ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፤ የ2011 በጀት ዓመት የአምስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለ5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ስብሰባ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ተቋሙ በሚመጡ ጥቆማዎች ከአንድ ቤተሰብ ብቻ ከአራት በላይ የቤተሰብ አባላት እንደተያዙ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ተቋሙም ይህን መነሻ አድርጎ የማጥራት ሥራ ቢሠራም ግለሰቦቹ ሲያዙ የፍርድ ቤት ትዕዛዝም ሆነ ያዢው ማን እንደሆነ በውል ባለመታወቁ ሥራውን በሚፈለገው ደረጃ ለማከናወን ተቸግሯል፡፡
በከባድ የአገር ሀብት ምዝበራ ወንጀልና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ከተያዙ ግለሰቦች ውጪ አሁንም በመንግሥት የሥራ ኃላፊነትና በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ በተደራጀ ሁኔታ የተቀነባበሩ በመሆናቸው ምርመራውን አዳጋችና ተጠርጣሪዎችን ወደ ሕግ የማቅረብ ሂደቱን ፈታኝ አድርጎታል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ከአገር ውጭ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በኢንተርፖል እየመጡ ከአገር ውስጥ ግን ተሸሽገዋል የሚባሉትን ስለምን መያዝ አዳጋች ሆነ? በዚህ መንገድስ የህዝብ አመኔታ ማግኘት ይቻላል ወይ? ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ አለማድረግስ የችግሩን ዕድሜ አያራዝመውም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና አባላት ተነስተዋል፡፡ በተመሳሳይ ክልሎች በወንጀል ተጠይቆ ይፈለጋል የተባለ የለም በሚል ካለም አሳልፈው እንደሚሰጡ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎችን የደበቁ እንዳሉ ይገልፃልና ይህ እንዴት ይታያል? ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተደበቁ ተጠርጣሪዎች በሌሉበት የሚታይበት አግባብ ላይ እንዲሁም የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ምክትል ለሕግ ቀርበው ጉዳያቸው ሲታይ ግብረአበራቸው በሚል ስማቸው ይነሳልና ያለመከሰስ መብት አላቸው ወይ?፣ ምንም እንኳ በአገሪቱ በነበረው የአመራር ሂደት ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጣ ቢሆንም ተጠርጣሪዎችን የመያዙ ጉዳይ ግን ብሔር ተኮር እንደሆነ ይነሳልና ከዚህ አንፃር በእኩል ደረጃ ተጠያቂ ማድረግ ጋር ተያይዞ ምን እየተሠራ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ጥያቄዎቹ ትክክለኛና ተገቢ እንደሆኑ በመግለጽ፤ መንግሥት ሕግን መሠረት አድርጎ ተጠያቂ የማድረግ ተግባሩን እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከተሸሸጉ ተጠርጣሪዎች ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሻቸውን ሲሰጡም አንዳንዶቹ ቦታቸውን በመለዋወጥ፣ የተወሰኑት ደግሞ ያሉበት የማይታወቅ ሲሆን፤ ከአገር ውጭ ያሉትን ግን በመነጋገር ወደ አገር እንዲመጡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር ተያይዞ ያለመከሰስ መብት አላቸው በሚል ለተነሳው ጥያቄ ግለሰቡ የፌዴራልም ሆነ የክልል ምክር ቤት አባል አለመሆናቸውን በመግለጽ ያለ መከሰስ መብት የሌላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የተሸሸጉትም በክልሉ ውስጥ ቢሆንም እርሳቸውን ለመያዝ ግን በተኩስ መሆን አለበት ብሎ መንግሥት አያምንም ብለዋል፡፡ ክልሎች ወንጀለኛ ተብሎ የተጠየቁት እንደሌለና አሳልፈው እንደሚሰጡ የሚያነሱትም ትክክል አይደለም፡፡ ይልቁንም በደብዳቤ ጭምር የተጠየቀ በመሆኑ ይህን መሠል ምላሽ የሚሰጠው ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› ሆኖ ነው ሲሉ ድርጊቱ ሆነ ተብሎ እየተፈፀመ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከብሔር ተኮር ተጠያቂነት ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ በከፍተኛ አመራር ቦታዎች ላይ አብላጫውን ቦታ ይዞ የነበረ ብሔር ተጠያቂ ሲደረግ ሊያዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህን ለማሟያ በሚል ሌሎችን የማካተት ሥራ አይሠራም፡፡ ተጠያቂነቱ ወንጀል ተፈጽሟል አልተፈፀመም? የሚለውን እንጂ በፖለቲካ አቋምና በብሔር አለመሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ በመሆኑም በሁሉም ክልሎች ወንጀለኞችን የሚሸሽጉ አካላትን አጋልጦ ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ፣ የፖለቲካ አመራርና የምክር ቤቱም ነው ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/20111