቃውሞም አልተነሳብኝም፡፡ አንዳንዶቹ ሲያበረታቱኝ፣ አንዳንዶቹ ጥርስ ነክሰውብኝ ወጡ፡፡ በዛን ጊዜ ሜቴክን፣ ስኳር ኮርፖሬሽ፣ታላላቅ ያልተሳካላቸውን ፕሮጀክቶችን እንደ ምሳሌ እየጠቀስኩኝ ዘረፋው የአመራሩ እንደሆነ የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ከእናንተ ጀምሩና ኪሳችሁን ፈትሹ፤ እውነት በትክክል በገቢያችሁ ነወይ የምትተዳደሩት፣ እያንዳንዳችንም ኪሳችንን እንፈትሽ ነበር ያልኩት፡፡ በወቅቱ ይህንን ማለት ድፍረት ቢሆንም ማለት ግን ነበረብኝ፡፡ መልስ አልነበረም፡፡ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡ ጓዶች ነበሩ ፤ ምንም አልተባለም፡፡ መፍትሄውም ጥፋት እየፈጸምን ያለነው ተናዝዘን ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ገብተን ህዝቡን ይቅርታ እንጠይቅ፣ ሰው መግደል እናቁም፣ በጠመንጃ ይህችን አገር ለመግዛት ያለንን ምኞት እናቁም ነበር ያልነው፡፡ ህይወት በማጥፋትና ሃብት በመዝረፍ ያጠፋናቸውን ጥፋቶች ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ እናቁም ነበር ያልነው፡፡ የተደመደመው ግን ይህንን ጉዳይ ወደ ክልላችሁ፣ ወደ ድርጅታችሁ ይዛችሁ ሄዳችሁ ይህንን በስፋት እዩ ተብለን ተለቀቅን፡፡

ወደ ድርጅታችን ተመልሰን መስከረምና ጥቅምት ወራትን ከመድረኩ የተሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ ስናደርግ በወቅቱ የነበረው አመራር ችግሮቹን ለማየት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ሥራ አስፈጻሚው በእኛ በኩል ምንም ጥፋት አላየንም የአመራር ውድቀት ግን አጋጥሞናል የሚል የሚጋጭ አቋም ያዘ፡፡ በድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ ላይ ስናይ በጭራሽ የሚያስማማ አይደለም፡፡ በወቅቱ የነበረውንም አመጽ የሚያስቆም አይደለም፡፡ እንደሚታወሰው የእሬቻ ግር ግር ሰሞን ነበር፡፡ ሥራ አስፈጻሚው ያቀረበውን ግምገማ አልተቀበልንም፡፡ ምክንያቱም አመራሩ ሀቁን መቀበል አልፈለገም፡፡ ወድቀናል ግን እንቀጥል የሚል ነበር፡፡ እኔ የነበረኝ አቋም አመራሩ መፍረስ እንዳለበት ነበር፡፡ ሥራ አስፈጻሚውና ማዕከላዊ  ኮሚቴው ፈርሶ በአስቸኳይ የድርጅት ጉባዔ ተካሂዶ አዲስ አመራር እንዲመረጥ ድርጅቱ እንደገና እንዲታደስ፣ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ይሰጥ የሚል አቋም ነበረኝ፡፡ ይህንን አቋምም በስፋት በማራመድ ማዕከላዊ ኮሚቴውን ለማሳመን ችያለሁ ለማለት እችላለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ አመራሩን በሙሉ አፍርሰን አዲስ ጉባዔ ከምንጠራ የጉባዔው ወቅት ስለደረሰ እስከ ጉባዔው ድረስ የድርጅት ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አንስተን አዲስ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንምረጥ የሚል መግባባት ላይ ደረስን፡፡ በዚህ መሰረት ነባሮቹ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ስልጣን ባለው ማዕከላዊ ኮሚቴ ተሽረው ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳና ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተመረጡ፡፡ ኦህዴድ ይህንን እርምጃ በመውሰዱ በተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ብዙም የተወደሰ አይመስለኝም፡፡ ተቃውሞም ቀርቦብናል፡፡ ኦህዴድ የሄደው ከተሰጠው አቅጣጫ ውጪ ነው በሚል ትችት ነበር፡፡

በወቅቱ 13 የኦሮሚያ ዞኖች አመጽ ላይ ነበሩ፡፡ ከመንግሥት ቁጥጥር ወጥተው የመንግሥት መዋቅር የፈረሰባቸው ስለሆነ ይህንን ማድረግ የግድ ነው የሚል መከራከሪያ ሃሳብ ነበረን፡፡ በኋላ ግን መፈንቅለ ስልጣን ነው የተካሄደው በሚል ከአንዳንድ ድርጅቶች በተለይም ከህወሓት ወቀሳ ነበር፡፡ አዳዲሶቹ አመራሮች ወርደው እንዲታሰሩ፣ የወረዱት ነባሮቹ አመራሮች ደግሞ ወደ ስልጣን እንዲመለሱ የፈለጉ የህወሓት አመራሮች ነበሩ፡፡ ይህ እንደማያስኬድ፣ ኦህዴድ የወሰደውን እርምጃ የኦሮሞ ህዝብ የደገፈው በመሆኑ ለከፋ አመጽ ይዳርገናል በሚል ተመካክረው ነው ያቆሙት፡፡

ከዛ ጊዜ ጀምሮ ህወሓት ደስተኛ አልነበረም፡፡ የተደራጀው አምባገነን መንግሥት ወታደራዊ፣ ጀኔራሎች ያሉበት የደህንነቱ ክፍል ደስተኛ አልነበረም፡፡ ወደ መንግሥት ኃላፊነት የመጣው የኦህዴድ አዲሱ አካል በተለይም የህዝብ ድምጽ ለመስማት፣ የህዝብን ችግር ለመፍታት የሚወስዳቸው እርምጃዎች በጭራሽ ለህወሓት እና ለተደራጀው የዘረፋ ቡድን የሚዋጥ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት በቀድሞው ኦህዴድ (የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) አመራርና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ የተደራጀው ቡድን የተለያዩ ጫናዎች ይደረጉ ነበር፡፡

ይህ አመራር ብዙም ስልጣን ላይ ሳይቆይ በሶማሌ ክልል መከላከያ ያደራጃቸው የሶማሌ ልዩ ፖሊስ የሚባለው ኃይል በኦሮሚያ ላይ እንዲዘምት ተደረገ፡፡ የሁለቱ ክልሎች ግጭት በማስመሰል በምዕራብ ሐረርጌ ከቦርደዴ እስከ ሞያሌ ባለው ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ልዩ ኃይሉ ዘምቶ የኦህዴድን መዋቅሮች፣ የክልሉን መንግሥት መስሪያ ቤቶች እስከማጥፋት፣ አስተዳደሮችንና ካድሬዎችን እስከ መግደል ደረሰ፡፡

የፌዴራል የፀጥታ ተቋሞችን በመጠቀም ወረራ ፈጸመ፡፡ ህዝቡ በተቻለውና ባለው አቅም ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ በመመከት ቢቀለብስም በዘረፋ ቡድኑ የተደራጀው ቡድን ይሁንታ በወቅቱ የሶማሌ ክልል አስተዳዳሪ የነበሩትና ተጠርጥረው እስር ላይ በሚገኙት አቶ አብዲ 700 ሺ ኦሮሞዎች ተፈናቅለው እንዲባረሩ ተደርጓል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለው በጅምላ መቃብር ተቀብረዋል፡፡ ይህንን ህግ ወደፊት መርምሮ የሚያወጣው ይሆናል፡፡

ከግጭቱ ውጪም ሰላማዊ የኦሮሞ ተወላጆች በሶማሌ ክልል በአብዲ ገዳይ ቡድኖች ተጨፍጭፈዋል፡፡ ይህ በተደራጀው ቡድን ይሁንታ የተፈጸመ ነው፡፡ የተደራጀው ቡድን እንዲህ ዓይነት ጭፍጨፋ ለሚያደርገው የአብዲ ቡድን ነበር የሚሟገተው፡፡ ትጥቅ ይሰጣል፣ የመንግሥት መሳሪያ ያስታጥቃል፣ የኦሮሚያ አካባቢ ደግሞ ትጥቅ ያስፈታል፡፡  አዋሳኝ አካባቢ ያለው የኦሮሚያ ህዝብ በፌዴራል መንግሥት አማካኝነት ትጥቅ እንዲፈታ ይደረጋል፡፡ በግሌ የፌዴራል መንግሥት ወረራ እንጂ የሶማሌ ክልል ወረራ አልልም፡፡ ምክንያቱም ልዩ ፖሊስ የሚባለው ራሱ የመከላከያ አካል ነው፡፡ አርማውም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ልዩ የፖሊስ ኃይል ነው የሚለው፡፡ በዚህ መንገድ ወደ ኦሮሚያ ክልል የመጣውን ልዩ አመራር እንዳይረጋጋ፣ የህዝቡን ጥያቄዎች እንዳይመልስ፣ ክልሉን በሥነ ሥርዓት እንዳይመራ ማድረግ ነበር፡፡

ትልቁ የቡድኑ ፍላጎት ሁለቱን የኢኮኖሚ መስመሮች ከአዲስ አበባ ቶጎ ጫሌ የሚወስደውን መንገድና ከአዲስ አበባ ሞያሌ የሚወስደውን መቆጣጠርና በሶማሌ ክልል አስተዳደር ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአዲሱ የኦሮሚያ አመራር ጊዜ ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ መያዝ ስለተጀመረ ነበር፡፡ እንደሚታወሰው ቦርደዴ ላይ 500 ሺ ዶላር ተይዞ ነበር፡፡ ጦርነት ያስነሳው ይህ ነበር፡፡ ገንዘቡን የያዘው ፖሊስ በሁለተኛው ቀን በስናይፐር ተገድሏል፡፡ አልተጠየቀም፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥፋት ነው የተፈጸመው፡፡ የፌዴራል መንግሥት አካላት እነ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በወቅቱ ምንም አይናገሩም ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት አፈና ነበር፡፡ በመጨረሻም አምባገነኑ ቡድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ማወጅ ገብቷል፡፡

የአዋጁ ዋና አላማ ኦህዴድን፣ የክልሉን አመራር ማፍረስ ነው፡፡ የክልሉን አመራር ስልጣን የገደበ ነበር፡፡ ነገር ግን አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ነበር፡፡ አዋጁ በዋነኝነት የታዘዘው በኦሮሚያ ላይ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ግን ኮማንድ ፖስት ውስጥ አይገባም፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ኢ-ህገ መንግሥታዊ የሆነ ተቋም ነው፡፡ አዋጁ ለጊዜው አመጹን አቀዝቅዞታል፡፡ ግን የአዋጁ ዋናው አላማ የወቅቱን የኦህዴድ አመራርን ማፍረስና ድርጅቱን ማዳከም ነበር፡፡ አመራር ከቀየረ በኋላ ኦህዴድ እንዲፈርስ ይፈለግ ነበር፡፡  የተደራጀው የዘረፋ ቡድን የኦህዴድን ከህዝብ ጋር መወገን ፈጽሞ አይፈልግም ነበር፡፡ አዋጁ በትግል እንዲነሳ ተደረገ፡፡ ከዛም የፌዴራል ተቋማት ለምሳሌ የደህንነት ተቋሙ ራሱ አመጽ ያነሳሳ ነበር፡፡ የኦነግን ባንዲራ በተለያዩ ቦታዎች እየበተነ ወጣቶችን በማነሳሳት ኦነጎች ናቸው በሚል እርምጃ እንዲወሰድ ያደርግ ነበር፡፡ አመጹን በማስቀጠል የመከላከያና የደህንነት ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

በመቀጠልም ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፡፡ ይህ ለመጨረሻ ጊዜ ኦሮሞን በወታደራዊ አገዛዝ ስር ለማስገባት የተደረገ የመጨረሻ ሙከራ ነው፡፡ ለይስሙላ በመላው አገሪቱ ታውጇል ይባል እንጂ ዋና አላማው የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡  ያ ሁሉ ህዝብ ከሶማሌ ክልል ሲፈናቀል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራ ላይ ነበር፡፡ አዋጁ 700 ሺ የኦሮሞ ተወላጆች እንዳይፈናቀሉ ማድረግ አልቻለም፡፡ ኦሮሚያ ክልል ሁለት ሦስት ሰዎች ከተሰበሰቡና የመብት ጥያቄ ከተነሳ ይመታሉ፡፡ በወቅቱ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት በተደራጀው ቡድን ትዕዛዝ በማፈናቀል ቀጥተኛ እጁ ነበረበት፡፡ በዚህ ሁኔታ ከችግር ወደ ችግር ስንሸጋገር ቆይተናል፡፡ ችግሩ እንዳይፈጠር ለማድረግ ብዙ ታግለናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ስቃወም የነበረው ይዘን የተነሳነው አላማ መንገድ ላይ መቅረቱን በመቃወም ነው እንጂ የተለየ ነገር አልነበረኝም፡፡

ደርግ የቀበራቸውን የጅምላ ቀብሮችን እያፈረስን አጽም አውጥተን በክብር ስናሳርፍ እንዳልነበረ በጅምላ ጨፍጭፈን በጅምላ ቀባሪዎች ወደ መሆን ተሸጋግረን ነበር፡፡ በቅርቡ ከአንድ ጉድጓድ 200 አስከሬን ወጥቷል፡፡ ይህ ሩዋንዳ ካልሆነ በስተቀር የትም ተደርጎ አይታወቅም፡፡ ገና ከዚህ በላይ የሚወጣ ይኖራል፡፡ መንግሥት የማያውቃቸው ስውር እስር ቤቶች እንዳሉ አሁን ነው የሰማነው፡፡ በዚህ ዘመን ይፈጸማሉ ተብሎ የማይታሰቡ ነገሮች ሲፈጸሙ ነበር፡፡ አመራር አንድ ጊዜ መውደቅ ከጀመረ ብዙ ጥፋቶች ይከሰታሉ፡፡ በዚህ ዘመን በትውልድ ላይ ይፈጸማሉ ተብለው የማይታሰቡ ነገሮች ሲፈጸሙ ነበር፡፡  እኔ ይህ እንዳይሆን እፈልግ ነበር ግን ሆኗል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ይህ ቡድን በዘመድ አዝማድ የተሳሰረ ነው ብለው ያምናሉ ?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- በዘመድ አዝማድ መረዳዳት አለ፡፡ ግን በጥቅም ነው የሚገናኙት፡፡ ከአንድ አካባቢ፣ ከአንድ ክልል ወይም ከአንድ ብሄር ብሄረሰብ የሚባል አይደለም፡፡ ከሁሉም ክልሎች አሉበት፡፡ እነዚህ የህዝብ ወኪሎች አይደሉም፡፡ ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ የጥፋት ቡድኖች ናቸው፡፡ ደርግን ለመጣል የታገለው ድርጅት ነው ወደዚህ የተቀየረው፡፡ አሳዛኙ ነገር እርሱ ነው፡፡ ደርግ ከፈጸመው የማይተናነስ ጥፋት የፈጸመው ደርግን ለመጣል የታገለው መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ወደ አንድ አካባቢ የሚወረወር አይደለም ህብረ ብሄር ነው፡፡ አገር አቀፍ ነው፡፡

ይህ የሚመለከታቸው ብዛት ያላቸው የኦሮሞ ተወላጆች፣ የአማራ ተወላጆች፣ የትግራይ ተወላጆች፣የሶማሌ ክልል፣ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ተወላጆች እና ሌሎቹም አሉበት፡፡ እነዚህ ሰዎች አገሪቱን ወደማፍረስ ነው የደረሱት፡፡ አሁንም የህግ የበላይነት ተከብሮ፣ የተረጋጋ መንግሥት ኖሮ ከማየት አገሪቱን ለማፍረስ ነው እየሰሩ ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መከላከል ያለበት ይህንን ነው፡፡ አገር እንዳይፈርስበት፣ አገር ለማዳን የቡድኑን ተግባር ማጋለጥ ይኖርበታል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በየአካባቢው ምንም አይነት ግጭት እንዳይጫር መመከት ይኖርበታል፡፡ ‹‹እኛ ካልገዛን ይህች አገር መጥፋት አለባት›› የሚሉ ቡድኖች አገሪቱን እንዳያፈርሱ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በክልል፣ በአካባቢና በአንድነት ተነስቶ አገርን ማዳን አለበት፡፡ ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይንሸራተትና እንዳይገታ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት መቆም አለበት፡፡ የዘረፋ ቡድኑ አገራዊ አንድነት አይሰማውም፡፡ የዘረፈውን ወደ ተለያዩ አገሮች ነው የወሰደው፡፡ የእርሱ አገር ገንዘቡን የደበቀበት አገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተጎሳቆለች፣ የተዘረፈች አገር ናት የእርሱ አገር አይደለችም፡፡ የህግ የበላይነት፣ ሰላም ብልጽግና እዚህ አገር መጣ አልመጣ የዘረፋ ቡድኑ ጉዳይ አይደለም፡፡ የእኔ ግምገማ ይህ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል፡፡ ምን ተስፋና  ስጋት ይታይዎታል?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- ስጋቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ቆሞ አገሩን ከጥቃት ካልተከላከለ አስጊ ነው፡፡ የዘረፋ ቡድኑ ካንሰራራ ትርምስ  ይፈጠራል፡፡ ይህ እንዳይፈጠር ካደረግን ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ህዝቡ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ለውጡን ካላስቀጠለ ያሰጋል፡፡ ሆኖም ከስጋቱ ይልቅ ተስፋው ይበልጣል፡፡ ዕድል አለን፡፡ ከታሪክም እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ህዝብ አገሩን ይወዳል፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡  ህዝቡ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከመንግሥት ጎን ይቆማል፡፡

የፖለቲካ ሥነ ምህዳሩ ተከፍቷል፡፡ በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ጦርነት፣ ግጭት፣ ግድያ፣ ስደት የማይታሰብበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህል ነው፡፡ ይህ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡  አንድ የጋራ አገር ለመገንባት ያለመ፣ ሰላማዊ ፉክክር የሚደረግበት፣ ለህግ የበላይነት፣ ለሰላም የሚደረግ ፉክክር የሚጠበቅ ዕድል ተከፍቷል፡፡ ይህ መልካም አጋጣሚ ከእጃችን እንዳይወጣ ያገባናል የሚሉ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ አለባቸው፡፡ መንግሥት የሚታይና የሚጨበጥ ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- በመገናኛ ብዙሀን በአመራርነት በቆዩበት ጊዜ ሚዲያው ምን ዓይነት ቁመና ነበረው፡፡ አሁንስ?

አምባሳደር ሱሌይማን፡- በሚዲያው ዘርፍ ከነበርኩበት ጊዜ አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሚዲያው መንግሥት የሚናገርበት ህዝብ የሚያዳምጥበት መሳሪያ ነበር፡፡ አሁን ህዝብ የሚናገርበትና መንግሥት የሚያዳምጥበት መሳሪያ መሆን አለበት፡፡ ሚዲያው ይህንን ማድረግ ካልቻለ የለውጥ አጋር መሆን አይችልም፡፡ በህዝብና በመንግሥት መካከል ገንቢ ሚና የሚጫወቱ መሳሪያዎች ሊሆኑ ይገባል፡፡ አሁን መንግሥት በሚዲያ ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች በነጻነት እንዲሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ባለሙያዎች በኃላፊነትና በነጻነት የህዝብ አገልጋዮች ለመሆን ቁርጠኛ አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ፕሮፌሽናሊዝም ማበብ አለበት፡፡ የደህንነት ክፍሉ ብቻ የሚናገርበትና በገንዘብ የሚደግፈው ሚዲያ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ሚዲያዎች አያስፈልጉም፡፡ መጥፋት ነበረበት ጠፋ፡፡ ነጻ የሆኑ፣ በህዝብ የተወደዱ፣ በመንግሥት የሚደገፉና ህዝብና መንግሥትን በበጎ ሚናነት የሚያገናኙ ሚዲያዎች መስፋፋት አለባቸው፡፡ ከፍርሃት ነጻ ሆነው ለህዝብ አንድነት መስፋፋት ይኖርባቸዋል፡፡  ክፍተቶች ካሉ መንግሥት እንዲያርማቸው የሚሰሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!

አምባሳደር ሱሌይማን፡-  እኔም ለተሰጠኝ ዕድል በጣም አመሰግናለሁ!

Source EPA

Comments are closed.