Take a fresh look at your lifestyle.

በዛሬው የጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫ ያልተጠቀሱት የሜቴክ አስገራሚ ጉዶች

720

በዚህ ፅሁፍ በተለያየ ወቅት በሜቴክ ዙሪያ ከሰራናቸው  ዘገባዎች መሃል ሶስቱን ብቻ እንዳስሳለን  ።

ቁጥር 1 ፡ የድንጋይ ከሰል ንግድ በያዬ ማዳበሪያ ፋብሪካ 

ነገሩ ከተበላሸ በኋላ በቅርቡ  የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት አሁን ለማንሳት ያሰብነው የማዳበሪያ ፋብሪካ ወደሚገነባበት ስፍራ ሄደው ነበር ። ከዚያም   በጉብኝቱ ወቅት ያልጠበቁትን ነገር ተመልክተው የመጡት አባላት ለምክር ቤቱ እንዲህ አሉ
* ገና ተሰርቶ ሳያልቅ
* የፋብሪካው የድጋፍ ግንብ ስድስት መቶ ሜትር ( ከግማሽ ኪሎ ሜትር በላይ ) ተሰንጥቋል ።
* ትልቁ ኩሊንግ ታወር እየሰመጠ ነው ፣ በተጨማሪም
* ፕሮጀክቱ በተመረጠበት አካባቢ ረዥም የመሬት መሰንጠቅ መኖሩን በስፍራው ተገኝተን ባደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል ሲሉ ቢናገሩም ሰሚ ግን አልነበረም ።

…………………………………..
ያዬ ቁጥር አንድ የማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ ታሪክ ሲጀምር ፕሮጀክቱን ለመስጠት የታሰበው በሙያው የብዙ አመት ልምድ ላለው ለአንድ የቻይና ኩባንያ ነበር ። ይህ የቻይና ኩባንያ የማዳበሪያ ፋብሪካውን በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሰርቶ እንደሚያዝጠናቅቅ ለዚህም 600 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልፆ ውሉ ተፈፀመ ። ሆኖም ሜቴክ ይህ ፕሮጀክት መሰጠት ያለበት ለእሱ እንደሆነ ግፊት በማሳደሩ ውል ከፈፀመው የቻይና ኩባንያ ተነጥቆ በ 11 ቢሊየን ብር እንዲገነባና በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሰርቶ እንዲያስረክብ ለሜቴክ ተሰጠው ።
ሆኖም ሜቴክ ይህን የማዳበሪያ ፋብሪካ በሁለት አመታት ሰርቼ አጠናቅቃለሁ ቢልም በስድስት አመትም ሊያልቅ አልቻለም ። በነዚህ ስድስት አመታት ውስጥም የፋብሪካው ግንባታ ከ44 % በላይ ሊሄድ ካለመቻሉም በላይ ሜቴክ ይህን የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ሲዋዋል የጠየቀው 11 ቢሊየን ብር ሆኖ ሳለ የተዋዋለውን ቃል በማጠፍ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ዘጠኝ ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልገው አስታወቀ ።
ይህም ማለት የፋብሪካውን ወጪ ከ ሃያ ቢሊየን ብር በላይ ያደርሰዋል ። የዚህ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በዚህ ሁኔታ ላይ ያለ ቢሆንም ሜቴክ እስካሁን 60 % የሚሆነው ገንዘብ ተከፍሎታል ።
የያዪ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጣጣ ይህ ብቻ አይደለም ። ለዚህ ፋብሪካ መስሪያ የሚሆን ገንዘብ ላበደሩ ባንኮች እስከዛሬዋ ቀን ድረስ በየቀኑ ወደ ሶስት ሚሊየን ብር ወለድ የሚከፈል ሲሆን በዚህም መሰረት በወር ዘጠና ሚሊየን ብር እየተከፈለ ይገኛል ።
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነገር በዚህ አያበቃም ።
የሜቴክ ስራ በውሉ መሰረት የፋብሪካውን ግንባታ አጠናቆ ማስረከብ ብቻ ሆኖ ሳለ የማዳበሪያ ፋብሪካ የመገንባቱን ስራ ችላ ብሎ ፡ ፋብሪካው በሚገነባበት ቦታ ያለውን የድንጋይ ከሰል እያወጣ በመሸጥ ከውሉ አላማ ውጭ መንቀሳቀሱ በቋሚ ኮሚቴ አባላት ጉብኝት ቢረጋገጥም ምንም አይነት የእርምት እርምጃ ሳይወስድ ቆይቷል ።
ሜቴክ በሁለት አመት አጠናቅቃለሁ ብሎ እስካሁን 44% ብቻ በሰራው ይህ ማዳበሪያ ፋብሪካ እስካሁን ካለመጠናቀቁም በተጨማሪ የተሰራው ስራም ጥራቱ የወረደ መሆኑን የተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት በመስክ ጉብኝታቸው ያዩትን ሲገልፁ
* የፋብሪካው የድጋፍ ግንብ ስድስት መቶ ሜትር ያህል ተሰንጥቋል ።
* የኩሊንግታወሩ እየሰመጠ መሆኑንና
* ግንባታው በተመረጠበት አካባቢ ረዥም የመሬት መሰንጠቅ መኖሩን በስፍራው ተገኝተን ባደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል በማለት ለምክር ቤቱ አስታውቀው ቢሆንም ከሳሽና ወቃሽ የሌለው ሜቴክ እስካሁን ድረስ ለችግሩ ምንም አይነት የእርምት እርምጃ ሳይወስድ ቆይቷል ።

ቁጥር ሁለት ፡ ባቡር ወዲያ ማዶ ሃዲድ ወዲህ ማዶ 

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሃዲድ የማንጠፍ ስራ ወደመጠናቀቁ በተቃረበበት ሰአት ላይ ሜቴክና የምድር ባቡር ድርጅት ሃይለኛ ውዝግብ ውስጥ ገቡ ።
የውዝግቡ መነሻ ሜቴክ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የሚሆኑ ሰው ማጓጓዣ ፉርጎዎችን ማምረት ያለብኝ እኔ ነኝ አለ ። ምድር ባቡር ደግሞ እነዚህ ሰው ማጓጓዣ የከተማ ባቡሮች ኢንተርናሽናል ደረጃቸውን የጠበቁና የሰው ማመላለሻ ፉርጎዎችን በመስራት ልምድ ባለው ድርጅት ነው መሰራት ያለበት ። ስለዚህ እነዚህን ፉርጎዎች አለም አቀፍ እውቅና ካለው የቻይና ኩባንያ አዝዣለሁ በሚል የተነሳ ውዝግብ ነበር ። አለመግባባቱ እየጠነከረ መጣና ሜቴክና ምድር ባቡር ድርድር ተቀመጡ ። ከዛም ሜቴክ ለናሙና የሚሆኑ የተወሰኑ የህዝብ ማመላለሻ ፉርጎዎችን ሰርቶ እንዲያቀርብ ። ከቻይና የታዘዙትም ፉርጎዎች እንዲገቡ ስምምነት ተደረሰ ።
ለሜቴክ የተወሰነ ብር ተገባለት እዚህ አዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ወርክ ሾፕ ፡ ብረት እየተቆረጠ ላሜራ እየተሰነጠቀ ዘመናዊ ህዝብ ማመላለሻ የባቡር ፉርጎ ለመስራት ስራ ተጀመረ ።
• ልብ በሉ ሜቴክ ከዚህ በፊት አንድም የባቡር ፉርጎ ሰርቶ አያውቅም ።
• በዚህ መስክ የተሰማራም ሰራተኛ አላሰለጠነም ።
እናስ ? …… እናማ በገገማ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የሚሆኑ ተጎታች ባቡሮች ለማምረት የተጀመረው ስራ ተጠናቆ የመጀመሪያዎቹ ፉርጎዎች ሜክሲኮ ከሚገኘው ወርክ ሾፕ ተጭነው ወደ ምድር ባቡር ግቢ ሄደው በረዥሙ ሃዲድ ላይ ተገጥመው ሙከራ ሊደረግባቸው ዝግጁ ሆኑ ………….. አሁን የቀረው ባቡሮቹን ሃዲዱ ላይ ማስቀመጥ ነውና ስራ ተጀመረ ። ቢባል ቢባል የባቡር ፉርጎዎቹ የብረት ጎማ ከሃዲዱ ጋር እንዴት ይግጠም …….. የተሰራው ፉርጎ ስፋትና የሃዲዱ ስፋት ፈፅሞ አይገናኝም ።
ሜቴክ ቀላል ባቡሮቹን እንደመኪና አስቦ ያለሃዲድ ሊያስኬዳቸው ፈልጎ ይሁን .. ምን ይሁን አልታወቀም ብቻ ሃዲድ እዛ ፉርጎ እዚ ሆነና አረፈው ። የባቡር ሃዲድም ሆነ የተጎታች ፉርጎዎች ስፋት ማንም እንደፈለገው የሚያጠበውና የሚያሰፋው ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀ ወጥ የሆነ ስታንዳርድ የሚሰራ በመሆኑ ሜቴክ እንደዚህ አይነት ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ ስህተት መስራቱ በጉዳዩ ዙሪያ በነበሩ ሰራተኞች ከፍተኛ ግርምትን ፈጠረ ።
በፉርጎዎቹ ላይ የነበረው ሌላው መሰረታዊ ችግር ይሄ ብቻ አልነበረም ። እንደው እድል ቀንቶት ፉርጎዎቹና ሃዲዱ ተገጣጥመውለት ቢሆንም ኖሮ ባቡሮቹ ግልጋሎት መስጠት አይችሉም ነበር ምክንያቱም ዛሬ ከተማችን ውስጥ ያሉት የባቡር ፉርጎዎች እንደምናያቸው በግራና በቀኝ ግድግዳቸው ላይ ሁለት አውቶማቲክ በር የተገጠመላቸው ሲሆኑ ሜቴክ ፉርጎዎቹን እንደ አውቶቡስ አስቧቸው ነው መሰል በር ሰርቶ ያመጣው በአንድ በኩል ብቻ ነበር በነዚህ መሰረታዊ ችግሮች ምክንያት ሜቴክ ለፉርጎዎቹ መስሪያ የወሰደው ብር ባክኖ ዛሬ የምናያቸው የከተማ የባቡር ፉርጎዎች ሙሉ ለሙሉ ከቻይና መጡ ። የሜቴክ እየሰራን እንማራለን ፡ እየተማርን እንሰራለን መርህ ያልገባበት ቦታ አልነበረም ።

ቁጥር ሶስት
ሜቴክና አስራ ሁለት ሺህ ዛፍ ቆራጮች

በዚህ በፎቶው ላይ በሚታየው ማሽን አንድን ዛፍ ቆርጦ ቅርንጫፉን መልምሎ ለአጫጫን እንዲመች አድርጎ ለማዘጋጀት የሚፈጀው ጊዜ ሶስት ደቂቃ ብቻ ነው እናም ይህን ማሽን አስራ ሁለት ሺህ መጥረቢያዎችን ይዘው ጫካ ከገቡ ሰወች ጋር እያነፃፀራችሁ ከስር ያለውን ጽሁፍ እዩት

የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚተኛበት ከአዲስ አበባ ዝዋይ የሚያክል ቦታ በደን የተሸፈነ በመሆኑ በዚህ ስፍራ ላይ ያለውን ትላልቅ ዛፎች ያሉበት ደን ለመመንጠር ሜቴክ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ያደርጋል ። ለዚህ ስራም ሜቴክ የጠየቀው ሁለት ቢሊየን ብር ይከፈለዋል ።
1 ) ሜቴክ በእስከዛሬው የስራ ሂደት ስራ በማጓተትና መሰል ችግሮች ምክንያት ጥሩ ስም እንደሌለው እየታወቀ ይህን ስራ ለሱ መስጠት ለምን አስፈለገ ? ለሌሎች ካምፓኒዎች መስጠት አይቻልም ነበር ? ይቻል ነበር ነገር ግን በስኳር ፡ በማዳበሪያ ፡ በህዳሴ ግድብ ላይና በሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች ላይ ቢዚ የሆነውን ሜቴክን ተጨማሪ የደን ምንጣሮ ስራ ሰጥቶ ገንዘቡ ባክኖ እንዲቀር ማድረግ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽንንም ተጠያቂ ያደርገዋል ። ኮርፖሬሽኑ ህግና ስርአት ባለበት ሃገር ከሜቴክ ጋር ሲዋዋል ልክ ስራው እንደተጠናቀቀ ተደርጎ 100% ክፍያ ለሜቴክ በመፈፀሙም ከተጠያቂነት አያድነውም ።
ሜቴክ ይህን ስራ ከተቀበለ በኋላ ያደረገው ልክ ስራና ሰራተኛን እንደሚያገናኝ ደላላ ሆኖ ስራውን የሰጠው ለሌሎች ሰወች ነበር ። እነዚህም ሰወች ከስራው ትልቅነት የተነሳ ስራውን በቀላሉ መስራት እንደማይችሉ ሲያውቁ በማህበራት ለተደራጁ ሰወች ስራውን ሰጥተው ያንን ግዙፍ ዛፎች ያሉበትን ትልቅ ደን አስራ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በሺህ የሚቆጠሩ ባህላዊ መጥረቢያዎች ገዝተው ፡ ያንን ችምችም ያለ ደን ቆርጦ ለመጨረስ ስራ ጀመሩ ። ይሄ እጅግ አስገራሚ ነገር ነበር አንድ ወፍራም የጫካ ዛፍ ለመቁረጥ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል ? ይህ ማሽን ታይገር ካት ይባላል ዋጋው 700 ሺህ ዶላር ሲሆን በተለያየ መልክአ ምድር የበቀሉ ግዙፍ ዛፎችን ቆርጦ ቅርንጫፉን መልምሎ ለአጫጫን እንዲመች አድርጎ ይቆራርጥና ደርድሮ ያስቀምጣል ። ለዚህ የሚያስፈልገው ጊዜ ደግሞ ዛፉን ለመቁረጥ አንድ ደቂቃ ለሌሎቹ ስራዎች ደግሞ ሁለት ደቂቃ ብቻ ይወስድበታል ። ሜቴክ ይህን ስራ ሲወስድ በዚህ መሳይ ማሽኖች ለመስራት ካልሆነ በምን መልኩ እሰራዋለሁ ብሎ እንደነበር ራሱ አስገራሚ ነው ። መሆን የነበረበት ይህን መሳይ አስር ሃያ ማሽኖች ተገዝተው በዘመናዊ መልኩ ጊዜም ሆነ ገንዘብ ሳይጠፋ ስራውን አጠናቆ መስጠት ሲቻል ሜቴክ የመረጠው ግን እጅግ ኋላቀር የሆነ መንገድ ነበር ። ያም ሆነ ይህ አስራ ሁለት ሺህ ወጣቶች በሺህ የሚቆጠሩ ባህላዊ መጥረቢያ ይዘው ያን ግዙፍ ደን ለመቁረጥ እየጣሩ ወራት አልፈው አመታት ተተክተዋል ። ይህ ደን ተመንጥሮ አልቆ እንደሆን የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ገንዘቡ ግን ሳይጠፋ አልቀረም የሚል ነገር ከሰማን ሰንበትበት ብለናል ። አሳዛኙ ነገር ይህን ስራ ለመስራት ውል የወሰዱትም ሆነ የጉልበት ሰራተኞች ሆነው ለወራት ድንኳን ተክለው በጫካ እያደሩ በእባብ እየተነደፉ ስራውን የሰሩትም ሰወች ተገቢውን ክፍያ አለማግኘታቸው ነው ። ምነው ከተባለ ሜቴክ ገንዘቡን ጨርሶታል ።፡ ወይም በለመድነው ቋንቋ ገንዘቡ ሳይባክንበት አልቀረም ።
በጠ/አቃቤ ህግ ያልተጠቀሱ የሜቴክ ጉዶች እነዚህ ብቻ አይደሉም ይቀጥላል  (  wasihune tesfaye )

 

Comments are closed.