የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ውስጥ በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት ጣቢያው ለሁለት እንደተከፈለ ከኢሳት አባላት የደረሰን ዜና ያመለክታል ። ከዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ የመጣውን የለውጥ መንፈስ በሚደግፉት በነአበበ ገላውና ዶክተር አብይን መቃወም በጀመሩት በኢሳት ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር አቶ ግሩም ይልማ ፣ ሃብታሙ አያሌው ርእዮት አለሙ .እና በሌሎች መካከል በተፈጠረው የአመለካከት ልዩነት መሃከል የተፈጠረው ግጭት ለኢሳት ለሁለት መከፈል ምክንያት እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።
በዚህም ምክንያት ላለፉት አመታት ኢሳትን በበላይ አመራርነት ሲመራ የቆየው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የመልቀቂያ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን በምትኩም አቶ ግሩም ይልማ በቦታው እንደሚቀመጥ ለማወቅ ተችሏል . በዚህ አለመግባባትና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የፋይናንስና የአስተዳደር አቅሙ የተዳከመው ኢሳት ለህልውናው አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱና በቅርቡ በአዲስ አበባ ወደተከፈተውና እየተጠናከረ ወደ መጣው የአዲስ አበባ ቢሮ ሊጠቃለል እንደሚችል ያላቸውን ግምት ገልጸውልናል ..ይህን አለመግባባት ተከትሎ የጣቢያው መደበኛ ፕሮግራሞች መታጠፍ መጀመራቸውና እለታዊ አዲስ የተባለው ፕሮግራምም መቋረጡ የታወቀ ሲሆን በአዲስ አበባ ያለው የኢሳት ስታፍ ይህን የተፈጠረ ልዩነት ለመሸምገል ቢሞክርም ክፍተቱ የሰፋ በመሆኑ ኢሳትን በቋሚነት የሚረዱት ደጋፊዎች በጣቢያው ተስፋ እየቆረጡ መሆኑ ታውቋል ።
በሌላ በኩል ለጣቢያው መልቀቂያውን ያቀረበው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የራሱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመክፈት ሃሳብ እንዳለው የደረሰን መረጃ ያመለክታል ።
Comments are closed.