Take a fresh look at your lifestyle.

ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሠጠ መግለጫ

479

በሃገራችን በህዝቦች ትግል የተገኘው የለውጥ ፍሬ ማፍራቱን ቀጥሏል፡፡ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለውጡን እንደ ሚደግፍ እና ዳር እንዲደርስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር፡፡

አሁን ላይ የሚታዩት ተጨባጭ የለውጥ ተግባራት በህዝብ ተጀምሮ በድርጅት በተቀጣጠለው ሃይል የመጣ ውጤት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ይህን ለውጥ ለመቀልበስ የሞት ሽረት ትግል የሚያደርግ የደባል የኢክኖሚ አቅም የገነባ ሃይል ቢኖርም ህዝብና መንግስት አንድ በመሆን ትግሉን በመግፋታቸው ማደናቀፍ ሊሣካ አልቻለም፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ አጓጊና ለሃገራችን ትልቅ ተስፋ ያለውን ለውጥ መጠበቅ ከህዝባችን ይጠበቃል፡፡

ለህግ የበላይነት ሁሉም ግድ ሊለው ይገባል፡፡ መንግስት በሰከነ መንገድ መረጃዎችን በማሰባሰብና በማስረጃ በመደገፍ ይህች ተስፋ ያላት ሃገር ሲደርስባት የነበረውን የሌብነትና ሃገር የማራቆት ተግባር ለማስቆም የሄደበት በሳልነት የተሞላበት አመርቂ መንገድን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በእጅጉ ያደንቃል፡፡

በዜጐች ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሠቦች ለህግ እንዲቀርቡ የተወሰደውን እርምጃ የክልላችን መንግሰት የሚደግፍ ሲሆን በተጨማሪም የሚጠበቅበትን ማንኛውንም ህጋዊ ተግባር ለመፈፀም ዝግጁ መሆኑን ይገልፃል፡፡

ሌብነትና ኢ-ሠብአዊ ድርጊት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች የትኛውንም ብሄር አይወኩሉም ፡፡ እነዚህ አካላት ውክልናቸው ለራሳቸው እና ለጥቅም አጋሮቻቸው ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የህዝብ ሀብት ከድሃ ጉሮሮ የነጠቁ ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር የመዋላቸው ምክንያት ሌብነትና ኢ-ሰብአዊነት የጐደው ተግባራቸው እንጂ የትኛውም ህዝብ መገለጫ ሆኖ ሊወሠድ አይገባውም፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እያከናወነ ባለው ተግባር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሰት ያለውን ድጋፍ እየገለፀ ይህ ትግል ውጤታማ እንዲሆን ህገ መንግስታዊ ግዴታቸውንና የህዝብ አደራ በትጋት የተወጡ አካላት በተለይም የፀጥታው መዋቅር እያደረገ ያለውን ጥረት የክልላችን መንግስትና ህዝብ ያደንቃል፡፡

በቀጣይም ይህን የህግ የበላይነት እና ፍትህን ለማስከበር በሚደረገውን ማንኛውም እንቅስቃሴ ዳር ለማድረስ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ በቁርጠኝነት እንደሚሠለፍ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

የህግ የበላይነትን በማስከበር የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል ርብርብ እናደርጋለን!!!
ህዳር 5/2ዐ11 ዓ/ም
ባ/ዳር

Comments are closed.