Take a fresh look at your lifestyle.

በሶሻል ሚዲያ ውዝግብ ስላስነሳው የቀዳማዊ ሃ/ስላሴን ሃውልት በተመለከተ ቀራፂው መልስ ሰጠ

1,376

ስለማክበር ሲባል የተፃፈ

የፌስ ቡክ ላይ እሰጥ አገባ፡ ባለመፈለግ በሰሞኑ የጃንሆይ ሀውልት ውዝግብ ላይ ዝምታን መርጨ ነበር ። ሆኖም በርካታ፡ብዙሃን መገናኛ አውታሮች እየደወሉ ቃሌን ስላስተጋቡት እንዲሁም አብላጫው ትችት ሰንዛሪ ምንነቱን ባላየውና፡ባላስተዋለው ጉዳይ በቅንነት ድፍረት ብቻ፡ እየተቀባበለ ከግራ፡ቀኝ የሚወራወር መሆኑን ስለተገነዘብኩ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ የሚከተለውን ማስገንዘቢያ ፡ ብፅፍስ ብዬ አሰብኩ ።
በመሰረቱ ለአደባባይ ያበቃኸውን ማናቸውንም ቁስ ማንም ያገባኛል ባይ ባቅሙና በተረዳበት ደረጃ፡በመሰለው መንገድ የሚሰጠው አስተያየት ሊከበር ይገባል ። በሰሞኑም የሆነው ይኸው ነው። ጃንሆይ ሀውልት አይገባቸውም ከሚለው ፅንፍ ሀውልቱ እርሳቸውን አይመስልም እስከሚለው ድረስ የተባለውን ሰብስበን ለመመዘን ሞከረን ነበር።( ሀውልቱ ስራ፡ ላይ የተሳተፍነው ማለቴ ነው ።) ጃንሆይ ሀውልት አይገባቸውም የሚለው ሩቅ አማራጭ በሀገሩ ላይ የሀሳብ ነፃነት ማመልከቻ ስለሚሆን እንደተከበረ እንደተደመጠ እንለፈው ።ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረትና፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከአብላጫው/አሸናፊ ካሉት ሀሳብ ጋር ቆመው መሰራቱን ሰለወሰኑ። የተረፈውንና አስፈላጊ መስሎ የታየንን ሶስት መሰረታዊ ጥያቄ ግን እንደሚከተለው አፍታተነዋል ።

  1. መልኩ ጃንሆይን አይመስልም። ይህ አስተያየት ለደቂቃም ቢሆን ሊያጨቃጭቅ አይገባም ። ሀውልቱ ካልመሰለ እንዲመስል መደረግ አለበት ከመሰለ ደግሞ መስሎ መቀጠል አለበት ። ይህንኑ በማሰብ ምን ጎደለ ብለን ራሳችንን በመጠየቅ ላይ ሳለን አስተያየቱ ከየትና፡እንዴት እንደተሰነዘረ ሲነገረን ለጥያቄው መልስ በመስጠት መድከሙን አቆምነው። መልኩ አልመሰለም ባዮቹ በጠቅላላ ንጉሱንም ሆነ የተሰራውን ሀውልት ለደቂቃ ባይናቸው አይተው የማያውቁ መሆኑን አረጋገጥን። ታዲያ፡ከየት የመጣ ውርጅብኝ ነው ስንል መነሻው ሁለት አየር ላይ የሚሯሯጡ ፎቶግራፎች መሆናቸው ተነገረን። አንደኛው ፎቶ ስራው ገና፡ የጭቃ ሞዴል ሂደት ላይ ሳለ ከድንገተኛ ጥግ በስርቆሽ የተነሳ የጭቃ ምስል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በምረቃው ቀን ከሃያና ሰላሳ ሜትር ላይ በሞባይል ከርቀት የተነሳ የሰለለ አካል ብቻ የሚያሳይ ሆነው አገኘናቸው። ብቻ ሞተ ሲሉ ተቀበረ ሆነ ነገሩ ። ባጭሩ አሁንም ስለ ሀውልቱ ምንም ዓይነት ትችት መሰንዘር የሚከበር ነገር ሆኖ በተበላሸና ምስሉ በሰለለ ፎቶ ለመዳኘት ከመድፈር በፊት መቸም ጃንሆይ ዛሬ የሉም እንደምንም መጀመሪያ ሀውልቱን ቀርበው ባይናቸው ቢያዩት እላለሁ ። ሀውልትን ባይንና፡በምስል ማየት የሚያጎድለው ብዙ ነገር አለ ።አንዱም ግርማ ሞገስ የሚሉ ሰዎች ከፎቶ ላይ የሚያጡት ነው ። ካልቻሉ ጅምር ስራና፡መናኛ ምስል ላይ ከመመስረት ለምሳሌ ደህና፡ ደህና፡ ፎቶግራፈሮች ያነሱትን መመልከትና፡መተቸት ይመረጣል። ለምሳሌ የቢቢሲውን ድረ ገፅ ለምሳሌ እዚህ ለጥፌዋለሁ።
  2. ለምን በዚህ ልብስ ተቀረፁ ?

ይህ ጥያቄ ከላይኛው የተሻለ ነው ለምን ቢያንስ ታስቦ የተጠየቀ በመሆኑ ። የአፍሪካ፡ህብረትና፡የኢትዮጵያ፡መንግስት ይህንን ሀውልት በአፍሪካ፡ህብረት ግቢ እንዲቆም የተስማሙት ጃንሆይ ከፈፀሙዋቸው አያሌ ገድሎች መካከል አፍሪካን ለማስተባበርና፡አንድ ለማድረግ ለታገሉት ለይቶ ለመዘከር መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ይመስለኛል ።ይህ በተለይ የተሰራበት ዓላማ ጃንሆይን ሌላ ነገር አልሰሩም ለማለት ሳይሆን ለዚህ ለሚቆምበት ቦታ ፡የተመረጠበት የተተኮረበት ገድላቸው ነው ። አፍሪካን ለማስተባበር ወጥተው በወረዱበት ዘመን ሁሉ ጃንሆይ ይለብሱ የነበረው ሁሌም ጥቁር ወይም ግራጫ፡ ሱፍ በክራቫት ብቻ፡ነው። በአፍሪካ ህብረት እንግዳ፡ሲያስተናግዱም ሆነ ሲስተናገዱ አቁዋቁዋማቸውና፡ እጆቻቸው ሁሌም በዚህ መልክ ተመዝቦ የሚታወቅ መሆኑን ቤተሰባቸውን ጨምሮ በሁሉም ዘንድ ምክክር ከተደረገበት በሁዋላ የተወሰነ ነው። እርግጥ፡ ነው ንጉሱ ብዙ የሚያምር ልዩ ልዩ ጌጥ ያለው ልብስና፡አቁዋቁዋም አላቸው ። እሱን ለራሳችን ስሜትና ከተማ ስንቀርፅ የምንመርጠው ይሆናል።መቸም ይሄ ሀውልታቸው የመጨረሻው አይመስለኝም።

  1. ሀውልቱ ለምን የዚህ ዓይነት መልክ ያዘ ?

አደባባይ የሚቀመጥ ፡ሀውልት በዓለም ዙሪያ ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ ባብዛኛው በነሀስ መስራት የተለመደና፡ የተመረጠ ነው ። ለምን ቢሉ ቢያንስ ለሶስት ጉዳይ አንድ በጣም ጠንካራ፡የብረት ዘር በመሆኑ ሁለተኛ፡ ተፈላጊውን ቅርፅ ለማስያዝ ለስራ፡አመቺ በመሆኑ ሶስተኛ ከአካባቢው ጋር በጊዜ ውስጥ፡ የሚመሳሰልና፡በመልኩ የማይረብሽ በመሆኑ ። ስለሆነም ባደባባይ ሲቀመጥ በየቀኑ ተላላፊው ተመልካች ሁሌም እንዲወደው ፓቲኔት ይደረጋል። ያደባባይ ሀውልት እንደሜዳሊያና እንደ ዋንጫ ተብለጭልጮ አይቀመጥም። ወይም ማናቸውንም ዓይነት ቀለም አይቀባም።በፍፁም። ፓቲኔት ይደረጋል ማለት በተመረጠ አሲድ በከፍተኛ የወላፈን እሳት (ብዙ ጊዜ ከ800 ዲግሪ ሴልሸስ ባልበለጠ ) እየተለበለበ ነሀሱ ከያዘው አብላጫ የመዳብ ይዘት ጋር ኦክሲጂንን እንዲቀላቅል ይደረጋል ። በዚህም ሰማያዊ አረንግዋዴ መልክ ወይም ያረጀ ሳንቲም እንዲመስል ይሆናል።በዓለም ላይ ይህ የተለመደ ነው። ለምሳሌ ሁሉም የሚያውቀው የኒውዮርኩዋ የሊበርቲ ሀውልት በዕድሜ ብዛት ወደዚህ ሰማያዊ አረንጉዋዴ መጥታለች። አዲስ የነሃስ ሀውልትም በዚህ ዓይነት የአሲድ ፕሮሰስ የአንቲክ ስሜት ተሰጥቶት ራሱ ደግሞ በጊዜ ብዛት አያደር ከአየር ኦክሲጂን እየተሻማ፡እንደሊበርቲ የማማሩን ዕድል ያፋጥንለታል። ውበት ማለት ላደባባይ ሀውልት እንዲህ ለነገም ለዛሬም የሚታሰብ እንጂ እንደ ስጦታ ዕቃ መብለጭለጭ የለበትም ወይም መቀባት የለበትም። የሙያው ዲሲፕሊን ይህንን ያስተምራል ። ይመክራል። ስለሆነም በላዩ ላይ ያለውን ቀለም በዚህ መንገድ ብታስቡት አንወዳለን። ይህንን ባህል የተላመዱት በውጭ የሚኖሩ የንጉሱ ቤተ ዘመዶች በምረቃው ላይ ረክተው በደስታና፡በምስጋና፡ተለያይተናል። የሁሉንም አስተያየት አከብራለሁ ግን ሁሌም ከሃላፊነትና ከጨዋነት ጋር ቢሆን ለሁላችን ይጠቅማል። ያዘመመ ዛፍ ተገኘ ሲባሉ ፈጥነው ለመገርሰስ መጥረቢያ ስለው የሚጠብቁ ብዙ እንዳሉ ሰሞኑን ታዝበናል ።ለነገሩ ባንድ ቀን ያልበቀለ ዛፍ ባንድ ቀንና የሚገረሰስ መስሏቸው ነዋ አመሰግናለሁ።

Comments are closed.