ኦነግ በቃል አቀባዩ በአቶ ቶሌራ ዳባ አማካኝነት እንዳስታወቀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፡ በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ መዝገብ በ1983 ዓ.ም በሕግ ስለተመዘገበ አሁን ድጋሚ አይመዘገብም ሲል ያቀረበውን አቤቱታ አዲሷ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ውድቅ አድርገውታል ።
አዲስ ፓርቲ አይደለሁምና ድጋሚ መመዝገብ የለብኝም ሲል መከራከሪያ ይዞ የቀረበው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ያቀረበውን አቤቱታ የተመለከተው የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የኦነግን በድጋሚ አልመዘገብም የሚል መከራከሪያ ውድቅ በማድረግ በድጋሚ እንዲመዘገብ ጥሪ አቅርቦለታል ። በተያያዘ ዜና ቀጣዩን ምርጫ በኤሌክትሮኒክስ መርጃ መሳሪያዎች ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል ። ይህን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ምርጫውን ፍፁም ተአማኒ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልፀው ከነዚህም መካከል አለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ የምርጫ ማከናወኛ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት እንደታሰበ ገልፀዋል ። እንዲሁም ተቋማዊ የሰው ሃይልንና ተጓዳኝ መርጃ መሳሪያዎችን በተመለከተ የሚደረጉ የሪፎርም ስራዎች ለማድረግ እቅድ መነደፉን የገለፁት ወ/ሪት ብርቱካን በምርጫ ቦርድ ላይ የነበሩት የኢ- ተአማኒነት ጥያቄዎች ለመቅረፍ ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ አስታውቀው በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ይገባዋል ብለዋል ።