ሲበላ ሳቀ !!!
ዳንኤል ክብረት
በሀገራችን ሲፈጠር የነበረው ችግር ሁሉ በአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ ነው ወይ የተፈጠረው?
በየአካባቢው ዛፉን ሲያስቆርጡ የነበሩ ጠማማ የመጥረቢያ እጀታዎች አልነበሩም ወይ?
አለቆቻቸውን ያስደሰቱ መስሏቸው ‹በጥፊ በለው› ሲባሉ ‹በጥይት በለው› እያሉ ሲተረጉሙ የኖሩ በየአካባቢው የሉም ወይ?
ክልሎቹ የፌዴራሉ መንግሥት ለወሰደው ርምጃ ድጋፋቸውን በመግለጫ እየገለጡ ነው፡፡
ከመግለጫው ይልቅ ግን የራስን ጠማማ ነቅሶ በማወጣት ቢገልጡ ይሻል ነበር፡፡
ችግሮቹኮ ሲፈጸሙ የኖሩት በማዕከል ብቻ አይደለም፤ በየጎጡ ነው፡፡ ለመሆኑ በየአካባቢው ዛሬስ የድብቅ እሥር ቤቶች የሉም ወይ?
አንድም ክልል ‹እስካሁን እዚህ ቦታ የድብቅ እሥር ቤት ነበረ፤ አሁን ዘጋሁት› ሲል አልሰማነውም፡፡
አንድም ክልል ‹በኔ አካባቢ ሥልጣን ላይ ሆኖ ሲዘርፍ፣ ግፍ ሲፈጽምና ሰው ሲያሰቃይ የነበረውን እገሌን ለፍርድ አቅርቤዋለሁ፤ ወይም ሽሬዋለሁ› ሲል አልሰማነውም፡፡
የጠፉ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ሕንጻዎች፣ መኪኖች፣ ማሽኖች በየክልሉ የሉም ወይ?
እየጠቆሙ ሲያስይዙ፣ ሲያሣሥሩ፤ በየእሥር ቤቱ ሰው ሲገርፉ፣ የድኾችን ሀብት ሲዘርፉ የኖሩ ባለ ጊዜዎች በየአካባቢው የሉም ወይ ?
መቼ ነው ለፌዴራሉ መንግሥት ከማጨብጨብ ወጥተው ክልሎቹ የፌዴራሉን መንግሥት መንገድ የሚከተሉት? ዐመድ በዱቄት እየሳቀ እንዳይሆን?
ድንቁርና ሀገር ሊወር ነው አሉና ፊደሎች ለውትድርና ተዘጋጁ፡፡
በኋላ ‹ላ› የተባለችው ፊደል ከሰሰች፡፡
‹ሲ – እግሯ ጠማማ ስለሆነ ለውትድርና መሰለፍ የለባትም› ተብላ ከውትድርናው እንድትሠረዝ ተደረገች፡፡
‹ሲ› የተባለችው ፊደልም ይህንን ስታይ ‹ላ›ን አብጠለጠለች፣ በ‹ላ› ላይ ሳቀች፤ ተደነቀች፡፡
የቀሩት ፊደሎችም ‹ሲበላ ሳቀ› ብለው ተናገሩ ይባላል፡፡
አሁንም ነገሩ እንዳይሆን፡፡ የተያዘ ጠማማ ባልተያዘው ጠማማ አይሳቅ፤ ሁሉም ጠማማውን ያውጣ፡፡ ሀገርም ከጠማሞች ትትረፍ፡፡
Comments are closed.