Take a fresh look at your lifestyle.

“ያለምኩት ነገር በሃገሬ ላያ ተሳክቶ ማየት እፈልጋለሁ” ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ( ከአዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ጋር ያደረገችው ሙሉ ቃለ ምልልስ )

198

 

ብርቱካን ሚደቅሳ እጅግ በተጣበበ የእንቅልፍና የእንግዳ ቅበላ ውጥረቷ መሃል በተለይ ለ”አዲስ ዘይቤ” ጋዜጣ ፀኃፊ ዳዊት ተስፋዬ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች። እነሆ ሙሉ ቃለ ምልልሱ!

አዲስ ዘይቤ፡ እንኳን ደህና መጣሽ፣ እንኳን ለሀገሽ አበቃሽ!

ብርቱካን ሚደቅሳ፡ አመሰግናለሁ! እንኳን ደህና ቆያችሁኝ።

ስምንት ዓመታት ገደማ የሆነው የውጪ ሀገራት ቆይታሽ እንዴት ታለፈ?

የውጭ ሀገር ቆይታዬ ከባድ ጎኖች ነበሩት። ከባድ ያደረገው ዋናው ነገር እኔ አቅጄ ፈልጌ የሄድኩበት ሁኔታ ስላልነበረ፣ እሰራው ከነበረው የፓርቲ አመራርነት፣ በእስርና በእንግልት ሁኔታ ተገፍቼ ከሀገሬ ስለወጣሁ በጣም ከባድ ነበረ። በዚህ ምክንያት ከዛ ሀሳብ ጋር እራሴን ማስማማቱ ከባድነት ነበረው። ከዛ ውጪ ግን ጊዜውን ጥሩ ተጠቅሜበታለሁ። ብዙ የጥናት ሥራዎችን በተለያዩ የትምህርት ተቋማቶች ውስጥ ለመሥራት ዕድል ሰጥቶኝ ነበር፤ በተጨማሪም ሁለተኛ ዲግሪዬንም ለመሥራት ዕድል ሰጥቶኝ ነበር። እና እሱ እሱ ያለኝን የሥራ ልምድም በተሻለ የዕውቀት ሆኔታ ውስጥ ሆኖ እንደገና ከራስ ጋር ለመነጋገር፣ እንደገና ለማሰብ፤ ምንድናቸው ችግሮቻችን? ወደፊትስ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምንድናቸው? የሚሉትን ለማብሰልሰልና ለመረዳት በጣም ጥሩ ጊዜ ነበረ። ከዛ ውጪ ደግሞ ያው በዋናነት እናት ነኝ፣ ልጅ አሳዳጊ ነኝና እሱ በጣም ጥሩ ነበር፤ ልጄ ጥሩ ተማሪ ነች። እሱም ቢሆን ግን ተግዳሮቶች ነበሩት። እኔ ያደግኩበት ሁኔታ፣ የባሕል ሁኔታ ሌላ ነው። ያኛው ደግሞ እራሱን የቻለ አዳዲስ ነገሮች አሉት። እሱ ዋናው ነገር ነበር በሕይወቴ። ያው ልጄም ዓይኔ እያየ በአእምሮም፣ በሰውነትም ስታድግ ማየት በጣም መልካም ነገር ነበረ። እንዲህ ነው እንግዲህ ያለፈው።

ያንቺ የፖለቲካ ጎዞ ሲታይ፣ ያሳለፍሻቸው መከራዎችም ሲታወሱ ቂምም ፀፀትም ሊፈጥሩ የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ። ቂምና ፀፀት አለብሽ ወይ?

ብርቱካን፡ በረጅሙ ተንፍሳ “እኔ በፖለቲካም፣ ሕይወቴንም ለመምራት ከምከተላቸው መርሆች አኳያ ቂም መያዝ አልፈልግም። በሰው ላይ ስመረር ወዲያው ነው ከውስጤ ቂም እንዲወጣ የማስበበት። እና እስር ቤትም እያለሁም እንደዚህ ዓይነት ስሜት ሲመጣ፣ ቁጣም ውስጤ ሲኖር፣ ያለሃጥያትህ ያለበደልህ ስትቀጣ እንደዛ ዓይነት ስሜት እንደሰው ይኖራል፤ ግን የራሴ ዕምነቶችና አስተሳሰቦች አሉኝ። ቂም ዞሮ ዞሬ እኔኑ እንደሚጎዳ፣ ከዚያም የማራምደውን ሀሳብም እንደሚጎዳ ስለማውቅ ከዛ ቶሎ ነው ራሴን የማወጣው። ግን ጉዳት፣ እና ሕመም አይቀርም። እሱን በውስጥህ ይዘህ ትቆያለህ። አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም አብቅቷል ስል ብዙ የሚያስታውሱኝ ነገሮች ይኖራሉ። እንግዲህ እንደምናውቀው ሌሎች ወገኖች በየቦታው፣ በየጊዜው በፖለቲካ ትግል ምክንያት፣ በሚዲያ ሥራ ምክንያት፣ በአደባባይ ወጥተው ሀሳባቸውን በመግለፃቸው ምክንያት በሀገሩ ሁሉ ሰዎች ሲታሰሩ፣ ሲገደሉ፣ ሲንገላቱ ሳይ ይመስለኛል ሌላው ዜጋ ከሚሰማው በላይ ሕመሙ ይሰማኛል። ምክንያቱም ስላለፍኩበትና በዚያ ልክ የራሴን ሕመም ቀስቅሶብኝ ግርሻ ነገር ይመጣብኛል። በተለይ ውጭ ሀገር በነበርኩበት ጊዜ እሱ የሚጎዳኝና የሚያስቸግረኝ ነገር ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ ስንደርስ ተስፋን የሚሰጡ ተግባራት እና የመቀየር ሁኔታዎች ማየት ለኔ መዳን ነው። እንጂ ከቂም ጋር የምኖር ዓይነት ሰው አይደለሁም። ለረጀም ጊዜ የቆየብኝም ሕመሙ ነው።

ፀፀትስ?

ብርቱካን፡ (ረጅም ዝምታ) እንዲሁ ባጭሩ ለመናገር ያህል የሕመም ሁኔታው፣ ስቃዩ፤ በእስር ውስጥም ስንኖር ያለው እንግልቱ፣ እንደገና ስደት እራሱ ሌላ ስቃይ አለው። ከሀገር መነጠል፣ ከወገን መነጠል፣ ከሚወዱት ሥራ መነጠል፣ እሱ ሁሉ ሁልጊዜ ስቃይ ነው። በዛ ስቃይ ውስጥም ስኖር ግን “ምነው በዚህ መንገድ ባልሄድኩ ኖሮ” የሚል ፀፀት መጥቶብኝ አያውቅም። አንድ ጊዜም፤ ድጋሚም ብኖረው እንደዚሁ ሳልኖረው አልቀርም። ምክንያቱም ይሄ መደረግ ያለበት ነገር ነበር፤ ሙከራዎቼን አልጠላቸውም። ዞሮ ዞሮ ሕይወታችን በጣም አነስተኛና አጭር ነች። የእያንዳንዳችን ሕይወት በአገር ደረጃ ያለን ችግር ለመፍታት ቀርቶ በጣም አነስተኛ በምንለው በራሳችንም ሕይወት እራሱ አርመን፣ አስተካክለን፣ አሳክተን ማለፍ የምንችላቸው ነገሮች ውሱን ናቸው። ግን በጣም የተሻለ የምንለውን፣ ወይም መልካም ነው የምንለውን ነገር ለማሳካት የምንችለውን ነገር ሁሉ ለማድረግ መሞከራችን ይመስለኛል ዋናው ነው ቁምነገሩ። ያለምኩት ነገር በሀገሬ ላይ ተሳክቶ ማየት ፈልጋለሁ ያ እንዲሆንም ሠራለሁ። ግን ለኔ ኃላፊነቴ ነው፣ ወይም ማድረግ አለብኝ ብዬ የማደርገው መሞከር የምችለውን ነገር ሁሉ ከኔ እንዲወጣ ማድረግ ነው። ሕይወት በሌላ መንገድም ሊያልቅና ሊጠፋ ይችላል። እና ከነውጣ-ውረዱ ሕይወቴን በጣም ትልቅ ዋጋ ላለው ነገር ነው የሰጠሁት፣ ያሳለፍኩት ብዬ አምናለሁ። እና ፀፀት የለብኝም።

ልትመጪ ነው የሚባለው ወሬ ከተሰማ ጀምሮ ስለምትመጪበት ምክንያት ብዙ የሹመትና የኃላፊነት መላ-ምቶችና ግምቶች ተሰምተዋል። ለምንድነው አሁን የመጣሽው?

ብርቱካን፡ (ሳቅ) ለምን አልመጣም? መጠየቅ ያለበት እኮ እሱኛው ጥያቄ ነው። (ሳቅ) ይህ የለውጥ ሒደት ከጀመረ በኋላ በጣም የሚያስደስቱ ክስተቶችና ቅጽበቶች ነበሩ። ብዙ ነገሮች ሲለወጡና ሰዉም ሲደሰት፤ ለምሣሌ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስር ቤት ሲለቀቁ የነበረውን ሁኔታ እኔም ቁጭ ብዬ በቴሌቭዥን እያየሁኝ፣ ቪዲዮዎችን እያየሁኝ የነበረኝ ፍላጎት እዚህ ሆኜ የዛ ነገር አካል መሆን ነበር። ምክንያቱም ይሄ ነገር የጓጓሁለት፣ የተሳተፍኩበት፣ የፈለግኩትም ነገር ነው። ከሕይወቴ ጋር በጣም የተቆራኘ ነገር ነው። እና ሕዝቡ መካከል ሆኜ አብሬ ነበር ማየት የምፈልገው። ሌሎችንም ነገሮች እንደዛው። አስቸጋሪ የሚባሉ ነገሮች በሚያጋጥሙበትም ግዜ ከሕዝቡ ጋር አብሬ ሆኜ፤ እንዴት እያዘነ እንዳለ፣ እንዴት መፍትሔ ለማበጀት እየሞከረ እንደሆነ ሁሉ በቅርብ ሆኜ አብሬ ማድረግ ነው የምፈልገው። እና ገና ከመነሻው እያሰብኩበት ነው የቆየሁት። እንዲያውም የቤተሰብ ኃላፊነት፣ የልጄም ትምህርትም ሁኔታ፣ ሌሎችም ሌሎችም ነገሮች አቆዩኝ እንጂ ተመልሼ እንጂ ከመጀመሪያው ነው እማስበው የነበረው። ግን አሁን በደረስንበት ሁኔታ የተጀመረው ለውጥ ወደኋላ እንዳይመለስ፣ የባሰ ችግር ውስጥ እንዳንወድቅ፣ የምንፈልጋቸውን የዴሞክራያሳዊ ሥርዓት ግንባታም ቢሆን፣ የኢኮኖሚ መሻሻል ቢሆን፣ የሕግ የበላይነትና የመሳሰሉት ነገሮች ቢሆን፤ ሀገራችንን የተደላደለ ሁኔታ ላይ ለማምጣት አሁን በተለይ የደረስንበት ቦታ ሆነን ሳየው የሚያስፈልጉ ዋና ነገሮች ተቋሞቻችን በትክክል የሚሠሩ፣ የሙያ ግዴታቸውን በሚወጡ ሰዎች የተሞሉ፣ ተቋማዊ ብቃትና ጥንካሬ ያላቸው፣ ነፃነታቸው የተጠበቀ ሆኖ፣ በተለይ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ መደራጀት እንዳለባቸውና፣ እንዳውም በዋናነት እሱን ካላደረግን ችግር ላይ እንደምንወድቅ በፊትም የማውቀው ነገር ነው። አሁን ደግሞ አስፈላጊነቱ እየጎላ መጥቷል። እኔ በእንደዚህ ያሉት ሒደቶች የተወሰኑ ላደርጋቸው የምችላቸው ነገሮች እንዳሉ ስለማውቅ አስፈላጊነቱ እየጎላ ሲመጣ አሁን መጥቻለሁ። ግን ገና ከመነሻውም መምጣት እፈልግ ነበር።

የምርጫ ቦርድ ሊቀ-መንበር ልትሆኚ ነው?

ብርቱካን፡ (ረጅም ሳቅና ዝምታ) ለሱ ጥያቄ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ መልስ ልሰጥ አልችልም። ምክንያቱም አሁን ምን እንደምሠራ በእርግጠኝነት ያወቅኩት ነገር ስለሌለ።

Comments are closed.