የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀይላን_ከበደ ዛሬ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሶሳ ወደ ቶንጎ ይጓዝ በነበረ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ላይ የደረሰውን የፈንጂ አደጋ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አደጋውን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት ስፍራውን በመቆጣጠር አካባቢውን የማጽዳት ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በቀጣይ የፌደራል ፖሊስ ከአደጋው ጋር በተያያዘ ምርመራውን እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።
አደጋው ኮድ 3 በሆነ ተሽከርካሪ ላይ መፈጸሙን ጠቅሰው፥ በአደጋው ንጹሃን ዜጎች መሞታቸውን አንስተዋል።
አደጋው የደረሰበት አካባቢ በርካታ ታጣቂ ሃይሎች የሚንቀሳቀሱበት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፥ የዛሬው አደጋም ለውጡን በማይቀበሉ ፀረ ሰላም ሃይሎች የተፈጸመ ነው ብለዋል።
የዛሬው አደጋ መንግስት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ማንነት ለመለየት ጥረት እያደረገ ባለበት ሰዓት መፈጸሙንም አውስተዋል።
በአደጋው የሞቱ ዜጎች ማንነትም በቀጣይ በምርመራ እንደሚለይም የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በቀጣይም ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በመለየትና መረጃዎችን በመስጠት የምርመራ ሂደቱን እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም በአደጋው ህይዎታቸውን ባጡ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል።
በዛሬው እለት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሶሳ ወደ ቶንጎ ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ የፈንጂ አደጋ የአስር ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
አደጋው የደረሰው ዛሬ ጠዋት 14 ሰዎችን አሳፍሮ ከአሶሳ ወደ ቶንጎ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ፥ ቤጊ መገንጠያ በተባለ ስፍራ ላይ በደረሰ የፈንጂ አደጋ ነው።
በአደጋው በተሸከርካሪው ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ የአስር ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፥ አራት ተሳፋሪዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ቤጊ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ
Comments are closed.