Take a fresh look at your lifestyle.

ዋናው መገለጫዬ የኢየሱስ ባርያ ነኝ ። ትልቁ መገለጫዬ ያ ነው ። ሌላው ለእኔ ትርፍ ነው ። ሌላው በሙሉ ትርኪ ምርኪ ነው። ( ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ )

1,312

ፍቅር፣ ፍትሕ እና ሰላም የኢየሱስ መንገድ

Written by

ፍቅር፣ ፍትሕ እና ሰላም የኢየሱስ መንገድ

የሕይወት ዘመኔን በሁለት እከፍለዋለሁ፤ አንደኛው መጽሐፍ ቅዱስ ከማንበቤ በፊት የነበረኝ እና መጽሐፍ ቅዱስ ካነበብሁ በኋላ ያለኝ ብዬ ለሁለት እከፍለዋለሁ።
……………………………………………….

በዚህ ልዩ ዕትም፣ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው እስክንድር ነጋ የሕንጸት ዕንግዳ ሆኖ ቀርቧል። አገራችን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲ የሚከበሩባት አገር እንድትሆን መሥዋዕትነትን የጠየቀ ትግል አድርገዋል ከሚባሉት ግለ ሰቦች መካከል አንዱ እስክንድር ነው። በዚህም፣ ከዘጠኝ ጊዜያት በላይ ደጋግሞ ለእስር የተዳረገው እስክንድር፣ በአጠቃላይ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ በእስር አሳልፏል።ጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ በተለያዩ ጊዜያት፣ ከተለያዩ ተቋማት ሽልማቶች የተበረከቱለት ሲሆን፣ የትዳሩ አጋሩ ከሆነችው ሰርካለም ፋሲል ናፍቆት እስክንድር የተሰኘ ልጅ አግኝቷል። ባለቤቱ ሰርካለም እንዲሁ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ተሰማርታ የቆየች ሲሆን፣ ምርጫ 97 ን ተከትሎ ወደ ወህኒ ከወረዱ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ነበረች። ወህኒ ስትወርድ ነፈሰ ጡር የነበረችው ሰርካለም፣ ልጃቸውን ናፍቆት እስክንድርን የተገላገለችው በማረሚያ ቤት ውስጥ ሆና ነበር። የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በቅርቡ በይቅርታ ከእስር ከለቀቃቸው የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መካከል አንዱ የሆነው እስክንድር፣ ስድስት ዓመት ተኩል በቆየበት የእስር ጊዜው ባዳበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ በልዩ ሁኔታ ስለተዋወቀው ኢየሱስ ክርስቶስ እና የክርስትና ሕይወት ለሕንጸት ዋና አዘጋጅ ሚክያስ በላይ እንዲህ አጫውቶታል። 


ሕንጸት፦ እስክንድርን ለማያውቁ አንባቢዎች ስለማንነትህ በመጠኑ ብትነግራቸው?

እስክንድር፦ አዲስ አበባ ነው የተወለድኩት። ከዚያ በኋላ ለብዙ ዓመታት በውጭ አገር ኖሬአለሁ። አሁን የምኖረው አገሬ ውስጥ ነው። ‘ማነህ?’ ላልከኝ ግን፣ ዋናው መገለጫዬ የኢየሱስ ባርያ ነኝ። ትልቁ መገለጫዬ ያ ነው። ሌላው ለእኔ ትርፍ ነው። ሌላው በሙሉ ትርኪ ምርኪ ነው። ዋናው መገለጫዬ ግን የኢየሱስ ባርያነት ነው።

ሕንጸት፦ ምን ማለት ነው?

እስክንድር፦ ለኢየሱስ ልቡ የተሰበረ ሰው ማለት ነው። እሱ እኛን ሊያገለግል ነው የመጣው፤ ምሳሌ ሆኖ ማለት ነው። እኔ ደግሞ የእሱ አገልጋይ መሆን ነው ትልቁ ጥሜ። አገራት ሕገ መንግሥት አላቸው። እኔ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው ሕገ ሕይወት ሊኖረው ይገባል ብዬ አምናለሁ። ለእኔ ሕይወት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋናው ምሰሶው ወይም ዋናው ግንዱ ኢየሱስ ነው። ከኦሪት ጀምረህ እስከ መጨረሻው ስለ እርሱ ነው የሚናገረው። የኢየሱስ ባርያ ነኝ ስል፣ ሁሉ ነገሬን ለኢየሱስ ያስገዛሁ ነኝ ለማለት ነው። ሙሉ ለሙሉ። ፈረንጆች “dependent” የሚሉት ነገር አላቸው። በእርሱ ላይ ሙሉ ለሙሉ የተደገፍሁ መሆኔን የተረዳሁና ያወቅሁኝ ሰው ነኝ።

ዋናው መገለጫዬ ግን
የኢየሱስ ባርያነት ነው።

በነገራችን ላይ፣ ይህንን ስልህ አንብቤ አይደለም የተረዳሁት፤ በጸጋ ነው ያገኘሁት። መረዳቱ ራሱ ጸጋ ነው። የእርሱ ስጦታ ነው እንጂ፣ እኔ በራሴ በአእምሮዬ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤ የደረስኩበት አይደለም። እምነት ራሱ ጸጋ ነው። መቀባት አለብህ። ከእሱ የሚሰጥህ ነው። የኢየሱስ ባርያ ነኝ ስል፣ ይህንንም ከግምት በመክተት ነው።

ሕንጸት፦ ሁለት እስክንድር አለ ልበል? በፊት የምናውቅህ፣ ለፍትሕና ዲሞክራሲ ስትሟገት ነው፤ በተለይ በጋዜጣ ሥራ ላይ። አሁን ደግሞ አሁን በነገርከኝ ማንነት ነው ያለኸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶች ይያያዙልሃል፤ ማለት አንዱ አንዱን የሚደግፍ አድርገህ ነው የምታየው ወይስ ሙሉ ለሙሉ አዲስ ማንነት እንዳለህ ነው የምታስበው?

እስክንድር፦ አይለያዩም። እንዳልኩህ ሕገ ሕይወት አለኝ ስል፣ እንደ ጋዜጠኛም፣ እንደ አባትም፣ እንደ ባልም፣ እንደ ልጅም፣ እንደ ጓደኛም እንደ ማኅበረ ሰቡ አባልም የሚገዛኝ ሕግ አለ። ያ ሕግ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ነው። ኢየሱስ ነው፤ መድኃኔዓለም ነው። ሁለት ማንነት የለም፤ ሁለት ሰው የለም።

ሕንጸት፦ አንድ ቦታ ላይ የተናገርኸው ነገር አለ፤ ‘በልማድ የማውቀው ኢየሱስ ነበረ፤ በክርስትና ባህል ውስጥ ነው ያደግሁት፤ አሁን ግን ከኢየሱስ ጋር ተገናኝቻለሁ (personal encounter)’ ብለህ ነበር። ከዚህ ተነሥቼ ነው ሁለት ማንነት ነው ወይ ያልኩህ? ከዚሁ ጋር አያይዘህ፣ ኢየሱስን ማወቅ ስጦታ ነው ብለሃል፤ እሱን የማወቁ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?

እስክንድር፦ በልማዳዊ ክርስትና ውስጥ መኖር እና በጸጋ እምነትን ማግኘት የሚለያዩ ነገሮች ናቸው። እኔ በጣም አማኝ ከሆኑ ቤተ ሰብ ነው የወጣሁት። አያቴ ልጅ ሆኜ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ይወስዱኝ ነበር። ቤተ ክርስቲያን ለእኔ አዲስ አይደለም፤ ከልጄነቴ ጀምሮ የማውቀው ነው። እንደ ገና የቤታችን ሥርዐት ጥብቅ ክርስትናን ይከተል የነበረ ነው። ሰባቱም አጽዋማት በሚከበርበት ቤት ውስጥ ነው ያደግሁት። አብዛኛውን ጊዜ እንደውም ቁርስ አላውቅም፤ ሁሉም ሰው ቁርስ የማይበላ ሁሉ ይመስለኝ ነበር። በኋላ ላይ ነው የተረዳሁት።

ከዓርብ እስከ እሑድ ምንም ነገር የማይሠራበት ቤት ውስጥ ነው ያደግሁት። ግቢ ውስጥ ካለው ቧንቧ ውሃ እንኳ አይቀዳም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት እያንዳንዱ ነገር እስከ ጫፍ ድረስ በሚከበርበት ቤት ውስጥ ነው ያደግሁት። ይህ በመሆኑም ክርስትና አብሮኝ የኖረ ነው። ቤተ ክርስቲያን ሳገኝ ሳልሳለም አላልፍም ነበር። አሁንም እሳለማለሁ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤ አላውቅም ነበር። ይህንን ዕድል ያገኘሁት፣ አሁን ስድስት ዓመት ተኩል እስር ቤት በገባሁ ጊዜ ነው። ስለዚህ እስሩንም አላማርርም። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስን አስተዋውቆኛልና ነው። ስድስት ዓመት ተኩል አጥቼ የዘላለም ሕይወት አግኝቼበታለሁ ብዬ ስለማስብ ነው። እስሩ አያስመርረኝም። ትልቁ ቁም ነገር፣ ትልቁ ጉዳይ የሸመትኩበት፣ ያገኘሁበት ወቅት ነው።

ስለዚህ የሕይወት ዘመኔን በሁለት እከፍለዋለሁ፤ አንደኛው መጽሐፍ ቅዱስ ከማንበቤ በፊት የነበረኝ እና መጽሐፍ ቅዱስ ካነበብሁ በኋላ ያለኝ ብዬ ለሁለት እከፍለዋለሁ። ከመማሬ በፊትና ከተማርሁ በኋላ ብዬ የምከፍለው አይደልም፤ ወይም አሜርካን አገር ከነበርኩበትና ከዚያ በፊት ብዬ የምከፍለው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ካነበብሁበትና ካነበብሁ በኋላ ብዬ ነው የምረዳው።

እዚህ ላይ ብዙ ሰው አይረዳም ብዬ የማስበው ነገር አለ፤ እኔም የማልረዳው ስለ ነበረ። መጽሐፍ ቅዱስን በአእምሮህ አንብበህ የምትረዳው ነገር አይደለም። ለዚህ ነው መረዳቱ ራሱ ሥጦታ ነው ያልኩሁ። መጀመሪያም መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መቀባት አለብህ። የእርሱ ፍቃድ ያስፈልጋል፤ ያለ እርሱ ፈቃደ አንብበህ ላትረዳው ትችላለህ። በነገራችን ላይ የዓለማችን ትልልቅ ሳይንቲስቶች፣ ትልቅ የአእምሮ ምጠቅት ያላቸው ሰዎች አንብበው አልተረዱትም። በአእምሮህ የምትረዳው ነገር አይደልም። አስቀድሞ ሊሰጥህ ይገባል። ስለዚህ ከምንም ነገር በፊት ሰው መጸልይ አለበት የምለው፣ እንዲሰጠው ነው፤ እንዲቀባ ነው። ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ ለሙሉ አላነበብሁም ብዬ እኮ አይደለም፤ አንብቤዋለሁ። አሁን በተረዳሁበት መንገድ ግን አልተረዳሁትም። ያን ጊዜ አልተቀባሁም ብዬ ነው የማምነው። ከዚህ በፊት ላይ ላዩን ባነብበውም፣ አሁን በተረዳሁት መልክ አልተረዳሁትም ለማለት ነው።ይሄ በጣም ሊሠመርበት ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን በአእምሮህ አትፈልገው፤ በልብ፣ በእምነት ፈልገው። እሱም እንዲሰጥህ ለምን፤ ጠይቅ። ይህንን ማስቀደም አለብህ ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ሳድግ የነበረኝ ክርስትና እና አሁን ያለኝ ክርስትና በጣም ይለያያል። ባህላዊ ክርስትና የምለው ያንን ነው። አሁን ደግሞ የሥጦታ ክርስትና ነው፤ የእምነት ክርስትና ነው። በዚህኛው ዓለም ውስጥ መኖር በትልቁ መታደል ነው የምልህ። እውነቴን ነው የምለህ!

አሁን ያለሁበት መገለጥ ልበለው፣ ዳግም መወለድ ልበለው፣ ያደረገልኝ ነገር በተለይ በዚህ በዓለማዊው ሕይወት ውስጥ የማደርገውን ነገር የበለጠ እንዳምንበት ርድቶኛል። ምክንያቱም፣ የክርስትና አንኳር አስተምህሮ ‘ጓደኛህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው ብዬ ስለማስብ። ‘አንኳሩ ትምህርት ምንድን ነው?’ ብለህ ብትጠይቅ፣ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አቅምህ ፍራ፣ ውደድ፤ ጓደኛህን እንደ ራስህ ውደድ የሚሉት እነዚህ ናቸው። ራሱ ኢየሱስ እንዳለው ማለት ነው። ፖለቲካ ውስጥ ለዲሞክራሲ ስንቆም፣ ጓደኛህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ የሚለውን መርሕ በፖለቲካ ዓለም አምጠተን መተግበር ማለት ነው።

ሕንጸት፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር። እንዴት አዳበርኸው? በቀን ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ታነብብ ነበረ?

እስክንድር፦ በነገራችን ላይ አንዳንድ ሰዎች በአንድ ጊዜ የሚገለጥላቸው ነገር አለ። አንድ ጧት ብድግ ብዬ የተገለጠልኝ አይደለም። ወይም ደግሞ የተለየ ዐይነት ብርሃን ያየሁት አልነበረም። ምንም የተለየ ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብብ፣ ቀስ ብሎ ውስጤ የገባ ነገር አለ። መልእክቱ ገብቷል፤ ይህም በሂደት ነው የሆነው። በስድስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ደግሜ፣ ደጋግሜ አንብቤአለሁ። በነገራችን ላይ ፕሮግራም አውጥቼ ጠዋትና ማታ ነበር የማነብበው። ጧት ግማሽ ሰዓት አነብባለሁ፤ ማታ ግማሽ ሰዓት አነብባለሁ። በርግጥ እስር ቤት ውስጥ ከነበረው ጊዜ አኳያ ብዙም አይደለም። በእጄ ላይ የነበረው አዲስ ኪዳን ብቻ ነበር። የእግሊዘኛው ትርጉም ነው የነበረኝ። ብሉይ ኪዳንን ለማግኘት ሞክሬ አልተሳካልኝም። ማረሚያ ቤቱ ብሉይ ኪዳንን እንዳላገኝ ከለከለኝ።

በነገራችን ላይ ይህ ውሳኔአቸው የመጨረሻው የዘቀጠና መጥፎ ውሳኔአቸው ነበር። ይህንን ደግሞ እዚያ በቆየሁበት ዓመታት ሁሉ ስነግራቸው ነው የኖርኩት። ይህን ሲወስኑ የነበሩ ሰዎች መጨረሻቸው አሁን ጥሩ ሳይሆን ሲቀር አይቻለሁ። እኛ በፖለቲካ እንለያያለን፤ መቼም ቢሆን የሚታረቅ መሥመር አይደለም ያለን። በሃይማኖት ግን አንለያይም። በሃይማኖት ከአንድ ወንዝ ነው የተቀዳነው። ስለዚህ እኔ መጽሐፍ ቅዱስ አግኝቼ ማንበቤ ለእነሱ ምንም ዐይነት ጉዳት የሚያመጣባቸው አልነበረም፤ የሚቃወሙትም አልነበረም። “ከእኔ ጋር አይደልም የምትጣሉት፤ ድፍረቱ እኔ ላይ አይደለም፤ ወደ ላይ ነው። እሱን መድፈር ነው፤ ከእሱ ጋር መጣላት ነው።” ብላቸው አልሰሙኝም። ሦስት ዓመት ሙሉ ስንከራከር የነበረው በዚህ ላይ ነበር። ስወጣም የመጨረሻው ንግግራችን በዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ የተለወዋወጥነው እንጂ፣ ‘ስድስት ዓመት በሐሰት ከሰሳችሁኝ’ ብዬ አልነበረም ስነግራቸው የነበረው።

ሕንጸት፦ መጀመሪያ አዲስ ኪዳን አስገብተውልህ ነበር ማለት ነው?

እስክንድር፦ አዲስ ኪዳን ቀድሞ ነበረኝ። መጽሐፍ መከልከል የጀመሩት፣ እኔ ውስጥ ሆኜ እጽፍ ስለ ነበረ ነው፤ የምጽፈውም እየወጣ ይታተም ነበር። ስለዚህ እነሱ፣ “ጽሑፍ አቁም” ይላሉ፤ እኔ ደግሞ “አላቆምም” በሚል ጭቅጭቅ ይፈጠራል። ይህንን ተከትሎ መጀመሪያ መጽሐፍ ከለከሉ፤ ከዚያ በኋላ ስክሪብቶ ከለከሉ፤ ከዚያ በኋላ ወረቀት ከለከሉ። ማዕቀብ ጣሉ። ከዚህ የተነሣ ለአራት ዓመት ተኩል አንድም መጽሐፍ አልደረሰኝም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስንም አንድ ላይ ደመሩት። “ሌላውን መጽሐፍ ከልክሉ፤ ችግር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስን ግን እዚህ ውስጥ አትክተቱት” ብዬ አስረዳኋቸው። “የማነብበው የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ ብሉይ ኪዳን ያስፈልገኛል” ብል አልሰሙኝም።

ሕንጸት፦ አዲስ ኪዳን ብቻ ስታነብብ ቆየህ።

እስክንድር፦ አዎ፤ አዲስ ኪዳን ብቻ ነው፤ “Lamp Foundation” ያሳተመው ትርጉም ነበር የነበረኝ። በዚህ አጋጣሚ ላምፕ ፋውንዴሽን እግዜር ይስጣቸው። በጣም ቀላል በሆነ ቋንቋ ነው ያዘጋጁት። ለስድስት ዓመት ተኩል መልሼ፣ መልሼ ያነበብኩት አዲስ ኪዳንን ነው። ስንት ጊዜ አነበብከው ብትለኝ አላስታውስም፤ ግን በጣም ብዙ ጊዜ አንብቤዋለሁ። በቀን አንድ ሰዓት አነብባለሁ፤ በሳምንት ሰባት ቀን ነው የማነብበው፤ ቢያንስ ለአራት ዓመት ተኩል አንብቤአለሁ። አሁን ከወጣሁ በኋላ ትንሽ ቀንሻለሁ። ያው፣ ዓለማዊው ነገር ጠልፎኛል። ይሄው ነው የሰው ልጅ። ይህን ለማስተካከል መሥራቴ አይቀርም። በዚህም ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በጣም ተቀራረብሁ። በአንድ በኩል it is a blessing in disguise. [‘ለበጎ ነው’ እንደሚባለው] ነው የሆነው። ቢከለክሉኝም፣ በመከልከሉ ሙሉ ለሙሉ አልተጎዳሁም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋናው ነገሩ አዲስ ኪዳን ነው። በነገራችን ላይ አሁንም አልጠገብኩትም፤ የሚጠገብም አይደለም። ለዘላለም ቢነበብ የማያልቅ መልእክት አለበት።

ሕንጸት፦ ብሉይ ሳይገባ ቀረ?

እስክንድር፦ አልገባልኝም። በአዲስ ኪዳን ነው የጨረስኩት። አማርኛ ብሉይ ኪዳን ነበረኝ፤ ግን የእንግሊዘኛውን ያህል clarity [ግልጽነት] አልነበረውም። ቀለል ባለ አማርኛ የተዘጋጁ አሉ፤ ነገር ግን እንደ አጋጣሚ እጄ ላይ የነበረው ጠጠር ባለ አማርኛ የተዘጋጀው ነው። በዘመናዊው አማርኛ የወጣው ቢኖረኝ ኖር ይቀልል ነበር።

ሕንጸት፦ “ፍቅር፣ ፍትሕ እና ሰላም የኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ናቸው” ትላለህ። ምን ማለትህ ነው?

እስክንድር፦ ሦስቱንም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታገኘዋለህ። የማቴዎስ ወንጌል የተራራው ስብከት በሚባለው ላይ ታገኘዋለህ። የሁሉም አባት ግን ፍቅር ነው። ይህንን ጳውሎስ በግልጽ አስቀምጦታል፤ ጥሩ አድርጎ (በርግጥ በእርሱ በኩል የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው)። የሁሉ ነገር ማሰሪያው ፍቅር ነው። በተለይ አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር እነዚህ ነገሮች ያስፈልጉናል። አገራችን በሽግግር ወቅት ላይ ነው ያለችው። ብዙ ነገሮች አልጠሩም፤ እነዚህ ዕሴቶች ወሳኝ ናቸው። እንደ ኅልውና፣ እንደ አገር ለመቀጠል ወሳኝ ናቸው። እነሱ ላይ ቆመን ነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዐቱን መገንባት የምንችለው። ፍቅር፣ ፍትሕ እና ሰላም በሌለበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን መገንባት አንችልም፤ የዴሞክራሲ ባህልን ማምጣት አንችልም። መሠረት ያስፈልገዋል። እነዚህ ደግሞ ሊያስተሳስሩ የሚችሉ የሞራል መሠረቶች ናቸው። ዓለምን የምታይበት መነጽር ናቸው። እነዚህ ከሌሉ የዴሞክራሲ ተቋማትንና ባህልን ማምጣት አይቻልም። በተለይ ፍቅር መሠረት ነው። ፍቅር ደግሞ፣ “ጓደኛህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” የሚለው ነው። ይህን ወደ ፖለቲካው ዓለም ስታመጣው ዴሞክራሲ ይሆናል።

ሕንጸት፦ አንዳንድ ሰዎች፣ ‘ዴሞክራሲ ከኢየሱስ ትምህርት ጋር ላይሄድ ይችላል’ ይላሉ። በዚህ ትስማማለህ?

እስክንድር፦ በፍጹም አልስማማም። ይሄ ትልቅ ስሕተት ነው። እንዳልኩህ የኢየሱስ አንኳር መልእክቱ “ጓደኛህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” የሚል ፍቅር ነው። ዴሞክራሲ የሚያስተምርህ እኮ፣ ከአንተ ጋር የማይስማማውን ሰው አክብረው ነው። የዴሞክራሲ አንኳር ይህ ነው። አንተ አስተሳሰብህን፣ እምነትህን በሌላው ላይ በኀይል እንዳትጭን ነው የሚያደርግህ። የሌላውን አስተሳሰብ፣ የሌላውን ሰው ማንነት አክብርለት ነው የሚልህ። ታዲያ፣ ይሄ አይደለም እንዴ ክርስትና? ይህንን አይደለም እንዴ ኢየሱስ ያስተማረው? የዴሞክራሲ አንኳር መልእክት ከኢየሱስ አስተምህሮ ጋር የሚስማማ ነው። ዴሞክራሲ፣ ሌላውን ሰው በእምነቱ አትጥላው፣ አታግልለው፣ አትጉዳው ነው የሚለው። እነዚህ መርሖዎች ግን ለክርስትና ብቻ የሚሠሩ አይደሉም፤ ሉል ዓቀፋዊ (universal) ናቸው። በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ሄደህ ታገኛቸዋለህ። በቁርዓና ውስጥ ታገኛቸዋለህ፤ በሂንዱ ውስጥ ታገኛቸዋለህ፤ በቡድሂዝም ውስጥ ታገኛቸዋለህ። ሉል ዓቀፋዊ ባሕርይ አላቸው። ሃይማኖቶች የተለያዩ ቢሆኑም በውስጣቸው የጋር መልእክት ደግሞ አላቸው። ለዚህ ነው ዴሞክራሲ በተለያዩ አገራት መሥራት የቻለው። ዴሞክራሲ ከክርስትና ጋር በጣም ይሄዳል።

ሕንጸት፦ ክርስትና ለአንዳንድ ሰዎች በምድራዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ሳይሆን፣ ሰማያዊ ብቻ ነው። ስለዚህ በመንግሥት ጉዳይ፣ በፍትሕና መሰል ጉዳዮች ላይ ከጸሎት ባለፈ መግባት አንችልም ይላሉ። የእነዚህን ሰዎች አመለካከት እንዴት ታየዋለህ?

እስክንድር፦ ይህን አመለካከታቸውን አከብራለሁ፤ ስሕተት ነው አልልም። አንድ ሰው ለኢየሱስ ብሎ ራሱን ከዚህ ዓለም ሊያገልል ይችላል፤ ምንም ችግር የለውም። መጽሐፍ ቅዱሱ ይፈቅዳል። ሌላው ሰው ደግሞ በዚህ ዓለም ጉዳይ ያገባኛል፤ በተለይ ለፍትሕ መሥራት አለብኝ፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ትቶልኝ የሄደው ምሳሌ ይሄ ነው። እርሱ ብዙ ቦታ ላይ ስለ ፍትሕ ተናግሯል፤ ስለ ፍቅር ተናግሯል። ስለዚህ እኔም ዓለማዊ ጉዳዩ ውስጥ ገብቼ ለእነዚህ ዕሴቶች እሠራለሁ ቢል ይህም ያስኬዳል። ሁለቱም ጎን ለጎን መኖር የሚችሉ ናቸው። አንተ ትክክል ነህ፤ አንተ ትክክል አይደለህም ተብሎ የምንወጋገዝበት አይደልም። ራሳቸውን ከዓለማዊ ጉዳይ አግልለው፣ ሙሉ ለሙሉ ለጌታ የተሰጡትን እኔ አከብራቸዋለሁ። ሌላው እንደ እኔ ዐይነቱ ደግሞ በዓለም ጉዳዩ ውስጥ መግባቱ ጌታን መተው ነው ማለት አይደለም። ይህም ከአስተምህሮ ጋር የሚቃረን አይደለም። ሁለቱም ዋጋ አላቸው። በሁለቱም መንገድ ሄደን ጌታ ጋር መድረስ እንችላለን። ዋናው ጌታን ለማስደሰት መኖር ነው። ለነገሩ እኛም በሁለቱም መንገድ ሄደን፣ ጎዶሎ ነን። ራሳችንን ከዓለም ነጠልን ወይም በዓለም ውስጥ ከተትን ጎዶሎ ነን። ሰው ነን። የመነነም ሰው እንኳ፣ ራሱን ሙሉ ለሙሉ ከዓለም ነጥሎ ገዳም ውስጥ የገባ ሰው እንኳ ጎዶሎ ነው። ሰው ብሎ ፍጹም የለም። ሁልጊዜም እኛ የምንጸድቀው በሥራችን አይደለም። የጳውሎስን መልእክት እንዳንረሳ፤ በሥራ መጽደቅ አንችልም። በሥራ እጸድቃለሁ ማለት መመጻደቅ ነው፤ መታበይ የምንለው ይህንን ነው። የሰው ልጅ በሥራው አይጸድቅም፤ የምንጸድቀው በጸጋ ነው፤ በይቅርታው ነው። ውስጣችን የወረስነው ኀጢአት አለ፤ ያንን ኀጢአት ልናሸንፈው አንችልም። በራሳችን ጉልበት ልናሸንፈው አንችልም። ያንን ኀጢአት ልናሸንፈው የምንችለው በእርሱ ይቅርታ ብቻ ነው። ስለዚህ በሁለቱም መንገድ ሄደን ጌታ ጋ መጨረሻ ላይ ይቅርታ ያስፈልገናል። ነገር ግን እዚህ ዓለም ላይ በምንቆይበት ጊዜ ምርጫችን አንዳችን ሙሉ ለሙሉ ጊዜያችንን በጸሎትና በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ማሳለፉ ጥሩ ነው፤ የሚደገፍ ነው። ሌሎቻችን ደግሞ፣ ‘አይ፣ ጌታን ተቀብለናል፤ ግን በዓለማዊ ጉዳይ ላይም እንገባለን’ ስንል ይህም ጥሩ ነው።

ሕንጸት፦ አንድ ክርስቲያን ስለ ፍትሕ ሲታገል የት ድረስ መሄድ አለበት ትላለህ? በዚህ ትግል ውስጥ የኢየሱስ መንገድ የትኛው ነው? መንገዱ መሥዋዕትነት ነው ወይስ አጥቂነት ነው?

እስክንድር፦ መሥዋዕትነት ነው። አጥቂነትማ አይቻልም፤ በክርስትና አይቻልም። ማጥቃት አትችልም፤ ምንም ነገር። ክልክል ነው። በነጭና በጥቁር የተጻፈ ክልከላ አለ። ፍርድ የፈጣሪ ነው። ማጥቃት አትችልም፤ መሥዋዕትነት ነው። ‘እሱን ከየት አመጣኸው?’ ካልከኝ ደግሞ፣ የኢየሱስ ምሳሌነት ነው። ኢየሱስ ትቶልን የሄደው ምሳሌ ነው። በነገራችን ላይ እኮ፣ እሱን ሲመቱት አልተማታም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ ሲዝቱበት መልሶ አልዛተም። ይህን ሁሉ ማድረግ ይችል ነበር። ይህንን ምሳሌ የመከተል ኀላፊነት አለብን። ይህን ሁሉ ያደረገው እኮ ዝም ብሎ አይደልም፤ ለእኔና ለአንተ ምሳሌ ለመተው ነው። ሲመቱህ እንዳትማታ ነው፤ ሲሰድቡህ አትስደብ ነው፤ ሲያጠቁህ አታጥቃ እያለን ነው። ያንን ምሳሌ ለመኖር መሞከር አለብን።

በርግጥ ይህን ሁልጊዜ እንተገብረዋለን ማለት አይደለም፤ አንችልም። ቅድም እንዳልኩት ጎዶሎ ነን። እሱን ሙሉ ለሙሉ መሆን አንችልም። ሰው ነንና፤ ጎዶሎ ነንና። በትንሹም በትልቁም መናደዳችን እኮ እይቀርም፤ እሱ ግን አይናደድም።ያ ሁሉ መዓት ወርዶበት፣ ያ ሁሉ ግፍ ወርዶበት ግን ኢየሱስ አይናደድም፤ አልተናደደም፤ አይቆጣም። ዞሮ ዞሮ ዋናው ትልቁ ቁም ነገር እሱን ለመሆን መሞከር ነው፤ እሱን ለመሆን መሞከር ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ራሳችንን በየጊዜው እየገታን መጨረሻ  ላይ ራሳችንን ለመሥዋዕትነት ማዘጋጀት አለብን። በዚህ ለመሥዋዕትነት ስንሄድ ግን ቅድም እንዳልኩት፣ ብዙ ኀጢአት እየፈጸምን ነው። እኔ ውስጤ ሳልቆጣ ቀርቶ አይደለም፤ በውስጤ ቂም ሳልይዝ ቀርቼ አይደልም። ስድስት ዓመት ተኩል በግፍ ታስሬአለሁ። በመሠረቱ እኔ በዚህ መንግሥት ከዘጠኝ ዓመት በላይ ነው የታሰርኩት።

 

 

ሕንጸት፦ ስንት ጊዜ ታሰርክ?

እስክንድር፦ ዘጠኝ ጊዜ ያህል ደጋግሜ ታስሬአለሁ፤ ከዘጠኝ ዓመት በላይ ደግሞ በእስር አሳልፌአለሁ። ስለዚህ ይሄ ነገር ውስጤ ምንም ነገር አልፈጠረም ልልህ አልችልም። ቤተ ሰቤን ጎድቶታል፤ ልጄን ጎድቶታል፤ ባለቤትን ጎድቷታል። ስለዚህ ውስጤ ቁጣ የለም አልልህም። ቁጣዬን ግን ሁልጊዜ እታገለዋለሁ። ያንን ነው ማድረግ የምችለው። ሰው ስለሆንኩ ግን በውስጤ ቁጣ አለ። ኢየሱስ ግን አይቆጣም። ስለዚህ ሁልጊዜ ኀጢአታችንን እየታገልን ለመሥዋዕትነት ነው መዘጋጀት ያለብን። እሱም ቢሆን ራሱ ትግል ይፈልጋል፤ ከራስ ጋ ትግል ይፈልጋል። በበቀሉ መንገድ እንድትሄድ፣ ወደ አጥቂነት እንድትሄድ፣ ወደ ቁጣው መንገድ እንድትሄድ ሰይጣን ሁልጊዜ ይፈታተንሃል። ሁልጊዜ ፈተና አለብህ። ራስህን እየታገልህ፣ ከታደልክ፣ ከተቀባህ፣ በእርሱ ከተመረጥክ፣ መጨረሻ ላይ መሥዋዕት ትሆናለህ። ለዚህ ደግሞ መጸለይ አለብህ። በማናቸውም ሰዓት፣ በቀላሉ በዚያኛው መንገድ ልትሄድ ትችላለህ። መሥመሯ በጣም ቀጭን ናት። በዚያች ቀጭን መሥመር ላይ ነው የምትጓዘው። ቀላል አይደለም ልልህ ነው። የመሥዋዕትነቱን መንገድ እንደ ኢየሱስ መምረጥ በጣም ከባድ ነው። ሃይማኖታችን የሚያስተምረንና የሚያስገድደን የመሥዋዕትነቱን መንገድ እንድንመርጥ ነው።

ሕንጸት፦ በአገራችን ያሉ የሃይማኖት ተቋማት ለፍትሕ፣ ለእኩልነት፣ ለሰላም ያበረከቱት አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው ትላለህ?

እስክንድር፦ ለምሳሌ የእኔን ቤተ ክርስቲያን ውሰድ፤ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን። የኦርቶዶክስን ብቻ የወሰድህ እንደ ሆነ፣ የረዥም ዘመን ታርክ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የሺህ ስድስት መቶ ዓመት ታሪክ ያላት ናት። በዚህ ዘመን ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ አልፋለች። Institutional memory የሚባል ነገር አለ። ዮዲትን ያየች ነች፤ የተለያዩ ዐፄዎችን ያየች ነች፤ በግራኝ አሕመድ ዘመን ያለፈች ነች፤ የተለያዩ የመሳፍንት ዘመንን ያለፈች ነች፤ ጣልያንን ያየች ነች፤ ደርግን ያየች ነች፤ አሁን ደግሞ ኢህአዴግን እያየች ነው። በእነዚህ ዘመናት ውስጥ ያካበተችው ዕውቀት አለ። በዚህ ሁሉ ዘመን ውስጥ ነገሮችን ቀስ ብሎ፣ ዝቅ ብሎ የማስተናገድ ባህልን ኮትኩታለች። ስለዚህ ምናልባት እኛ አሁን በምንፈልገው መጠን ላይሆን ይችላል ምላሽ የሰጠችው። ነገር ግን ያለፈችባቸውን አንድ ሺህ  ስድስት መቶ ዓመታት ግምት ውስጥ ሳናስገባ ልንፈርድባት አንችልም። ‘ለምንድን ነው እንደዚህ የሆንሽው? ለምንድን ነው እንደዚህ የምታደርጊው?’ ልንላት አንችልም።ሌሎቹ ሃይማኖቶችም እንዲሁ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያለፉ ናቸው። ፕሮቴስታንቱ እንዲሁ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያለፈ ነው፤ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ በተለያዩ ችግር ውስጥ ያለፈ ነው፤ ሙስሊሙም እንደዚሁ በተለያየ ዐይነት ችግር ውስጥ ያለፈ ነው። ስለዚህ ልክ አሁን እዚህ ላይ ቆመን፣ ከዚህ በፊት የነበረውን ታሪክ በሙሉ ግምት ውስጥ ሳናስገባ ልንፈርድባቸው አይገባም ብዬ አስባለሁ። ሁሉም ግን ከዚህ የበለጠ መሥራት እንዳለባቸው አምናለሁ፤ ከዚህ የበለጠ ሊሠሩ ይገባል። በተለይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት እውን ሲሆን፣ የሞራል መሪነቱን ሚና ይበልጥ አጉልቶ መጫወት ይገባቸዋል። ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን የመገንባቱ ዋና ኀላፊነት ግን የእምነት ተቋማቶቻችን አይደለም። ይሄ ግልጽ ልሆን ይገባል። በዓለማዊ ተቋማት ውስጥ ያለው ምስቅልቅል ተጠያቂዎቹ እኛ ነን። እኛ ነን ያበላሸነው። መጨረሻ ላይ ዞሮ ዞሮ ማስተካከል ያለብንም እኛው ነን ብዬ አምናለሁ። እኔ በእምነት ተቋማቶቻችን ላይ ወቃሽ አይደለሁም።

ሕንጸት፦ ለጭቆና ሠርተዋል ብለው የሚወቅሷቸው ሰዎች አሉ።

እስክንድር፦ እኔ በዚህ አልስማማም። የእምነት ተቋማት ዋና ሥራቸው በሰውና በፈጣሪ መካከል ድልድይ መሆን ነው። እዚያ ላይ ወድቀዋል ብሎ መነጋገር ሌላ ጉዳይ ነው። በዴሞክራሲና በፖለቲካ ላይ መሥራት የሚገባቸውን ያህል ባይሠሩ እንኳን፣ ዋና ተልእኳቸውን አበላሽተዋል ማለት አይደለም። ተጨማሪ ነገር ቢሠሩ ጥሩ ነው፤ የሚደገፍ ነገር ነው። እኔ በግሌ የእምነት ተቋማትን የምለካቸው፣ ዋና ተልእኳቸውን እንዴት ተወጡ በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ነው። በዚህ ረገድ እኔ ብዙ ችግር ያለ አይመስለኝም። በነገራችን ላይ ዲያስፖራውን እንኳን ስትመለከት፣ ጠንካሮቹ የእምነት ቤቶቻችን ናቸው። ያ የሚያሳይህ የሃይማኖት ተቋማቶቻችን የሚባለውን ያህል ደካሞች እንዳልሆኑ ነው። እነሱ ያስተላለፉት፣ ያስጨበጡ ዕሴት አለ። እነሱ ባይሠሩት ኢትዮጵያዊ ተበትኖ ወደ ሌላ አገር ሲሄድ፣ በነጋታው እንደየእምነቱ በየቦታው ቤተ እምነቱን አይተክልም ነበር። ይሄ በጣም ውስብስብ ጥያቄ ነው፤ ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ጥያቄ ነው። በእኔ ደረጃ ሊመለስ የሚችልም አይደለም። ኢትዮጵያ ግን የሃይማኖት አገር ነች። ከሌሎች አገሮች ጋር ስናነጻጽረው፣ በአውሮፓም፣ በአሜሪካም ካሉት በእምነቷ የምታንስ አገር አይደለችም። አማኝ ሕዝብ ነው። ብዙ የአውሮፓ አገሮች ግን አማኝ ተብለው ሊጠሩ በማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት፣ የእምነት ተቋማቶቻችን የተባለውን ያህል ደካማ ስላልሆኑ ነው።

ሕንጸት፦ ቀደም ሲል፣ አንተም እንደጠቀስከው አሁን በአገሪቷ ላይ ለውጥ አለ። ይህን ለውጥ ከፍቅር፣ ከምሕረትና ከሰላም አንጻር ለመቃኘት እየተሞከረ እንዳለ በመንግሥት በኩል ይነገራል። በሕዝቡም ዘንድ ተስፍ እንደተሰነቀ ይስተዋላል። የኢየሱስን መርሕ አጥብቆ እንደሚከተል አማኝ፣ ይህ በጎ ጅምር ዳር እንዲደርስ ቤተ ክርስቲያን (ሉል አቀፋዊቷ ማለት ነው) ምን ማድረግ አለባት ትላለህ? በአጠቃላይም አማኝ ነኝ የሚለው የክርስቲያን ማኅበረ ሰብ ምን ያድርግ?

እስክንድር፦ እኔ አሁን የምወስድህ ወደ ቅድሙ ነው። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ የጻፈው ነገር አለ፤ ‘የሁሉ ነገር ማሰሪያው ፍቅር ነው’ ብሏል። ስለዚህ አሁን የታየው ተስፋ እንዳይጨልም ወይም ደግሞ ወደ ተሳሳተ መንገድ እንዳይሄድ የእምነት ተቋማት ፍቅርን በማስተማር፣ ሰላምን በማስተማር፣ ፍትሕን በማስተማር ሊያግዙት ይችላሉ። ከሁሉም በላይ ግን ፍቅር ነው። ፍቅር ስታስተምር በውስጡ ሰላም አለ፤ ፍቅር ስታስተምር በውስጡ ፍትሕ አለ፤ ፍቅር ስታስተምር በውስጡ መቻቻል አለ። በተለይ አገራችን በሽግግር ላይ ባለችበት ወቅት ላይ እነዚህ ዕሴቶች ናቸው የሚያስፈልጓት። የሃይማኖት ተቋማቶቻችን እከሌን ይደግፋሉ ወይም ለእከሌ ያዳላሉ የሚል ጥርጣሬ የለኝም። ስለዚህ ማዳላት የለባቸውም ብዬ አልናገርም፤ ሁሉንም እኩል ማየት አለባቸው ብዬ አልልም፤ ምክንያቱም ሁሉን በእኩል ያያሉና። ስለዚህ ፍቅርን ማዕከል ባደረገ መልኩ ማስተማር አለባቸው ብዬ ነው የማምነው።ሌላው ግን ጸሎት መደረግ አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ ጭቆና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ፣ ከምንጩ እንዲደርቅ የምናደርገበት አጋጣሚ እንዲሆን ወደ አምላክ በመጸለይ እንዲረዱ ነው የምጠይቀው። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለን ሰዎች ልባችንን ቅን እንዲያደርግልን ጸሎት ያስፈልገናል። ስለዚህ ትልቁ ሥራ ለእኛ እንዲጸልዩልን ነው።

ሕንጸት፦ አማኞችስ ምን ያድርጉ?

እስክንድር፦ ለዴሞክራሲ በሰላማዊ መንገድ መታገል ነው። እኔ ይህንን ነው የምለው። መጀመሪያ ነገር፣ አንድ ክርስቲያን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው መታገል ያለበት። ሌላ ሁለተኛ አማራጭ የለውም። አማኝ ከሆነ። እኔ አማኝ የምለው እዚያ ላይ ነው። ቅድም እንዳልነው፣ ‘ጓደኛህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለውን ማንም መንካት አይችልም። የሰውን አካል የፈጣሪ ቤተ መቅደስ ነው ብለን ስለምናም፣ እሱ ላይ ጉዳት ማድረስ አትችልም። እምነታችን ስለሚከለክለን የግድ በሰላማዊ መንገድ ነው መታገል ያለብን። ለእኛ ግዴታ እንጂ ምርጫ አይደለም። መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ይፈቅዳል፣ አይፈቅድም ሌላ ጉዳይ ነው። እሱ የፖለቲካ ትንታኔና ምርጫ ነው። እኛ ግን ክርስቲያን ነን የምንል ከሆነ ከሰላማዊ መንገድ ውጭ መታገል አንችልም። በዚህ የማይስማሙ ብዙ አሉ። እኔ ግን በግሌ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው መታገል ያለብኝ ብዬ ነው የማምነው። መታገያው መድረክ ደግሞ ብዙ ነው። የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብቶ መታገል ይቻላል፤ በሲቪክ ማኅበራት ውስጥ ገብቶ መታገል ይቻላል፤ ጋዜጠኛ ሆኖ መታገል ይቻላል። ከዚያ ባሸገር ግን፣ በምርጫ ካርድ መታገል ደግሞ አለ። ድምፅ ለማን እንደሚሰጥ በጥንቃቅ አስቦ፣ ተጨንቆበት፣ ተጠብቦበት፣ ያቺ ድምፅ ዋጋ እንዳላት ተረድቶ መስጠቱ ራሱ ትግል ነው። ይህ ለአገር ይበጃል፣ ለወገን ይበጃል፣ ለፍቅር ይበጃል፣ ለወንድማማችነት ይበጃል።

አንድ ክርስቲያን በሰላማዊ መንገድ
ብቻ ነው መታገል ያለበት።
ሌላ ሁለተኛ አማራጭ የለውም።

ሕንጸት፦ የኢየሱስን የመሥዋዕትነት መንገድ በመከተል ለፍትሕ እና ለእኩልነት ታግልው አልፈዋል የምትላቸውና እንደ ምሳሌ የምትጠቅሳቸው ሰዎች አሉህ?

እስክንድር፦ ብዙ አሉ፤ በጣም ብዙ አሉ። በአገራችን ውስጥም ሆነ በውጪ። የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑም ያልሆኑም። በግሌ በጣም የሚማርከኝ ማርቲን ሊተር ኪንግ ነው። ይህ ሰው የጻፋቸውን አንብቤ የማልጠግበው ሰው ነው። የዚህ ምክንያቴ ደግሞ ትግሉን በክርስትና መነጽር ስለሚያየው ነው። መልእክቱ ግን ለክርስቲያኖች ብቻ አይደልም፤ ለሁሉም ነው። ከእርሱ በተጨማሪ፣ ማንዴላና ጋንዲም አሉ። ማንዴላን ባላውቅም ጋንዲ ግን ክርስቲያን አልነበረም። አሁን አንተ ያልከውን መሥፈርት ግን የሚያሟላ ነው። ብዙ ምሳሌዎችን መጥራት ይቻላል። ለዚህ፣ ዓለም ደኻ አይደለችም፤ አገራችንም ደኻ አይደለችም። ችግሩ ግን የአብዛኞቹን ስም አናውቀውም። እኛ እንደ ሰው ባናውቃቸውም በእርሱ ግን ይታወቃሉ። ቁም ነገሩ ያ ነው። በጌታ የሚታወቁ በርካቶች አሉ፤ እኛ እንኳ ሁሉንም ባናውቅ።

ሕንጸት፦ እስክንድር በመጨረሻ የእስር ቆይታው አግኝቼዋለሁ ከሚለው አብርሆት በኋላ፣ ወደ ኋላ ሄዶ ‘ይህን ባላደርግ፣ ይህን ባልጽፍ’ የሚለው ወይም ‘ተሳስቼ ነበር’ የሚለው ነገር አለው?

እስክንድር፦ በጣም ብዙ አለ። ልቁጠር ብል እዚሁ መዋላችን ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም ሆነ ወደ ፊትም ይኖራል። ቅድም እንዳልኩህ እኛ እኮ ጎዶሎ ነን፤ሰው ነን። በሥራ ፍጹም መሆን አንችልም። እዚህ ዓለም ላይ ስንፈጠር ጀምሮ ጎዶሎ ሆነን፣ ኀጢአተኞች ሆነን ነው የተወለድነው፤ ከፅንስ ጀምሮ። የአዳምን ኀጢአት ይዘን ነው የተወለድነው፤ ስንሄድም የአዳምን ኀጢአት ይዘን ነው የምንሄደው። የምንጸድቀው በእርሱ ይቅርታና ጸጋ ብቻ ነው። የማልዘረዝርልህ በጣም ስለሚበዙ ነው። አሁንም ከወጣሁ በኋላ ርግጠኛ ነኝ ብዙ የፈጸምኳቸው ነገሮች ይኖራሉ። ወደ ፊትም ብዙ የምፈጽማቸው ይኖራሉ። የእኔ ዋስትና የእርሱ ይቅርታ ብቻ ነው።

ሕንጸት፦ በዚህ አጋጣሚ ያዘኑብህ ሰዎች ወይም ሊወቅሱህ የሚፈልጉህ ሰዎች ቢኖሩ ይቅርታ ትላቸዋለህ?

እስክንድር፦ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያሳዘንኩት ሰው በጣም ብዙ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ። ወደ ፊት የማሳዝናቸው ሰዎች ይኖራሉ። ለእነርሱም አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ፈጣሪዬን ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ሕንጸት፦ ቀደም ሲል እንዳልከኝ አንተ እዚህ ነው መኖር የምትፈልገው። ባለቤትህና ልጅህ ደግሞ አሜሪካን አገር ነው የሚኖሩት። ወደዚህ ይመጣሉ ወይስ …?

እስክንድር፦ ለልጄ ልሰጠው የምችለው ትልቁ ነገር ሀብት አይደለም። ገንዘብ የለኝም፤ ቢኖረኝም ግን ቁም ነገሩ እሱ አይደለም። የክርስትና እምነቴን ነው። አያቴ ለእኔ እንደ ሰጡኝ ማለት ነው። ይህንን አሁን እንዳለነው ተራርቀን ልሰጠው አልችልም። ያለፉት ስድስት ዓመታት ጠፍተዋል። ሰርካለም [ባለቤቱ] እየሞከረች ነው። እኔ ግን በዚያ ላይ ማገዝ ብችል ደስ ይለኛል። ይህን ለማድረግ አንድ ላይ መኖር አለብን። ይህንን ለማድረግ ግን እዚህ አገር ውስጥ ያለው ሁኔታ መረጋገጥ አለበት። ሰርካለም እዚህ የተመለሰች እንደ ሆነ፣ እሷም እኔም አንድ ላይ እስር ቤት እንገባለን ማለት ነው። ይሄ ከሆነ ደግሞ ልጁ መንገድ ላይ ይወድቃል። ሁለታችንን ደግሞ በአንድ ጊዜ ማጣት የለበትም። ስለዚህ አገር ውስጥ ያለው ሁኔታ በየት አቅጣጫ ይሄዳል የሚለው ሳይጣራ ወደዚህ መመለስ አይችሉም። ለዚህ ደግሞ እኔ ትልቁ መሥፈርት የምለው የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ነው። ሁሉንም፣ ዋና ዋና የፖለቲካ ድርጅቶች ያቀፈ የሽግግር መንግሥት መመሥረት ከቻልን እነርሱ ይመለሳሉ።

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ 
ያሳዘንኩት ሰው በጣም ብዙ 
ነው ብዬ አስባለሁ፤ 
ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ።

እግዚአብሔር ፍቃዱ ከሆነ የጌታን ቃል ለልጄ ወይም ለልጆቼ (እግዚአብሔር ለዚያ ካደለኝ) ለማካፈል ዕድሉን አገኛለሁ። ያ ካልሆነ ግን እኔ እዚህ ቃል አለብኝ፤ እንደ ቤተ ሰብ የገባነው ቃል አለ። ትግሉን ትቼ መሄድ አልችልም። እኔ እዚህ እታገላለሁ፤ ቤተ ሰቤ እዚያ ይቆያል። ተለያይተን ለመኖር እንገደዳለን ማለት ነው።ሕንጸት፦ በቀጣይ ምን ልተሠራ አስብሃል?

እስክንድር፦ አክቲቪዝም እና ሚዲያ ላይ እሠራለሁ። መጽሔት፣ ቴሌቪዥን እንዲሁም ኢንተርኔት ላይ ለመምጣ ነው የማስበው። እንግዲህ አሁን የተገናኘነው ቢሮ ውስጥ አይደል? ይህንን ሥራ ለማስጀመር ይህችን ሦስት በሦስት የሆነች ጠባብ ቢሮ ተከራይተናል። ጉዞውን ጀምረናል፤ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ነን።

ሕንጸት፦ መታወቅ የምትፈልገው በአክቲቪስተነትህ ነው ወይስ በጋዜጠኝነትህ? የትኛው ያይልብሃል? 

እስክንድር፦ አክቲቪዝሙ ግዴታ ነው። ዴሞክራሲ እስከሌለ ድረስ ጋዜጠኛ መሆን አትችልም፤ ጋዜጠኛም እንድትሆን ሁኔታዎች አይፈቅዱልህም። ስለዚህ ዴሞክራሲ እስከሌለ ድረስ አክቲቪዝሙና ጋዜጠኝነቱ ጎን ለጎን የሚሄዱ ናቸው። ምናልባትም አክቲቪዝሙ ሊጎላ ይችላል። ዴሞክራሲያዊው ሥርዐት ካለ ግን፣ በዋናነት ማንነቴም፣ ሰብእናዬም ጋዜጠኝነቱ ነው የሚሆነው። የአንድ ፓርቲ የበላይነት አገሪቱ ውስጥ እስካለ ድረስ፣ የኢህአዴግ የበላይነት እስካለ ድረስ አክቲቭዝሙ የግድ ነው። ይሄ ሁኔታ ከተቀየረ አክቲቪዝሙ ጡረታ ይወጣል ማለት ነው።

ሕንጸት፦ ለዚህ ቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ሆነህ ጊዜህን ስለሰጠኸን በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር ያክብርህ!

እስክንድር፦ የእናንተ እኔን ያስቀናኛል። ጌታን ነው የምታገለግሉት። ስለዚህ ከእኔ የበለጠና እጅግ የገዘፈ ዋጋ ያለው ሥራ ነው የምትሠሩት። እናንተ በዚህ ሥራችሁ ሂደት ውስጥ እኔ ጋ መጥታችሁ ይህንን ቃለ ምልልስ ስላደረጋችሁ እግዚአብሔር ያክብራችሁ። እንደውም እናንተ አለነበራችሁም እኔ ጋ መምጣት የነበረባችሁ፤ እኔ ነኝ እናንተ ጋ መምጣት የነበረብኝ። እሱን ባለማድረጌ ይቅርታ እጠይቃለሁ። አመሰግናለሁ !

Source ፡ hintset

Comments are closed.