Take a fresh look at your lifestyle.

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች የአክሲዮን ባለቤት ሊሆኑ ነው ።

931

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ ባስገነባው የኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል ሠራተኞቹ የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት እንዲሆኑ እንደወሰነ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ግሩፕ እሑድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ ፕሮጀክትና ያስገነባውን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ባስመረቀበት ወቅት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ባሰሙት ንግግር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደረሰበት የስኬት ደረጃ የበቃው ከ16,000 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞቹ በትጋት በመሥራታቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የሠራተኛውን የባለቤትነት ስሜት ለመጨመር የአየር መንገዱ ሠራተኞች በስካይላይት ሆቴል የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት እንዲሆኑ፣ ማኔጅመንቱና የዳይሬክተሮች ቦርድ እንደወሰኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሠራተኞቻችን ይህን ወርቃማ ዕድል እንዲጠቀሙበት ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በ65 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በ42,000 ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው ስካይላይት ሆቴል 373 የመኝታ ክፍሎች፣ የተለያየ መጠን ያላቸው የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ሦስት ምግብ ቤቶች፣ ሦስት ቡና ቤቶች፣ የጤና ማዕከል፣ የመዋኛ ገንዳ፣ አነስተኛ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳና ሌሎች በርካታ የሆቴል አገልግሎቶች አሟልቶ የያዘ ነው፡፡

አየር መንገዱ በሁለተኛ ምዕራፍ የሚገነባው ሆቴል 627 ክፍሎች እንደሚኖሩትና 150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ ተገልጿል፡፡

አየር መንገዱ ለሠራተኞቹ ግዙፍ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ቀርፆ ተግባራዊ በመሆን ላይ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ተወልደ 1,200 ቤቶች ተጠናቀው ሠራተኞች መረከባቸውን ገልጸው፣ 12,000 የመኖሪያ ቤት አፓርትመንቶች ገንብቶ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደሚያስረክብ ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃና ስካይላይት ሆቴልን በክብር እንግድነት መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አየር መንገዱ የገነባቸውን የአቪዬሽን አካዴሚ፣ የጥገና ማዕከል ተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ አየር መንገዱ በገነባቸው ዘመናዊ የአቪዬሽን መሠረተ ልማቶች መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በየአገሩ ስንሄድ የማየውን አገሬ ላይ እንዳይ ስላደረጋችሁኝ አኩርታችሁኛል፤›› ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ ጠንካራ የማሠልጠኛ ተቋም፣ የጥገና ማዕከልና የካርጎ ተርሚናል መገንባቱን ጠቁመው የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ እንዲገነባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተገኙት ስኬቶች ሳይዘናጉ ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዲያስቡ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ 100 ሚሊዮን መንገደኞች የሚያስተናግድ ግዙፍ ኤርፖርት እንዲገነቡ አሳስበዋል፡፡

መላ የአየር መንገዱን ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ያመሠገኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄና ለአቶ ተወልደ ልዩ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ ኩባንያው የሠራተኞቹ የአክሲዮን ባለቤት እንዲሆኑ መጋበዙ ሠራተኞች ተቀጣሪ ብቻ ሳይሆኑ ባለቤት ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ ለሌሎች ተቋማትም ትምህርት የሚሆን ዕርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሙስሊም፣ ክርስቲያን ሳንል እንዲህ ያለ ያማረ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ አየር መንገዱን ወደ ኋላ መመለስ የለበትም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ መንግሥት በአየር መንገዱ ማኔጅመንት ሥራ ጣልቃ እንደማይገባ ይልቁንም የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከአራት ዓመት በፊት ግንባታውን በ245 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስጀመረው የአዲስ አበባ ኤርፖርት ተርሚናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት፣ በሒደት በተካተቱ ተጨማሪ ሥራዎች ወጪው ወደ 363 ሚሊዮን ዶላር አድጓል፡፡

ግንባታው በሦስት ምዕራፍ ተከፈሎ የሚካሄድ ነው፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ የምዕራብና ምሥራቅ ክንፍ ሕንፃ ግንባታ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ የቪአይፒ ተርሚናል ግንባታና ሦስተኛ ምዕራፍ የአገር ውስጥ ተርሚናል ማስፋፊያ ናቸው፡፡ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎችና የመዳረሻ መንገዶች ግንባታ በፕሮጀክቱ ተካተዋል፡፡

የዋናው ተርሚናል ግንባታ 86 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የቪአይፒ ተርሚናሉ ግንባታ ከአንድ ዓመት በፊት ተጀምሯል፡፡ የአገር ውስጥ ተርሚናል ማስፋፊያ ሥራም በቅርቡ ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ በአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ቀዳሚ መዳረሻ ትሆናለች፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ በነሐሴ 2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አቪዬሽን ግሩፕ እንዲቀላቀል መደረጉ ይታወሳል፡፡ ዋናው ተርሚናል እ.ኤ.አ. 2003 ዓ.ም. ሲመረቅ በዓመት ስድስት ሚሊዮን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም እንዳለው ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ብሔራዊ አየር መንገዱ ከተገመተው በላይ በማደጉ ምክንያት በዓመት 11 ሚሊዮን መንገደኞች በማስተናገድ ላይ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የተፈጠረውን መጨናነቅ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀርፈው ይታመናል፡፡

አሁን ያለው ተርሚናል የወለል ስፋት 48,000 ካሬ ሜትር ሲሆን፣ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ አዲስ የተገነባው ሕንፃ ወለል ስፋት 74,000 ካሬ ሜትር ነው፡፡

አዲሱ ሕንፃ 72 የመንገደኛ ማስተናገጃ መስኮቶችና 21 የመሳፈሪያ ቢሮዎች አሉት፡፡ ግንባታው በሰኔ 2011 ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ የፕሮጀክቱ ዋና መሐንዲስ አቶ ኃይሉ ለሙ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የቪአይፒ ተርሚናሉ ከአንድ ዓመት በኋላ፣ የአገር ውስጥ ተርሚናሉ ማስፋፊያ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የተርሚናሉን የማስተናገድ አቅም በዓመት ከ11 ሚሊዮን ወደ 22 ሚሊዮን መንገደኞች እንደሚያሳድገው ተገልጿል፡

Source ፡ ሪፖርተር

Comments are closed.