Take a fresh look at your lifestyle.

በኦሮሚያ ባንክ ላይ የተፈፀመው የ80 ሚሊየን ብሩ የዘረፋ ድራማ

755

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ንብረት የሆነ ገንዘብ ከአንድ ቅርንጫፍ ወደ ሌላው ሲዘዋወር እንደተዘረፈ ተሰምቷል።

ታህሳስ 19፣ 2011 ዓ. ም. በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዋና ከተማ ጭሮ ውስጥ የሚገኘው የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ 80 ሚሊዮን ብር ወጭ ያደርጋል።

ገንዘቡን ወደ ደብረ ዘይት ቅርንጫፉ ለማዘዋወርም ጉዞ ይጀምራል። ሆኖም ገንዘቡን የጫነው መኪና የታሰበበት ሳይደርስ መኤሶ ወረዳ አሰቦት አካባቢ መሳሪያ በያዙ ሰዎች ተከበበ።

ከዚያስ? የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሐላፊ ኮማንደር ጋዲሳ ንጉሳ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚከተለውን ብለዋል ” የተወሰኑ ኃይሎች ሽጉጥ የያዙ እንዲሁም ባዶ እጃቸውን የነበሩ ግለሰቦች መኪናውን መንገድ ላይ አስቆሙት። ሾፌሩን አስፈራርተው በማስወረድ አሰቦት ወደምትባል አካባቢ መኪናዋን ወሰዷት”

ከተዘረፈው 80 ሚሊዮን ብር ውስጥ በሽምግልና፣ በድርድርና በፍተሻ ማስመለስ የቻሉት ገንዘብ እንዳለም ይናገራሉ።

ይህን ያህል ገንዘብ አስመልሰናል ለማለት ሰነድ ባያጠናቅሩም “እጅ ከፍንጅ የተያዘ ገንዘብ የለም። አብዛኛው ብር የተመለሰው በጥቆማ ነው። በርካታ መኪና ይዘው ሲሄዱ በፍተሻ የተያዙ አሉ” ብለዋል።

ለመሆኑ አንድ ባንክ ከአንድ ቅርንጫፍ ወደ ሌላ ቅርንጫፍ ገንዘብ ሲያዘዋውር የሚደረግለት የጥበቃ ኃይል ወደየት ሄዶ ነው ዝርፊያው ሊፈፀም የቻለው? በሚል ቢቢሲ ኮማንደሩን ጠይቋል።

“በወቅቱ አብረው የነበሩት ፖሊሶች ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ መያዝ አልቻሉም። ወደ ሌላ እርምጃ ከተገባ በነሱም ደህንነት ላይ አደጋ ስለሚመጣ በልመናና በድርድር ገንዘቡን መውሰድ እንዲያቆሙ ለማድረግ ተሞክሯል። ማስፈራራትና ወደ ሰማይም ተተኩሷል።”

ዘራፊዎቹ በቁጥር ብዙ እንደነበሩ የሚናገሩት ኮማንደሩ፤ ዘራፊዎቹ ገንዘቡን ከዘረፉበት ቦታ ወደ ከተማ ይዘው ከሄዱ በኋላ ለመከፋፈል ሲሞክሩ የከተማው ከንቲባ “የሕዝብ ንብረት ነው” ብለው በድርድር ለማስቆም ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ይገልጻሉ።

ፎርቹን ጋዜጣ፤ ብሩ ወደ አዲስ አበባ መጓጓዝ ላይ እንደነበር ጠቅሶ 100 ግለሰቦች በዝርፊያው ተጠርጥረው ተይዘዋል ሲል ዘግቧል።

ከዘረፋው ጀርባ ያሉ ሰዎችን ማንነት ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ኮማንደሩ ቢናገሩም፤ “ዘራፊዎቹ ከሩቅ የመጡ አይደሉም” የሚል ጥቆማ ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ከድሬዳዋ ቅርንጫፍ 80 ሚሊዮን ብር ጭኖ በመኢሶ ወረዳ ሲተላለፍ ነበር። ያኔ ገንዘቡን ይዞ ይጓዝ የነበረው መኪና አሽከርካሪ አህያ ገጭቶ በአካባቢው ፖሊስ ተይዟል። በወቅቱ የተገኘው ገንዘብና አጓጓዡ የያዘው ሰነድ ላይ የሰፈረው የገንዘብ መጠን መካከል ልዩነት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።

ገንዘቡን መጫን የነበረበት መኪና ሰሌዳ ቁጥርና በፖሊስ የተያዘው መኪና ታርጋ ቁጥርም የተለያየ ነው ተብሎ ነበር። ለመሆኑ የዚህ ገንዘብ ጉዳይ ከምን ደረሰ? ኮማንደር ጋዲሳ ምላሽ አላቸው።

“አምሳ ሚሊዮኑን የሚያሳይ ሰነድ በገንዘብ ያዡ እጅ አልነበረም። ይህም ከኔትወርክ ችግር ጋር የተያያዘ ነው። መንገድ ላይ በኢሜይል እንልክላችኋለን የሚል ነገር ነበር”

ገንዘቡ ከወጣበት ቅርንጫፍ ጀምሮ ስለነበረው ሂደት ምርመራ ተእየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

መጀመሪያ ገንዘቡን ይጭናል ተብሎ የነበረው መኪና ሰሌዳው ቁጥር ሌላ ሲሆን፤ ይህም በአጋጣሚ ገንዘቡን ይጭናል ተብሎ የታሰበው ሾፌር በህመም ላይ ስለነበር ነው ብለዋል።

“ስለ ሹፌር ለውጥ የሚገልጽ ደብዳቤ ሳይቀየርብ ሌላ መኪና በመተካቱ ነው” ሲሉ የድሬዳዋ ስራ አስኪያጅ እንደነገሯቸው ኮማንደሩ ገልፀዋል።

“ገንዘቡ ህጋዊ መሆኑን ነው የምናውቀው። አሁን ምርመራ ላይ ነው። በቅርብ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል።

መኪና ውስጥ የተገኘው ገንዘብ ጉዳይ እስኪጣራ ድረስ ገንዘቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ቅርንጫፍ ውስጥ እንዲቆይ መወሰኑንም ኮማንደር ጋዲሳ ገልፀዋል።

ምንጭ ቢቢሲ

Comments are closed.