Take a fresh look at your lifestyle.

ከብዕር ይልቅ ዱላ የቀለለውን የዩንቨርሲቲ ተማሪ እና የነገዋ ኢትዮጵያ ሳስብ (በያሬድ ሃ/ማርያም )

269

ጋብ ብሎ የነበረው በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታየው ተማሪዎች በጎጥ እየተደራጁ የመቧቀስ የኋላ ቀርነት አዙሪት ይህን ሳምንት ደግሞ እንደ አዲስ አገርሽቶ መታየቱ እጅግ አሳዛኝም፤ አሳሳቢም ነው።

ዩንቨርሲቲዎች የምርምር፣ የእውቀት፣ የጥበብ እና የመፈላሰፊያ መንደሮች ናቸው። የዩንቨርሲቲው ማህበረሰብም አቅሙ የሚለካው በሰነቀው እውቀቱ፣ ባደረገው ምርምር እና የምርምር ውጤት ወይም ግኝት፣ በሃሳቦች ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች እና ሙግቶች እና ታትመው በሚወጡ ጽሁፎች ነው። የአንድን አገር እጣ ፈንታ የሚወስነው፣ የአገርን እድገት የሚመትረው፣ ትውልድ ቀራጭ የሆነው፣ የአገርን ሁለተናዊ ጉዞ እና አቅጣጫ የሚያሰምረው የህብረተሰብ ክፍል የሚወጣው ከእነዚህ ተቋማት ነው። እነዚህ ተቋማት የሚያፈልቁት የህብረተሰብ ክፍል ጤናማ መሆን የአገሪቱን ጤናማ ሆኖ መቀጠል ያመላክታል። በዛው ልክ የታወከ ምሁር ካፈለቁም የአገሪቱ እጣ ፈንታም እንዲሁ የሁከት ይሆናል።

እንዴት በዩንቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ሰዎች በሃሳቦች ዙሪያ ሳይሆን በዘር ይቧደናሉ? እሺ መቧደናቸውስ ባልከፋ ያላቸውን ልዩነት በሰለጠነ የውይይት መድረክ ለመፍታት ለምን ድፍረት እና ብልሃቱን አጡት? እንዴትስ በአንድ ገበታ አብሯቸው ተቀምጦ እውቀት የሚገበይ ወንድማቸውን እና እህታቸውን መጤ ብለው ፈርጀው ለማጥቃት ተነሱ? በእውነት ይህ እንደ ሃገር ጠልቀን የገባንበትን ዝቅጠት ነው የሚያመላክተው።

ዛሬ በዩንቨሪስቲ ውስጥ ተማሪ የሆኑ ወጣቶች ይህ ሥርዓት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የተወለዱ ናቸው። አንዳንዶቹ ወጣቶች ሲናገሩ አገራችን ብለው የሚያስቡት ተወልደው ያደጉበትን ክልል ነው። ትልቋን ኢትዮጵያን በቅጡ አያቋትም። እንዲያውቋት ተደርገውም አላደጉም። ክልላቸውን ከኢትዮጵያ አግዝፈው እና አተልቀው የሚያዩ ይመስለኛል።

የሚገርመው አጥቂዎቹ ተማሪዎች መፈክራቸው ‘ከሃገራችን ውጡ’ ነው። አንዳንድ ጥቃት የደረሰባቸው ተማሪዎችም በመንግስት መገናኛ ጣቢያዎች ሳይቀር ሲናገሩ እንደሰማሁት ጥያቄያቸው ‘ወደ አገራችን መልሱን’ የሚል ነው። በሁለቱም ወገኖች በኩል በግልጽ የሚታየው እነሱ ከተወለዱበት ክልል ውጭ ያለው ሥፍራ አገራቸው አይደለም ወይም እነሱ የተወለዱበት ክልል የሌላው አገር አይደለም።

ለነገሩ የወያኔ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ውስጥ በዙ አገሮችን ፈጥሯል። ተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ፖለቲከኞችም ክልላቸውን እራሱን እንደቻለ እንደ አንድ ሉዐላዊ አገር አድርገው ሲገልጹ መስማት የተለመደ ሆኗል። ክልሎች እራሳቸውን ማስተዳደራቸው መልካም ሆኖ ሳለ በዘርና በቋንቋ ላይ መዋቀራቸው ግን ሌላ ገጽታ ሰጥቷቸዋል። ለዚህም ጥሩ ማሳያው በተለያዩ የክልል መንግስታት መካከል በአደባባይ ፈጦ የሚታየው ግጭት እና ንቁሪያ በሁለት ሉዐላዊ አገሮች መካከል የሚደረግ እንጂ በአንድ አገር ውስጥ በፌደራል አወቃቀር በተሳሰሩ ክልሎች መካከል ያለ አለመግባባት አይመስልም። ከዛም አልፎ አንዳንድ ክልሎች የፌደራል መንግስቱንም ጭምር እየተገዳደሩ ያለበት ሁኔታ በግልጽ እየታየ ነው። የትግራይ ክልላዊ መንግስት ወንጀለኞችን አሳልፌ ለፌደራል መንግስቱ አልሰጥም ማለቱ፣ ታሳሪዎችን አልፈታም ማለቱ እና አንዳን እያሳያቸው ያሉት ባህሪያት ትግራይ እራሷን የቻለች ሉዐላዊት አገር አስመስሏታል። በክልሎች መካከል ያለው የወሰን ግጭትም እንዲሁ የሁለት አገር የድንበር ግጭት ነው የሚመስለው።

ለማንኛውም እነኚህ በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታዩት መናቆሮች እና በቡድን የሚደረጉ ዘር ተኮር ግጭቶች የጠቅላላ ፖለቲካው ነጸብራቅ ስለሆኑ በቅጡ ሊያዙ እና አፋጣኝ መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል። የዚህ ዘር ተማሪዎች ወደዚህ ክልል አትሂዱ እየተባለ በአደባባይ የሚነገርበት እና ቅስቀሳ የሚደረግበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ከዚህ በኋላ የቀረን ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱ ከባድ አይሆንም።

ተማሪ ከመንግስት ጋር በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ወይም በነጻነት ጉዳይ ሲጋጭ እና እርስ በርሱ በዘር ሲጋጭ እንድምታው ለየቅል ነው።

ተሜ በጋራ ቆማ ለአካዳሚክ ነጻነት፣ ለፍትሕ፣ ለማህበተሰብ እኩልነት እና ጥቅም ከሥርዓት ጋር ስትታገል ሰው ሰው፣ ሙሁር ምሁር ትሸታለች። ተሜ በዘር ተቧድና ወንድም እና እህቶቿን መጤ እያለች ዱላና ድንጋይ ተሸክማ እርስ በርስ መፋለጥ እና እስከ እልፈተ ህይወት የሚያደርስ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረች ግን ምሁርነቱም ቀርቶ ከሰው ተራም ትወርዳለች። ያ ማለት ደግሞ የነገዋ ኢትዮጵያ ከሰውም ተራ በወረዱ ሰዎች እጅ ትወድቃለች ማለት ነው። ሊነጋ የሚመስለውም ጨለማ ጭርሱኑ ድቅድቅ ይሆናል።

<span;>የነገ ብርሃኖቻችን ገና በጠዋቱ መጨላለም ከጀመሩ የመከራ ዘመናችን ይራዘማል። እንደ ማለዳ ጸሃይ እየፈኩና እያንጸባረቁ ከመመጡም መንገዳችን ሁሉ ከተጀመረው ለውጥ ጋር ተዳምሮ ከትውልድ ትውልድ የሚዘልቅ እና ጽልመት የማያሸንፈው የብርሃን መንገድ ይሆናል።

እባካችሁ በልዩነታቸው ዙሪያ ተወያዩ፣ ተጨቃጨቁ፣ ተከራከሩ፣ ጻፉ፣ አንብቡ እንጂ ዱላ አታንሱ። ወገኑን ለመጉዳት ዱላ የሚያነሳ ሰው ከተሸከመው ዱላም ይሁን ድንጋይ የተሻለ ዋጋ አይኖረውም። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ሰው እና ጥሩ ተመራማሪ ምሁር መሆን በቂ ነው።

ለማንኛውም ልቦናውን ይስጣችሁ!

Comments are closed.