በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ መዓሾ ኪዳኔና አቶ ሀዱሽ ካሳ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ መዓሾ ኪዳኔ እና አቶ ሀዱሽ ካሳ ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10 የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።
በፍርድ ቤቱ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራር ናቸው የተባሉት አቶ መዓሾ ኪዳኔና አቶ ሃዱሽ ካሳ፥ ጠበቃ ለማቆም አቅም የለንም ማለታቸውን ተከትሎ መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው በመሃላ አረጋግጠዋል።
መርማሪ ፖሊስ 1ኛ ተጠርጣሪ አቶ መዓሾ ኪዳኔን ከኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር ተመሳጥረው ያለአግባብ በማሰርና በመደብደብ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በመፈፀም የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማድረስ እና ያለአግበብ ሶሰት መኖሪያ ቤቶችን በማፍራት እንደጠረጠራቸው ገልጿል።
ተጠርጣሪው አቶ መዓሾ በበኩላቸው በፖለቲካዊ ውሳኔ ብቻ መታሰራቸውን ጠቁመው፥ ከዚህ በፊት በታታሪነት የተሸለሙና አሁን በቱርክ ኢስታንቡል በዲፕሎማትነት መሾማቸውን በማንሳት፥ ያሰሩትም ሆነ የበደሉት እንደሌለ አስረድተዋል።
2ኛ ተጠርጣሪ አቶ ሃዱሽ ካሳ ላይ በተመሳሳይ ፖሊስ ያለአግባብ ዜጎችን በማሰር፣ በመደብደብ እና ተገቢ ያልሆነ ሃብት በቤተሰቦቻቸው ውክልና በመስጠት አካብተዋል ብሎ መጠርጠሩን ለችሎቱ አብራርቷል።
1ኛ ተጠርጣሪ አቶ መዓሾ እኔ በዳይሬክተር ደረጃ ስራዎችን በማስተባበር የኦፕሬሽን ዘርፍ ሰራተኛ ሃላፊ እንጂ አሳሪ አይደለሁም ብለዋል።
2ኛ ተጠርጣሪ አቶ ሃዱሽ ካሳ በበኩላቸው እኔ ሃላፊነቴ የጽዳት የተሽከርካሪ እና የአትክልት ስራ ቁጥጥር እንጂ የማሰርም ሆነ የማሰቃየት ሃላፊነት የለኝም ይህ እኔን ለማጥቃት ያለመ ነው ብለዋል ለችሎቱ።
ከዚህ ባለፈም ልጆቻቸው በአንድ ኮንዶሚኒየም እንደሚያድጉ ጠቅሰው 10 ሺህ ብር በብርበራ ተወስዶብኛል አቅም የለኝም ዋስትና ይፈቀድልኝ ሲሉ ጠይቀዋል።
2ኛ ተጠርጣሪ በ29 አመሻሽ ላይ በብሄራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ በስራ ላይ ሆነው መያዛቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ደሞዛችን ለልጆቻችን ቢከፈልልን ሲሉም ጠይቀዋል ችሎቱን።
ፖሊስ በበኩሉ በ1ኛ ተጠርጣሪ አቶ መዓሾ ላነሱት ትግሬ በመሆኔ ባሉት ጉዳይ እኛ ትግሬ በመሆናቸው ሳይሆን ህገመንግስትን ለማስከበር፣ በሰውና በሰነድ ማስረጃ መያዛችንን ፍርድ ቤቱ ይመዝግብልን፤ እኛ ህግ አስከባሪ እንጂ የፖለቲካ አስፈጻሚ አይደለንም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
1ኛ አቶ መዓሾ ሃላፊነት የለኝም ያሉት ሃሰት ነው ያለው ፖሊስ ግለሰቡ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ልዩ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር እንደነበሩ ጠቅሶ፥ 2ኛ ተጠርጣሪ አቶ ሃዱሽ ካሳን በተመለከተ ፖሊስ የስራ ሀላፊነታቸውን በተመለከተ በቀጣይ ማስረጃ እናቀርባለን ብሏል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ ነገ ጠዋት የፖሊስን የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ከሰዓት ትዕዛዝ ለመስጠት በይደር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪዎች ያነሱትን የደሞዝ ጥያቄ ለፖሊስ በማመልከቻ እንዲያቀርቡም አዟል።
በታሪክ አዱኛ