Take a fresh look at your lifestyle.

በሁለት ኤምባሲዎች በኩል 30 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የገቢዎች ሚኒስቴር ተናገረ፡፡

158

 

በተለያዩ ስምምነቶች መሰረት ከዚህ ቀደም ኤምባሲዎች የሚያስገቡት እቃ እንደማይፈተሽ ይታወቃል፡፡ አሁን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በምን ምክንያት ፈትሾ በሚሊዮን ብሮች የተገመተውን ህገወጥ እቃ ይዣለሁ ሊል ቻለ ? ስንል የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩን አቶ ኤፍሬም መኮንንን ጠይቀናቸዋል፡፡ አቶ ኤፍሬም እንዳሉት በኤምባሲ ስም 20 ሚሊዮን ብር የተገመተ ህገወጥ እቃ በአንድ ኤምባሲ አማካይነት የገባው ባለፈው መስከረም ወር ነበር፡፡

በጥቅምት ወር ደግሞ ሌላ ኤምባሲ 10 ሚሊዮን ብር የተገመተ ሌላ ህገወጥ የመኪና መለዋወጫዎች፣ ካሜራና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን አስገብተው ደርሰንባቸዋል ብለዋል፡፡ በስምምነቱ መሰረት የኤምባሲ እቃዎችን ለመፈተሽ ባንችልም በተለያዩ ምክንያቶች ጥርጣሬ ስለገባን እቃዎቹን መከታተል ጀመረን ይላሉ አቶ ኤፍሬም፡፡ በተደረገው ክትትልም እቃዎቹ ወደ ኤምባሲው ሳይሆን ወደ ሌላ መጋዘን እንደገቡ ደርሰንበታል፡፡

በዚህም ምክንያት የእቃው ባለቤት ለሆኑ ኤምባሲዎችና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቀን እነሱም ባሉበት የመፈተሽ ስራ ሰርተናል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም 30 ሚሊዮን ብር የተገመተውን ህገወጥ እቃ ከሁለት ኤምባሲዎች ይዘናል እቃዎቹንም መንግስት ወርሷል ብለዋል፡፡ ህገወጥ ስራ ሰርተዋል የተባሉት ኤምባሲዎችን ስም ግን ሊነግሩን አልፈቀዱም፡፡ ይሁንና ከእንዲህ ካለ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጋር ይነጋገሩበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

SHEGER FM 102.1 RADIO

Comments are closed.