Take a fresh look at your lifestyle.

የቀድሞው ፕሬዝዳንት የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

557

የቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የቀብር ስነ ስርዓት በዛሬው አለት ከቀኑ በአስር ስዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርሰቲያን በክብር ተፈፅሟል።

ክብርት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ፣ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

ከጧቱ ሶስት ስዓት ጀምሮ በርካታ ስነ ስርዓቶች ተከናውነዋል።
መላው የአዲስ አበባ ህዝብ ከጧቱ ሶስት ስዓት ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ በመገኘት የስንብት ስነ ስርዓት አድርጓል።

በሚሊኒየም አዳራሽ ፍትሀተ ፀሎት ተደርጓል። የህይወት ታሪካቸው ተነቧል። ክብርት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ የስንብት ንግግር አድርገዋል።

ከሚሊየኒየም አዳራሽ ጀምሮ የቀብር ስነ ስርዓቱ እስከ ተፈፀመበት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ድረስ አስከሬናቸው በክብር ሰረገላ እና ማርሽ ባንድ ታጅቦ የአሸኛኘት ስነ ስርዓት ተደርጓል።

አስከሬኑ በክብር ቅደስት ስላሌ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እንደደረሰ በካህናት የመጨረሻ ፍትሀተ ፀሎት ተደርጓል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የማሳረጊያ ፍትሀተ ፀሎት አድርገዋል።

ክብርት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እና ክቡር የኢ.ዲ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፐሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳር ለማ መገርሳ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የቀደሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሸመ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና በፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ እና የአፍሪካ ሀብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ እንደ ቅደም ተከተላቸው የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

እንዲሁም ሁሉም የክልል መስተዳድሮች እና የሁለቱ ከተማ እሰተዳደሮች፣ የኢ.ዲ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣፣ የሰላም ሚኒስቴር እና በርካታ የፌዴራል ሚኒስቴር መ/ቤቶች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

ከቀኑ በአስር ስዓት አሰከሬኑ በተዘጋጀለት ቦታ ላይ በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል። በመጨረሻም መድፍ ተተኩሶ የቀብር ስነ ስርዓቱ ፍፃሜ አግኝቷል።

የቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ አገራቸውን ለ12 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ባገለገሉበት ወቅት በተለያዩ የሰብዓዊ ልማት ስራዎች ላይ በስፋት ይሳተፉ እንደነበር የታወቃል። ክቡር ፕሬዝዳንቱ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች እንዲቋቁሙና ወደ ስራ አንዲገቡ ደከምኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር ያደረጉ ታላቅ የአገር ባለውለታ ሰው ነበሩ።

በኢትዮጵያ የሰላም፣ የዲሞክራሲና ህዝባዊ የምክክር መድረክ እንዲጠናከር፤ የኢትዮጵያ የአይን ባንክ የአካል ክፍል ንቅለ ተከላ እንዲመሰረት እና አገልግሎት እንዲሰጥ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በራሳቸው ወጪ የሰላም አዳራሽ በማስገንባት በውስጡ የዲጂታል ቤተ መፅሀፍት በማቋቋም ለህዝብ ያበረከቱ፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎቸ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር አገር አቀፍ የአገር ሽማግሌዎች ማህበር የበላይ ጠባቂ በመሆን ያገለገሉ፤ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓድ ልማት እድገት እንዲስፋፋ በመላ አገሪቱ የችግኝ ተከላ እና የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች እንዲዘወተሩ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ታላቅ የአገር ባለውልታ ነበሩ።

በክልሉ ሰላም እንዲሰፈን በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማደረጋቸው ይታወቃል።

Comments are closed.