Take a fresh look at your lifestyle.

ከ37 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ግዥዎችን የሚያሳይ 5 ሺህ ያህል የክፍያ ልውውጦችን የያዘ የግዥ ሂሳብ መረጃ  ተገኘ ።

290
  • ሜቴክ በአመዛኙ አስመጪና አከፋፋይ እንጂ አምራች አልነበረም ።

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ለአመታት ሀገሪቱን በቴክኖሎጂና በፈጠራ እመርታ እንድታመጣ እየሰራ እንደሆነ ሲናገር ቢቆይም የድርጅቱ የውስጥ መረጃ የሚያሳየው ተቋሙ በአብላጫው የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሪ ያለከልካይ እየተጠቀመ የአስመጪና አከፋፋይነት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ነው። ከተለያየ የዓለም ክፍሎች ያለቀላቸውን ተሽከርካሪና ቁሳቁስ እንዲሁም መለዋወጫ በማስመጣት ለገበያ ያቀርባል። በዚህም መንገድ ቢሆን ድርጅቱ ትርፋማ መሆን አልቻለም።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ብርሃኑ ጸጋዬ ሰኞ እለት በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መግለጫን ሲሰጡ : የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከ2004 እስከ 2010 አ.ም ከ37 ቢሊየን ብር በላይ የውጭ ግዥን መፈጸሙን : ይህ ግዥም ያለ ምንም ጨረታ መከናወኑን ገልጸዋል። ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችውና መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ሜቴክ አምስት ሺህ ያህል የክፍያ ልውውጦችን አድርጓል። ዋዜማ ራዲዮ  ከ37 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለውና ሜቴክ የፈጸመውን የውጭ ሀገር ግዥ የሚያሳይ የንግድ ልውውጥ ዝርዝር (የግዥ ሂሳብ) መረጃ  ደርሷታል። ይሁንና የደረሰን መረጃ ትክክለኛ ቢሆንም የተፈጸሙትን ግዢዎች ሙሉ በሙሉ የሚያካትት ይሁን አይሁን ለጊዜው ልናረጋግጥ አልቻልንም። [የደረሰንን መረጃ ዝርዝር እዚህ ይመልከቱ-Wazema Radio METEC Transactions ]

የደረሰን መረጃ እንደሚያሳነው በሜቴክ በኩል አብዛኛው ግዥ የተፈጸመው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ከፋችነት ነው። ብዙዎቹ ግዥዎችም የተፈጸሙት ከቻይና ሲሆን ክፍያዎችንም ለመፈጸም እንደነ ስዊፍት: ዌስተርን ዩኒየን አይነቶቹ አለማቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጥቅም ላይ ውለዋል።

ከሜቴክ የተፈጸሙ ክፍያዎችም በቻይና በኩል ባሉት : እንደነ ቻይና መርቻንት ባንክ፣ ኮሜርዝ ባንክ፣ አክሲስ ባንክና ባንክ ኦፍ ቻይና በኩል ነው።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ብርሃኑ ጸጋዬ በወቅቱ የነበረውን ምንዛሬ አስልተው በጋዜጠኞች ፊት እንደተናገሩትም የሜቴክ የውጭ ግዥ ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ የሚልቅ ነው።በርግጥ ከ2004 እስከ 2010 አ.ም በዚህ ደረጃ የውጭ ምንዛሬ የተፈቀደለት ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖሩ በእጅጉ ቢያጠራጥርም ሜቴክ ይህን የውጭ ምንዛሬ የተጠቀመበት መንገድም እጅግ በጣም ጥያቄን የሚያስነሳ ነው።

የቀድሞው ሜቴክ በስሩ 14 ኢንዱስትሪዎች ነበሩት።ኢንዱስትሪዎቹም አምራችነትን ቀዳሚ ያደረጉ እንደሆኑም በተደጋጋሚ ሜቴክ ተናግሯል። በተቃራኒው ሜቴክ የፈጸማቸው የውጭ ግዥዎች የሚያሳዩት፣ ሜቴክ አስመጪና አከፋፋይ መሆኑን እንጂ አምራች መሆኑን አይደለም።

በእርግጥ አልተሳካለትም እንጂ ሙሉ በሙሉ አምርቶ ወደገበያ ሊያቀርብ ያሰባቸው ምርቶች ነበሩት። ድርጅቱ እንደ አማራጭ የተጠቀመው መለዋወጫና አብይ ቁሳቁሶችን በመግዛት የራሱ ምርት እንደሆኑ ለማሳየት የመገጣጠምና ጥቃቅን አካላትን የመጨመር ስራዎችን ሰርቷል። ይህ ሙከራው ደግሞ ለተጨማሪ ወጪ፣ ጥራቱን ላልጠበቀ ምርትና ለተደጋጋሚ ስህተቶች ዳርጎታል።

ኢትዮጵያም የምትጠቀምበት አሰራር አንድ ነገር አገር ውስጥ ተመረተ እንዲባል ከነበረበት ደረጃ ቢያንስ 35 በመቶ እሴት ሲጨመርበት መሆኑን ይገልጻል።ሆኖም ሜቴክ የፈጸማቸው ግዥዎች የአስመጭና አከፋፋይነት እንጂ የአምራችነት ወይም ጉልህ የእሴት ጭማሪ አለመሆናቸውን ያሳያል።

ቢሸፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የተባለው የሜቴክ አካል የከተማ አውቶብሶችንና ሌሎች መኪኖችን እንደሚያመርት በተደጋጋሚ ተነግሯል።ሆኖም ከባንኮች ያገኘነው የዚህ ኢንዱስትሪ ግዥ ቢያንስ 35 በመቶ እሴት የሚጨምር ሳይሆን የሙሉ አውቶብስ ግዥ ነው። ይህ ኢንዲስትሪ ከ279 በላይ የውጭ ግዥዎችን ፈጽሟል።ሆኖም በብዛት ግዥው የሙሉ ያለቀላቸው መኪኖችና መለዋወጫዎች መሆኑን እንጂ አምራች ነው ብሎ ለመበየን የሚያበቃ አይደለም። የግዥ ታሪኩ የሚያሳየው ሙሉ መኪናና መለዋወጫዎችን ነው ።

ፓወር ኢንጂነሪንግ የተባለው ኢንዱስትሪም የአስመጭነት ታሪክ ነው ያለው። 204 የባንክ ትራንዛክሽን ያለውና ሚሊዮን ዶላሮችን ለቻይና ኢንዱስትሪዎች ሲከፍል የቆየው ይህ ኢንዱስትሪ ያለቀላቸው ስማርት ሜትሮች፣ ተርባይን እና ጄኔሬተሮችን ሲያስመጣ መክረሙን ነው የሚያሳየው።

ይህ ኢንዱስትሪ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስት የሀይል ማመንጫ ተርባይኖችን አቀርባለሁ ብሎ ባለመቻሉ ስራው ለጀርመኑ ቮይስ ኩባንያ መሰጠቱ የሚታወቅ ነው።
ሀይ ቴክ የተሰኘውና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እንዲያመርት የሚጠበቀው ኢንዱስትሪም ያለቀለት ቴሌቭዥን ሲያመጣ የቆየ ነው።ይህ ኢንዱስትሪ 47 የውጭ ግዥ እንዲፈጽም ምንዛሬን ሲጠቀም ነበር፤ ቴሌቭዥንና መለዋወጫዎችን ለማምጣት ።
የአዳማው አግሪካልቸራል ማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪም የትራክተር አስመጪ እንጂ አምራች አይደለም።በቅጡም አይገጣጥምም። 179 የውጭ ሀገር ግዥን በሚሊዮን ዶላሮች የፈጸመው ይህ ኢንዱስትሪም ታሪኩ ከሌሎች የሜቴክ ኢንዱስትሪዎች ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሜቴክ በኢትዮጵያ የነበረው የኢኮኖሚ ተሳትፎም ከማምረት ይልቅ የብቸኛ አስመጭና አከፋፋይነት ነው ። ለዚህም በሌለ የውጭ ምንዛሬ እንደልብ ከውጭ ግዥ ሲፈጽም ቆይቷል ተብሏል።  [ዝርዝር የሜቴክን የግዥ ሂሳብ ዝርዝር እዚህ  ይመልከቱ። Wazema Radio METEC Transactions ]

————

ማስታወሻ፤
ይህ ዜና መጀመሪያ ከታተመ በኋላ አነስተኛ የሰዋሰውና የቋንቋ ማስተካከያ ተደርጎበታል። በተጨማሪም የደረሰን የውጭ ግዥ ዝርዝር ትክክለኛ ቢሆንም ሁሉንም የሜቴክን ግዢዎች የሚካታት ይሁን አይሁን ለጊዜው ለማረጋገጥ አለመቻላችንን የሚያሳይ ዓረፍተ ነገር ጨምረናል።

Comments are closed.