Take a fresh look at your lifestyle.

ፍርድ ቤቱ የሶማሌ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ላይ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

142

 

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት ነው አቶ አብዲ መሃመድ ዑመር ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈቀደው።

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ችሎት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ላይ የ10 ቀን ምርመራ ጊዜ መፍቀዱ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት መርማሪ ፖሊስ ከሃምሌ 26 ቀን እስከ 30 ቀን 2010 ዓ/ም በሶማሌ ክልልና በአካባቢው በተፈጸመው ወንጀል ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ 30 ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች የህክምና ማስረጃ ማሰባሰቡን፣ የ62 ሰዎች የጉዳት መጠንን ማስረጃ በአማርኛ ማስተርጎሙን ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።

በተጨማሪም ለሄጎ ቡድን ለወንጀሉ መፈጸሚያ የዋለውን ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣ የገንዘብ መጠን እና የገንዘቡ 16 ገጽ የኦዲት ማስረጃ ማምጣቱን እና በንግድ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚገልጽ 35 ገጽ ማስረጃ ማቅረቡን ለችሎቱ አስረድቷል።

በሌላ በኩል ፖሊስ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ 200 ግለሰቦች መገደላቸውን ፥ በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሃመድን ጨምሮ አራት ተጠርጣሪዎች ላይ በሚደረግ ምርመራ ላይ ማግኘቱን ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።

በመቀጠልም ፖሊስ ቀረኝ ያለውን በጅምላ የተቀበሩ 200 በላይ ግለሰቦች አስከሬን መለየትና የዚህን ድርጊት መፈጸም የሚያረጋገጡ ምስክሮች ቃል ለመቀበል፥ እንዲሁም በተለያዩ ዞኖች ጉዳት የደረሰባቸው 37 ግለሰቦች ማስረጃ ተርጉሞ ለማምጣት እና ለወንጀሉ ተግባር የዋለ ገንዘብና መሳሪያን ለመያዝና ሌሎች ስራዎችን ለማከናወን 14 ቀን ጊዜ ይፈቀድልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ያቀረበው የምርመራ ስራ ተመሳሳይ በመሆኑና፥ የሚያቀርበው ምክንያትንም አግባበነት የሌለውና የተጠርጣሪዎችን አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብትን የሚጎዳ ነው ብለዋል ።

ሰለሆነም ተጠርጣሪዎች እያንዳንዳቸው አደረሱት የተባለው ጉዳት መጠን በተናጠልና በዝርዝር ሊቀርብ ይገባል በማለት ተከራክረዋል።

በተጨማሪም በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ 200 ሰው ተገደለ የተባለው አዲስ ምርመራ በመሆኑ፥ ለብቻው ተነጥሎ ሊታይ ይገባል ሲሉ የፖሊስን ምርመራ በምክንያት ተቃውመዋል።

ፖሊስ በበኩሉ 200 ሰዎች ተገደሉ የተባለው በዚሁ ምርመራ ሲከናወን የተገኘ በመሆኑ አንድ ላይ ሊካተት ይገባል ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ሰለሆነም ከወንጀሉ ከባደና ውስብስበነት አንጻር ተጨማሪ 14 ቀን መጠየቄ አግባበ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ምርመራው በአጭር ጊዜ ሊከናወን የማይችል በመሆኑ እና ከወንጀሉ ከባድና ውስብስብነት አንጻር ፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ መጠየቁ ትክክል ነው ብሏል።

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የምርመራ ስራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለህዳር 13 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።

Comments are closed.