Take a fresh look at your lifestyle.

4583 ካ.ሜ መሬት ለባለሃብቶች ያስተላለፈው ኃላፊ ለከንቲባ ፅ/ቤት በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

537

በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ አጃንባ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የመሬት አስተዳደር የሰነድ አልባ ዴስክ ኃላፊ የሆነው ግለሰብ ከሶስት የክፍሉ ባለሞያዎች ጋር በመተባበር መሬት ባንክ በኮድ ቁጥር 79 ገቢ የተደረገን ባዶ ቦታ የድርጅት በማድረግ እና መረጃ በማዛባት ለግለሰቦች ካርታ አዘጋጅቶ በመስጠት የህዝብን ውስን ሃብት ለግል ጥቅም በማዋል መንግስት ሊያገኘው የሚገባውን 12.1 ሚሊየን ብር አሳጥቷል፡፡

የመሬት አስተዳደር የሰነድ አልባ ዴስክ ኃላፊ የሆነው ግለሰብ ከተጠቀሱት ባለሃብቶች ጋር በግል በፈጠረው ያልተገባ ቁርኝት አንደኛውን ባለሃብት 600,000 እና ሁለተኛውን 400,000 ብር የሊዝ ዋጋ በማስከፈል በድርጅት ስም የመሬት ባንክ ንብረት የሆነውን 4583 ካሬ ሜትር አጥር የሌለው ቦታ አስተላልፏል፡፡

ይህን የታዘቡት የአከባቢው ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ በዘረጋው የጥቆማ መስጫ ቁጥር በመጠቀም ለከንቲባ ፅ/ቤት ጥቆማ አድርሰዋል፡፡

የከንቲባ ፅ/ቤት ጥቆማው እንደደረሰው አጣሪ ግብረሃይሉን በቀጥታ ወደ ተጠቀሰው ክፍለከተማ በመላክ ከመሬት ማኔጅመንት ቢሮ ጋር በመተባበር ባደረገው የማጣራት ስራ መሬቱ ያለ አግባብ መሠጠቱን እና በሰነድ አልባ ዴስክ ኃላፊው የተፈረመው ካርታም ትክክለኛ አለመሆኑን ካረጋገጠ በኃላ ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳያቸውን በማጣራት ላይ ይገኛል።
ሰሞኑን በተመሳሳይ ለከንቲባ ፅ/ቤት በደረሰ ጥቆማ ለካርታ አገልግሎት 90,000 ብር ጉቦ የጠየቀው የየካ ክፍለከተማ ሰራተኛ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።
የከተማችን ነዋሪዎች አሁንም የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር በመደገፍ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ አመራሮችን ፥ ባለሞያዎችን እና ግለሰቦችን በመጠቆም ለውጡን እንዲደግፉ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Comments are closed.