ሞቶ የተገኘውና ወላጆቹ አልቅሰው የቀበሩት ወጣት ከሳምንታት በኋላ ወደ ወላጆቹ ተመለሰ

ሞተ የተባለው ሰው አልሞትኩም ብሎ መጣ!

• ሞቶ የተገኘውና ወላጆቹ አልቅሰው የቀበሩት ወጣት ከሳምንታት በኋላ ወደ ወላጆቹ ተመልሷል፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ሕዳር 19 ቀን 2011ዓ.ም በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አስተዳደር አንድ ወጣት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድሎ ይገኛል፡፡ ይህም ከፖሊስ ጆሮ ይደርሳል፡፡
ጉዳዩን የሰማው ፖሊስ የሟችንም ሆነ የገዳይን ማንነት ለማወቅ ያደረገው ጥረት ለጊዜው ሳይሳካለት ይቀራል፡፡ የወንጀሉ መርማሪ ሳጅን አየነው ጎበዜ እንዳሉት ማንነቱ ያልታወቀውን ሟች ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ወደ ቆቦ ሆስፒታል ይወስዱታል፡፡

ነገር ግን ሐሙስ ሕዳር 20 ቀን 2011ዓ.ም ከሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ 02 ቀበሌ ገረገራ አካባቢ ከምሽቱ 5፡00 አቶ ታረቀ መንግሥቴ የተባሉ ሰው ወደ ፖሊስ በመሄድ ‹‹ሟች የእኔ ልጅ ነው›› በማለት በኮንትራት መኪና አስከሬኑን መውሰዳቸውን ሳጅን አየነው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

አቶ ታረቀ ልጃቸውን ከቀበሩ በኋላ ሕዳር 24 ቀን ወደ ቆቦ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በመሄድ ክስ መመሥረታቸውንና የልጃቸው ገዳዮች እንዲነግሯቸው መጠየቃቸውንና ፖሊስ በግድያው ዙሪያ የደረሰበትን ለአባት መንገሩን ሳጅን አየነው አስረድተዋል፡፡
አባት አስከሬኑን ሊረከቡ በመጡበት ጊዜ ስለልጃቸው የሚያውቁትን ልዩ ምልክት ተጠይቀው እንደተናገሩና የሟቹን ፎቶግራፍ ሲያዩ በጣም እንዳለቀሱ፤ እንዳጽናኗቸውም መርማሪ ፖሊሱ ተናግረዋል፡፡

የልጃቸውን አስከሬን ከፖሊስ ተቀብለው ሌሊቱን ሲጓዙ ያደሩት አቶ ታረቀ ሕዳር 21 ቀን 2011ዓ.ም ወዳጅ ዘመድ እያስተዛዘናቸው በፍላቂት ገረገራ ደብረ ሃይማኖት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩን ያስፈጽማሉ፡፡
‹‹ቆቦ ሰው መሞቱንና የመቄት ሰው ነው መባሉን ስሰማ አጣራሁ፤ ሊቀበር መሆኑን ስሰማም ለማጣራት ሄድኩ፡፡ ደርሼም አስከሬኑን አገላብጨ አየሁ፤ ልጄ ነው፡፡ አምጥቼ ከዘመድ ወዳጅ ጋር ሆኜ ቀበርኩ፡፡ ሥርዓተ ፍትሐቱንም አስፈጸምኩ፤ ሳልስት፣ ሰባት አስቀደስኩለት፡፡ ሰላሳውን ላስቀድስ እየተዘጋጀሁ ሳለ ግን ነገሮች ተቀዬሩ›› ብለዋል አቶ ታረቀ መንግሥቴ ለአብመድ ሲናገሩ፡፡
‹‹ድንገት ስልክ ተደወለ፤ አነሳሁት፡፡ ‹ሞቷል ብላችሁ እንዳለቀሳችሁ ሰምቻለሁ› ብሎ ልጀ ደወለ፡፡ እሱ መሆኑን ስላላመንኩት የተለያዬ ዘመድ እንዲጠራ አደረኩት፤ ተጠራልኝ፡፡ ከዚያም ወደ ቤተሰቡ መጣ›› ብለዋል አባት፡፡

በወቅቱ የሟችን አስከሬን ሲያዩ ከእጁ ጣት ላይና ከጥርሱ ልዩ ምልክትን መሠረት አድርገው ልጃቸው መሆኑን እንዳረጋገጡ የገለጹት አባት ስለተፈጠረው ነገር ተገርመዋል፡፡
‹‹ሞቷል›› ተብሎ የተለቀሰለት አበበ ቤተሰቦቹ ለማመን መቸገራቸውን ገልፆ ‹‹ከሟች ጋር እንዴት እንደተመሳሰልኩ ገርሞኛል፡፡ ለማንኛውም አሁን በወላጆቼ ፊት በመገኜቴና በሕይወት በመሆኔ ደስተኛ ነኝ›› ብሏል፡፡
ምንጭ ፡ አማራ መገናኛ ብዙሃን