Take a fresh look at your lifestyle.

ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን በተመለከተ ከኢሕአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

426

 

ድርጅታችን ኢሕአዴግ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል በማስተባበር ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለ ድርጅት ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሀገራችንን ሕዝቦችና የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶችን ለቅሬታና ለምሬት የዳረጉ ጥፋቶች በአመራር ዘመኑ እንደተፈጸሙ አበክሮ ይገነዘባል። ለተከታታይ አመታት የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችን በማካሄድ የችግሮቹን ምንጭና መፍትሄዎች ለመለየት ሲሰራ የቆየውም ከዚሁ በመነሳት ነው።

ድርጅታችን ቁልፍ የሆነው ችግር መንግስታዊና የፓርቲ ስልጣንን ለህብረተሰባዊ ለውጥ ከማዋል ይልቅ የግል ጥቅምን ለማካበት የማዋል ፍላጎትና ተግባር መሆኑን በጥልቅ ተሃድሶው ግምገማ መለየቱ ይታወሳል። አሁን ከደረስንበት ለውጥ በመነሳት የህዝባችን ቅሬታ በዚህ መልኩ ምላሽ ሳያገኝ እንዲቆይ ማድረግ የሚቻልበት አንዳችም መንገድ እንደሌለ የተረዳው ድርጅታችን ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት ስር ነቀል የአመራርና የአሰራር ለውጥና ማሻሻያዎች አድርጓል። የለውጥ ጊዜው አጭር ቢሆንም በስፋቱና በጥልቀቱ ግን በሀገራችን ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው። አሁንም የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ዘላቂነት ከማረጋገጥ ጎን ለውጡ ተቋማዊ እንዲሆን ማድረግ የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት በድርጅታችን እየተፈፀመ ያለ ተግባር ሆኗል።

ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታና እሮሮ ከሚሰማባቸው ውስጥ ሀገራዊ የፍትህ ስርዓቱ በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ሌብነትና ብልሹ አሰራር ሊያስቆም አለመቻሉ ይገኝበታል። የዚህ ዘርፍ ዋነኛ ተልዕኮ ህገ ወጥነትን መከላከልና ሲፈፀምም ህጉን ተከትሎ የእርምት እርምጃ መውሰድ ቢሆንም በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የተደራጁ ሃይሎች በተሰጣቸው ሃላፊነት ልክ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ከማስቆም ይልቅ ራሳቸውን የህገ ወጦች ፍላጎት ማስፈፀሚያ መሳሪያ በማድረግ በሀገርና በህዝቦቿ ላይ በደል ሲፈፅሙ ቆይተዋል። የሀገራችንን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዱ አሻጥሮች ሲፈፀሙ፣ የዜጎችና የቡድኖች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በግላጭ ሲጣሱ እንዲሁም መንግስታዊ ስልጣን ለሽብር ተግባር ማስፈፀሚያ ሲውል ቆይቷል።

ከዚህ በመነሳት ድርጅታችንና መንግስት በዚህ ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ በማመን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በርካታ ጥናት ሲያደርጉና ርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል። በቅርቡም የተሰጣቸውን መንግስታዊና ህዝባዊ ሃላፊነት ወደጎን በመተውና ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ በአስከፊ የምዝበራ፣ የሰብዓዊ ጥሰትና የሽብር ተግባር ስለመሳተፋቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ህጋዊ መንገዱን በመከተል በቁጥጥር ስር ውለዋል። ከድርጅታችን ህዝባዊ ባህሪ በማይመነጭና ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አላማዎቻችን ፍፁም በተፃራሪ ድርጊቶች የተሰማሩ ግለሰቦችንና ግብረ አበሮቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

መላ የድርጅታችን አመራሮችና አባላት እንዲሁም የሀገራችን ህዝቦች በዚህ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ከመንግስት ጎን ቆመው ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኢሕአዴግ ጥሪውን ያስተላልፋል።

ህዳር 05/2011 ዓ.ም
የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት

Comments are closed.