የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በሰላምና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ያደረጉት ስምምነት እስካሁን ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለ ኦዴፓ አስታወቀ።
ሁለቱ ፓርቲዎች በደረሱት ስምምነት መሰረት የጋራ ኮሚቴ ቢያዋቅሩም ከያዟቸው እቅዶች መካከል ብዙዎቹን መፈፀም አልቻሉም።
የሰላም ስምምነቱ አስፈጻሚ ኮሚቴና የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሞገስ ኢደኤ በሰጡት መግለጫ፤ በስምምነቱ መሰረት በአስራ አምስት ቀናት የሚፈጸም እቅድ አውጥተው ቢንቀሳቀሱም ከታቀደው አብዛኛው እስካሁን አልተተገበረም።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) አመራር ወደ አገር የገባው መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም ነው።
የአመራር ቡድኑ ከሁለት አስርተ ዓመታት የስደትና የትጥቅ ትግል በኋላ ወደ አገር ቤት ሲገባ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን ወስኖ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
“የህግ የበላይነት ጊዜ ሳይሰጠው ከዛሬ ጀምሮ መከበር አለበት” በማለት ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ሲናገሩ፤ በአገሪቷ የለውጡ መሪ ከሆነው መንግስት ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመስራት ወስነው መመለሳቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከስምምነቶቹ መካከል ትጥቅ ያልፈቱ የኦነግ ሰራዊቶች በአጭር ጊዜ ትጥቅ ፈተው ወደ ማስልጠኛ እንዲገቡ፣ ለአካባቢው ሰላም በጋራ በመስራት የህግ የበላይነት እንዲከበርና ለልማት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተንቀሳቅሰዋል።
ይሁን እነጂ በኦነግ በኩል ሰራዊቱ ትጥቅ ባለመፍታቱ በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶች ምክንያት ሆኗል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ፤ የተደረሰው ስምምነት በህዝቡ ዘንድ ብዥታን እየፈጠረ በመሆኑ በጋራ መግለጫ ለመስጠት ቢታሰብም እስካሁን አልተፈፀመም።
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሰው ህይወት መጥፋቱንና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም መዘጋታቸውን አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ብርቱ ጥረት ቢያደረግም ‘የኦነግ አመራር አባላት ግን ለእቅዱ መፈጸም ፈጣን ምላሽ አልሰጡም’ ብለዋል።
የተያዘው እቅድ ተግባራዊ ያልሆነው በኦነግ በኩል በእቅድ ያልተያዙ ጥያቄዎችን በማንሳቱ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር የሚደረጉ ጥረቶች ማነስና ለሰላም ፈጣን ምላሽ ባለመስጠቱ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ መንግስት ትጥቅ ፈተው ወደ አገር ውስጥ ለገቡ የኦነግ ሰራዊት አባላት በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም መሰረት የኦነግ አባላት ትምህርት ደረጃቸውንና ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ የስራ ምደባ የተሰጣቸው ሲሆን 747 አባላቱም በአዳማ ፖሊስ ማሰልጠኛ ገብተው እየሰለጠኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልሉ መንግስት በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብና በህዝብ መስዋዕትናት የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑንም አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
ኮሚቴውም የተጀመረው የሰላም ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን “ጥረቱን ይቀጥላል” ብለዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ያልሆነበትን ምክንያትና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ የኢዜአ ሪፖርተር የግንባሩን ቃል አቀባይ ቢያነጋግርም በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት አልቻለም።
Comments are closed.