Take a fresh look at your lifestyle.

የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የቀረበው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑ ተገለጸ ።

299

 

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሰሞኑን በግብፅ የመገናኛ ብዙሃን የቀረቡ መረጃዎች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን የግድቡ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሚታተመው ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ሰሞኑን የግብፁ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የቴክኖሎጂ ደረጃ አስተማማኝ ያልሆነና አካባቢውም የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሚያሰጋው መሆኑን ያቀረበው መረጃ ከእውነት የራቀና ውሸት ነው።

እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ገለጻ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሎ ከሚታሰቡ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በረጅም ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ እስከአሁን ባለው መረጃም የአደጋ ምልክት አለመኖሩን ጠቁመዋል። የግድቡ ዲዛይንም በጥንቃቄ መዘጋጀቱንና የግብፅ ባለሙያዎችን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን መረጋገጡን አስረድተዋል።

በጋዜጣው ላይ የተጠቀሰው «በግንባታው ወቅት ሁለት ጊዜ የመፍረስ አደጋ አጋጥሟል» የሚለው ሪፖርትም ከእውነት የራቀና ግድቡ እስከአሁን ውሃ መያዝ አለመጀመሩን ኢንጂነር ክፍሌ ተናግረዋል። የዚህ ዓይነቱ የግብፅ ሚዲያ ዘገባ ሆነ ተብሎ መደናገርን ለመፍጠር እንደሆነ የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ይህም በፕሮጀክቱ ላይ በዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ዘንድ የተዛባ ገጽታን ለመፍጠር ታስቦ የተሠራ እንደሆነ አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ግድቡን ለተዛባ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ጠቁመዋል። ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድንም የግድቡን ደህንነት ማረጋገጡን ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል። የግድቡ የመካኒካል ሥራዎች ግንባታ ሂደት ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መሰጠቱንና በመንግሥት በኩልም እንዳይዘገይ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥትም የግንባታ ሂደቱ እንዳይዘገይ የተለያዩ የማስተካከያ ዕርምጃዎችን መውሰዱንና ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደተቀመጡ አብራርተዋል።

የምሥራቅ ናይል አካባቢ ቴክኒካል ጽህፈት ቤት (ENTRO) ዋና ዳይሬክተር ፈቅአህመድ ነጋሽ በበኩላቸው ግብፅ ግድብ የሠራችው ከአርባ ዓመት በፊት አስዋንን በገነባችበት ወቅት መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በቂ ልምድ እንደሌላቸው ጠቁመዋል።

በጋዜጣው የተጠቀሰው መረጃም በግንባታው ሂደት ያልታየና ከባዶ ስሜት የመነጨ የፈጠራ ወሬ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ ግድቡን ለጎርፍ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል የሚለው ዘገባ ሱዳንን ስጋት ውስጥ ለመክተትና የራሳቸው ፍላጎት አጋር ለማድረግ ታልሞ የተጻፈ ነው ብለዋል።

ግድቡ ከስምጥ ሸለቆ 800ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ምንም ዓይነት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እንደማያሰጋው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ህዳር 3 ቀን 2011 ዓም

Comments are closed.