Take a fresh look at your lifestyle.

ታላቁ ሩጫ ኤርትራዊውን አትሌት ዘረሰናይ ታደሰን ሊጋብዝ ነው ።

256

ጥቅምት 21 – ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለሚያካሂደው የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ የሩጫ
ውድድር ድምቀት የሚሰጡ የክብር እንግዶችን ከተለያዩ ሃገራት ይጋብዛል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተለይ በረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች ከፍተኛ ውጤቶችን ያስመዘገቡና ታዳጊ አትሌቶች እንዲሁም ተሳታፊዎች ሊያዩዋቸው የሚጓጉላቸውን አትሌቶች በመጋበዝ ሩጫው ላይ ከተለያዩ የሚዲያ አካላት ጋር እንዲገናኙ፤ ደማቁ ታላቁ ሩጫ ላይ ተካፋይ እንዲሆኑ እድል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ቀደም ከመጡ የክብር እንግዶቻችን ውስጥ የሴቶች ማራቶን ሪከርድ ባለቤቷ ፓውላ ራድክሊፍ፤ የረጅም ጊዜ የሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ ተፎካካሪና ጓደኛ ኬንያዊው ፖል ቴርጋት፤ የቅርብ ዘመን የጥሩነሽ ዲባባ እና መሠረት ደፋር ተቀናቃኝ ቪቪያን ቼሮይት እንዲሁም የቀድሞዋ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮኗ ሆላንዳዊቷ ሎርናህ ኪፕላጋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በዘንድሮው ሩጫ ላይም ታዋቂው እና ከኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ጋር ታሪካዊ ፉክክሮችን ያደረገው ኤርትራዊው አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ መሆኑን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡ ከዘረሰናይ በተጨማሪም የአለም ሻምፕዮን ማራቶን ወርቅ ሜዳልያ ባለቤት ኡጋንዳዊው ስቲቨን ኪፕሮቲችም ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ.ሜ ዓለም አቀፍ ውድድር በክብር እንግዳነት ይገኛል፡፡ ከክብር እንግዶቹም በተጨማሪ በአትሌቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር ከኬንያ፤ ከኡጋንዳ፤ ከኤርትራ እና ከሌሎችም አገሮች የሚመጡ ተፎካካሪዎችን የሚያስተናግድ በመሆኑ ውድድሩን አጓጊ እንደሚያደርገው ይህም የአትሌቶች ውድድር የወንዶቹ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት እንዲሁም የሴቶቹ 2፡10 የሚጀመር ሲሆን ከ2፡00 – 4፡00 ሰዓትም በቀጥታ ስርጭት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደሚተላለፍ የ2011 ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትየጵያ አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡

Comments are closed.