ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በፈረንሳይ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው

1 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአውሮፓ የሚያደርጉትን ይፋዊ የስራ ጉበኝት በዛሬው እለት ጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ጉብኝታቸውን በፈረንሳይ የጀመሩ ሲሆን፥ በዛሬው እለትም ፓሪስ ገብተዋል።

ፓሪስ ቻርለስ ደጎል አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም በፈረንሳይ የኢፌዴሪ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አሊ ሱሌይማንን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች እና በርካታ ኢትዮጵያውያን አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የፈረንሳይ መንግስት ልዑካን አባላትም አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አሁን ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤልዜ ቤተ መንግስት ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር እየተወያዩ ነው።

የሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ አካባቢያዊና አለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች የውይይታቸው ዋነኛ አጀንዳ ይሆናል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በሃገራቱ መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትም የመወያያ ነጥባቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።

መሪዎቹ ከውይይታቸው በኋላ የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶችን ይፈራረማሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው።

በመቀጠልም በነገው እለት ወደ ጀርመን የሚያቀኑ መሆኑም ታውቋል።

በጀርመን ቆይታቸውም ከሀገሪቱ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክልና ከሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀርመን ከተመረጡ ግዙፍ የጀርመን ኩባንያዎች ጋርም እንደሚወያዩ ነው የተገለጸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጀርመን ቆይታቸውም ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ከሚውጣጡ 25 ሺህ ኢትዮጵያውያን ጋር በፍራንክፈርት ይወያያሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ጉብኝት “አንድ ሆነን እንነሳ ነገን በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ መሆኑም ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን የሚያደርጉት በሀገራቱ መሪዎች በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ነው።

በሰለሞን አለሙ